ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም? - Melkam Zena

ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም?

ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም?

ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም።?

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይላሉ የድሮ ሰዎች። ዘንድሮ ደግሞ ሰምቼ የማላውቀውን ጉድ ነው እየሰማሁ ያለሁት። መልካም ነገር ልበለው ወይስ ምን? እርሱን አውቄ ስጨርስ እደመድማለሁ።

ከፍያለው ቱፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለችው ማርያምና ሰዎች የሚነግዱባት ማርያም የሚለውን የቪዲዮ መልእክት ከለቀቀ በኋላ ሁለት ማርያሞች አሉ እንዴ? የሚል ከባድ ጥያቄ ተፈጠረብኝ። ከዚያም የምችለውን ያህል መጽሐፍ ቅዱሱን ማንበብ ጀመርኩና ጉዳዩን ቶሎ ለመረዳት ስለዚህ ነገር በደብን የሚያስረዳኝ ሰው ስፈልግ አንድ ሰው አገኘሁ። የተነሳነው ከከፍያለው ቱፋ መልእክት ቢሆንም አሁን ያገኘሁት ሰው ግን ከዚያም ጠለቅ ያለ መረዳት ነው የሰጠኝ። ጭራሽ ሁለት ማርያሞች አሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ስጠይቀው ኢትዮጵያዊቱን ማርያም ከቆጠርካት አዎ በማለት አስደነገጠኝ። እኔም ኢትዮጵያዊ ማርያም ስትል ምን ማለትህ ነው? እኔ የማውቀው ከእስራኤል ምድር የሆነችው የአብርሃም ዘር የሆነችውና ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ጸንሳ የወለደችውን ማርያም ነው፡ እርስዋ ደግሞ ኢትዮጵያዊ አይደለችም አልኩት፡ እርሱም መለስ አደረገና አየኸ ኢትዮጵያውያን አንድ መልካም የሚመስልና ራሳቸውን የሚያስደስት አስተሳሰብና ባህል አላቸው። ይኸውም ሁሉ ነገር መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ እንደተገኘ አድርገው መናገር ይወዳሉ። አንድ ነገር ስትናገር ይህ እኮ በመጀመሪያ የተገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ እኮ ከኢትዮጵያ ነው። ይሉሃል። አገራቸውን ከመውደዳቸው የተነሳ እንደሆነ ቢገባኝም እንዲሁ በጭፍኑ አገር ስለወደድን ብቻ ከኛ ያልተገኘውን ሁሉ ከኢትዮጵያ ተገኘ ብሎ ማውራት ግን አግባብ አይመስለኝም በታሪክ ያስወቅሳል በእግዚአብሔርም ያስጠይቃል። እውነት ነው አንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ እንደ ቡና ያሉ እንደ ዋልያ ያሉ ነገሮች ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ እናውቃለን ነገር ግን ሁሉም ነገር ምንጩ ኢትዮጵያ እንደሆነ መናገር እውነት አይደለም። ይህን ስትናገር ደግሞ አገር ወዳድ እንዳልሆንክ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ስለዚህ እውነት እንዳልሆነ የምናውቀውን ነገር ሁሉ አገሩን አይወድም እንዳንባል ብቻ አሜን ብለን እንቀበላለን። ይህን ሲናገር ቆይ ቆይ አሁን ወደተነሳንበት ነገር እንመለስና ስለኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ንገረኝ አልኩት። እርሱም መለሰና ምን መሰለህ አስቀድሜ እንደነገርኩህ ሁሉንም ነገር ኢትዮጵያዊ መልክ አላብሶ መፍጠር ልማዳቸው የሆነ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ያለችውን ሐዋርያት በአካል የሚያውቁአትን በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚያውቁአትን ማርያም አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ የምናውቃት። ለወንጌሉ ክብር የሌላቸውና በምናባቸው በፈጠርዋት የልብ ወለድ ማርያም ትርፍ ለማግኘት የፈለጉ በየዘመኑ የተነሱ የኢትዮጵያ ባህታውያንና ካህናት ሐዋርያትና ራሱም አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማያውቃትን ማርያም ፈጥረው በህዝቡ ልብ ሲስሉ ዘመናት አልፈዋል። ስለዚህ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ማርያም ሲል እነርሱ ፈልስፈው በልቡናው የሳልሉትንና ከወላጆቹ የሰማትን ማርያምን እንጂ እውነተኛዋን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ማርያም ማለቱ አይደለም። በእርግጥ ወንጌሉን አንብቦ ስለማያመሳክር ወላዲተ አምላክ ማርያምን የሚል ይመስለዋል። ቄሶቹና ባህታውያኑ የጻፉትን የኢትዮጵያዊቱን ማርያም ታሪክና ተአምር አንብበን በወንጌሉ ካለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ስናወዳድራት ግን ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውን እናውቃለን። ለምሳሌ ዋና ዋና የሆኑትን ነገሮች እናንሳና እናወዳድራቸው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ያለችው ወላዲተ አምላክ ማርያም የአዳም ልጅ ናት። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር ሰው ሁሉ ከአንዱ አዳም እንደተወለደና ከአዳም የተወለደው ሰው ሁሉም ደግሞ ከአዳም የውርስ ኃጢአትን እንደተካፈለ ይናገራል። (ሮሜ.5፡12-15) ወላዲተ አምላክ ማርያምም የአብርሃም ዘር የሆነች እስራኤላዊ ስትሆን ኤልሳቤጥ አክስትዋ የሆነች እንደማንኛችንም ከሰው ዘር የተወለደች ሰው ናት። ነገር ግን የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርስዋ እንዲወለድ ተመርጣ በድንግልና የወለደችልን ናት። የወለደችው ጌታ የእርስዋም መድኃኒት እንደሆነ ራስዋ ተናግራለች። (ሉቃ.1፡ 47-48) ምክንያቱም እርስዋ መንፈስ ቅዱስ ጸልሎአት ኃጢአት የሌለበትን ጌታ ብትወልድም እርስዋ በራስዋ ግን ከአዳም የውርስ ኃጢአትን የተካፈለችና በወለደችው ጌታ የመስቀል ሥራ ስርየትን ያገኘች ናት። እንደማንኛችንም ሞት ገዝቶአት በሞት ከዚህ ዓለም ተለይታለች። ጌታችን የሞተው እኛን ለማዳን እንጂ እርሱ ሞት አይገዛውም ነበር። ድንግል ማርያም ግን በሰዎች ሁሉ ላይ የሚገዛው ሞት ስለሚገዛት ነው የሞተችው።

ቀሳውስት የፈጠርዋት ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ግን ኃጢአት የሌለባት ንጽህት ናት። የአዳም የውርስ ኃጢአት አልደረሰባትም ይላሉ። ስለዚህ በነርሱ ትምህርት ሰው ሆና ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእትነትና ደም ኃጢአትዋ የተወገደ ወይም ደግሞ ንጹህ ስለሆነች የኢየሱስ ክርሰቶስ ደም ያላስፈለጋት ሰው ናት ማለት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ግን የሰው ዘር ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ እንደነበረና በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሞት ብቻ እንደታረቀ ይናገራል። በቄሶቹ አስተምህሮ ግን ኢትጵያዊትዋ ማርያም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ጸንሳ ብትወልድም እርስዋ ግን የርሱ ማዳን አያስፈልጋትም ነበር ማለት ነው። ስለዚህ የመስቀል ሞቱ እርሱዋን አያካትትም ብለው ያስተምራሉ። በነርሱ አስተምህሮ ማርያም የአዳም ልጅ ስለሆነች የውርስ ኃጢአት አለባት ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሞት ነው የዳነችው ብሎ ማመን ኑፋቄ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ያለችው እመቤታችን ማርያም ግን «ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤» ( ሉቃ.1፡47-48) በማለት መድኃኒትዋ እንደሆነ ተናግራለች።  ሌላው ወንጌሉ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተና እንደተነሳ እንዳረገም ይናገራል። ድንግል ማርያም ግን እንዳረገች አይናገርም። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ግን አርጋለች ብለው ጽፈውላታል። ከዚህም ሌላ በወንጌሉ ያለችው ማርያም የዓለምን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ናት። የወለደችው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ሞቱ ዓለምን ከራሱ ጋር በማስታረቅ ይህንን የመስቀሉን ስራ ለኣለም ሁሉ እንዲሰብኩለትና በርሱ መሞትና መነሳት የሚያምን ሁሉ የዘላለምን መዳን እንደሚያገኝ ተናግሮ ሐዋርያቱን ወደ ዓለም ሁሉ ልኮአቸዋል። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ግን ራስዋ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር የምታስታርቅ ናት። ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችበት ዋና ምክንያት እርሱ ዓለምን እንዲያድን ሳይሆን እናቱ እንድትሆንና በእናትነት ዝምድናዋ አማካኝት ልጄ ወዳጄ ይህን ማርልኝ እያለች ሰዎችን ከርሱ ጋር እንድታስታርቅ ነው። ያው እንደምታውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰው መሄድ ይወዳል። አንድ መስሪያ ቤት ሊሄድ ሲል ለመሆኑ የምታውቀው ሰው አለ? ተብሎ ነው የሚኬደው። ያው ከዚያ ተነስቶ አይደል አሁንስ ሙስና እያስቸገረን ያለው። መንፈሳዊው ሙስና ግን ከመሬታዊው ሙስና የከፋ ነው። ምክንያቱም የመንግስት ሙስና ግፋ ቢል ኪሳችንን ነው የሚያራቁተው መንፈሳዊው ሙስና ግን ውስጥን ልብን መንፈስ ነፍስን ያራቁታል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሐይማኖት መምህራን ይህንን የህዝቡን ባህል ተገን በማድረግ የምትመቸውን ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህርይ ያላትን በዘመድ የምታድነውን ማርያምን ፈጥረውለታል። በወንጌሉ ያለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ስራዋና መመረጥዋ የዓለም መድኃኒት የሆነውን ጌታ መውለድዋና እርሱም በመስቀል ተሰቅሎ ሰዎችን ማዳኑ ነው። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ግን በራስዋ ምልጃ ነው የምታድነው። ማንም ሰው እናቱን እንደሚወድ በሚገባ የሚያውቁት የሐሰት ቀሳውስት እናቱን የሚወደውን ህዝብ ማርያምን እናት አድርገው ሰጡት። ማንም ሰው እናቱ ከመጡበት ስስ ብልቱን እንደተካ የሚያውቁት ብለጦች የኢየሱስ ክርስቶስም ስስ በልቱ እናቱ ናት በርስዋ ከመጡበት መሸነፍ እንጂ ሌላ ምርጫ የለውም በማለት አሳመኑት። ሌላው ቀርቶ ሰባ ስምንት ሰው አርዶ የበላ ሰው እንኳ በስምዋ እፍኝ ውሀ ሰጥቶ ጸድቆአል በማለት ህዝቡን አፉን አስከፈቱት። ሰባ ስምንት ሰው የበላ ሰው በስምዋ እፍኝ ውሀ ሰጥቶ ከጸደቀ ሌላ ምን ያስፈልጋል? ለጽድቅ መኖር የኢየሱስ ክርስቶስን የመስቀል መስዋእትነት ማመን ምን ያደርጋል? ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ማርያም ፈጥረው የእውተነተኛዋን ማርያም ስራ ሸፈኑት። ስምሽን የጠራ ተዝካርሽን የዘከረ እምርልሻለሁ ብሎአታል። ስለዚህ በርስዋ ቃል ኪዳን አምናችሁ በስምዋ ጠላ እየጠመቃችሁ ድግስ እየደገሳችሁ እኛን ብትንከባከቡ ሰተት ብላችሁ መንግስተ ሰማያት ነው የምትገቡት ብለው ሐዋርያት የማያውቁትን አገር በቀል ወንጀል ሰበኩ። እውነተኛዋ ማርያም ግን የሚያድነን ጌታ ነው የወለደችልን። ያም ጌታ በመስቀል ተሰቅሎ አዳነን። ያ የመስቀል ፍቅሩ ግድ ብሎንም እንከተለዋለን።  ምናልባት ካልሰማህ እንጂ ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም በኢትዮጵያም ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች። ለምሳሌ በአንዱ ተአምራዋ ላይ ለሚኒሊክ አባት ለንጉስ ሳህለ ስላሴ ተገልጣ ስለበጌምድሩ ንጉስ ቴዎድሮስ እንዲህ ብላ እንደተናገራቸቸው ተጽፎአል። አንድ ቴዎድሮስ የሚባል ክፉና ጨካኝ ንጉስ ይነሳል ልጅህንም ሚኒሊክን ማርኮ ይወስዳል እኔ ግን አስመልጨ አምጥቼ ዙፋንህን እሰጠዋለሁ ብላቸዋለች ይላል። ብቻ ኢትዮጵያዊትዋን ማርያምና በወንጌሉ ያለችውን ማርያም ብዙ ነገር ነው የሚለያቸው። ጨርሶ አይመሳሰሉም ማለቱ ይቀላል። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም በገድልዋ በተአምርዋ ሰዎችን የምትገድል የምትቀስፍ ኃይለኛ በቀለኛ ሆኖ ነው የተጻፈችው። እርስዋ የምትራራው በስምዋ ከዘከርክ ደግሰህ ካበላህ ህንጻ ካሰራህ ብቻ ነው። በአጠቃላይ በስምዋ ሁሉን ካደረግህ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ጋር ታስታርቅሃለች። እንደዚህ ካላደረግህ ግን መጨረሻህ ሲኦል መሆኑን እወቀው። የወንጌልዋ ማርያም ግን አምነን የምንድንበትን መድኃኒት ክርስቶስን ነው የወለደችልን። እርሱም በመስቀል ላይ ሞቶ አድኖናል። እርስዋን መድኃኒትን ስለወለደችልን እግዚአብሔር መድኃኒት የሆነውን አምላክ እንድትወልድ ስለመረጣት ብጽእት እንላታለን እናከብራታለን እንጂ በስምዋ ዘክረን አይደለም የምንድነው። በወለደችው አምነን ነው የምንድነው። እርሰዋ በር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችልን ናት። የሚገርምህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስናነብ በበዓለ ሐምሳ ቀን እመቤታችን ማርያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ለጸሎት ትተጋ እንደነበረ ይናገራል። መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ለብዙ ሺህ ህዝብ ቆሞ ወንጌልን ሰበከ። ወንጌሉን የሰሙት ሰዎች ልባቸው ተነክቶ ምን እናድረግ? ብለው ሲጠይቁት በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲያገኙ መከራቸው። ያመኑትን ተጠመቁ። እመቤታችን እዚያው ከነርሱ ጋር በአካል ቆማ እንኳ ወደርስዋ እየጠቆመ እርስዋ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታስታርቃችሁ አላለም። እርስዋም ቢሆን ትክክለኛዋ ማርያም ናትና ይህንን አላለችም። የአገራችን ቄሶች ቢሆኑ ኖሮ ምን የሚሉ ይመስልሃል? እንኳንስ በአካል ከነርሱ ጋር ቆማ ቀርቶ አሁን በምናብ በፈጠርዋት ሌላ ማርያም እንኳ የሚያደርጉትን ተመልከት። ሐዋርያት ግን ኢትዮጵያዊትዋን ማርያም አያውቁአትም። በምናብ ሳትፈጠር ተአምረ ማርያም ሳይጻፍ ነው የሞቱት። ያው ተአምረ ማርያም የተጻፈው በአስራ አራተኛው ክፍል ዘመን እንደሆነ የምታውቅ ይመስለኛል። ራሱ ተአምሩ ይህንን ይናገራል። እንግዲህ ከሐዋርያት ዘመን አንድ ሺህ አራት መቶ አመት በኋላ ማለት ነው። ስለዚህ ሐዋርያት እንደ ኢትዮጵያ ቄሶች ማርያም አይሰብኩም ነበር። የወለደችውን የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርሰቶስን ነው እንዲሰብኩ የተላኩት የሰበኩትም እርሱን ነው። እስኪ ቆም ብለህ አንድ ጥያቄ ጠይቅ። ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው አስራ ሶስት መልእክቶች ውስጥ ስንት ጊዜ ነው ማርያምን የጠቀሰው? አንድ  ቦታ ላይ ያውም ስለኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለመናገር «ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤» በማለት ከሴት የተወለደውን በሚለው ቃል ላይ እመቤታችንን ጠቅሶአል። (ገላ.4፡4) በዚህ ሁሉ ስብከቱና መልእክቱ ውስጥ ማርያምን አለመጥቀሱ ስለማይወዳት ይመስልሃል? አይደለም። ከርስ የተወለደውንና ዓለሙን ያዳነውን ጌታ እኮ ነው እየሰበከ ያለው። ስለዚህ እግዚአብሔር በርስዋ የጀመረውን ስራ ነው እኮ እየፈጸመ ያለው።  ማርያምን መውደድ ማለት እግዚአብሔር ከርስዋ በመወለድ ሊፈጽም የወደደውን ነገር መፈጸም ማለት ነው። ይኸውም ሰዎች ዓለምን ለማዳን ከርስዋ የተወለደውን ጌታ አምነው እንዲድኑ ወንጌልን መስበክ ነው። ትክክለኛዋ ማርያም አለምን ለማዳን ከርስዋ የተወለደውን ጌታ አምነው በሚድኑ ሰዎች ደስ ይላታል። ምክንያቱም እርሱን የወለደችበትን ከርሱ ጋር ብዙ መከራ ያየችበት ምክንያቱ ይህ ነውና። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ግን ዋናው ዓላማዋ በስምዋ የሚዘክርና ለቄሶች የሚያበላ ሰው ማግኘት ነው። ይህንንም የሚሰብኩት ቄሶቹ ናቸው። ሐዋርያት ያልሰበኩትን ወንጌል ነው የሚሰብኩት። በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ብር ሲሰራ የተያዘ ሰው ምን ያህል በህግ የሚጠየቅ ይመስልሃል? ተመሳሳይ ማርያም ተመሳሳይ ወንጌል የሚሰራና የሚሰብክ ግን አይጠየቅም። ህዝቡ ካልነቃና ወደ ወንጌሉ ካልተመለሰ ነገሩ ይቀጥላል። ከወንጌሉ ወጥተው ይህንን ያደረጉና እያደረጉ ያሉ ሰዎች የሚጠየቁት በፍርድ ቀን ብቻ ይሆናል። ስለዚህ አስተውሎ ለሚያይ ሰው ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም አንደኛ ፈጽሞ አገር በቀልና በአገር ውስጥ ፈላስፎች የተፈጠረች ጽንሰ ሐሳብ ናት። በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ ያሉ እህት አብያተ ክርስቲያናት በወንጌሉ አንድነትና በመድኃኔ ዓለም በክርስቶስ ኢየሱስ እንደዚሁ በወንጌሉ ባለችው ወላዲተ አምላክ የሚስማሙ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ቀሳውስት በፈጠሩአት ማርያም ግን አይስማሙም። ኢትዮጵያዊትዋ ማርያም ለኢትዮጵያ ብቻ ናት። ተአምርዋም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ነው። እነርሱ የፈጠርዋት ናትና የነርሱ ናት። እኔ የምፈራው ትንሽ ቆየት ብለው ክርስትና የተጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ከአዲስ አበባ የአርባ አምስት ደቂቃ መንገድ በሆነችው ሶደሬ አጠገብ ባለችው በናዝሬት ከተማ ነው  ኢየሱስ ክርስቶስም ያረገው በመካከል ባለችው በደብረ ዘይት ነው እንዳይሉ ብቻ  ነው። ለነገሩ ማን አለባቸው? ህግ አይጠይቃቸው የፈለጉትንስ ቢሉ። የናዝሬት ስም ወደ አዳማ ደብረ ዘይት ወደ ቢሾፍቱ መቀየሩ ግን ይህንን ሐሳባቸውን ሳያሰናክልባቸው አይቀርም። ለማንኛውም ወንድሜ ወንጌሉን ካነበብክ ብዙ አገር በቀል የክርስትና ተለጣፊ ታሪኮች ታገኛለህ። እውነተኛውንና ያልተበረዘውን ክርስትና የምታገኘው በመጀመሪያ ወንጌልን ከሰማው ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባና በሶስተኛው ክፍለ ዘመን ወንጌልን ከሰበኩት ከመጀመሪያው ጳጳስ ከአቡነ ሰላማ ነው። ፊሊጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወንጌልን ሲሰብከውና አጥምቆ ክርስቲያን ሲያደርገው ስለማርያም አማላጅነት አልሰበከውም። ቢፈልግማ ኖሮ ማርያም በአካል ስለነበረች ወደርስዋ በወሰደው ነበር። ነገር ግን ሰው የሚድንበትን የእውነት ወንጌል ከነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ጀምሮ ከሰበከው በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ በመጠመቅ የዘላለምን ደህንነት አገኘ። ውይ ታድሎ ይህ ሁሉ ተለጣፊ ነገር ሳይጻፍ ክርስትና ሳይበረዝ ለመጽደቅ ተዝካር ሳያስፈልግ ከልጅዋ ከወዳጅዋ የሚል ስምሽን የጠራ ተዝካርሽን የዘከረ የሚል ድርሰት ሳይጻፍ ኩልል ያለውን የእውነት ወንጌል ሰምቶ በተሰቀለለት ጌታ በማመን ደህንነትን ያገኘ ኢትዮጵያዊ። በሶስተኛው ክፍለ ዘመን የመጣው አቡነ ሰላማም ከታላቁ የወንጌል አባት ከቅዱስ አትናቴዎስ ተልኮ ስለመጣ እውነተኛውን ወንጌል ሰበከ። ህዝበ ኢትዮጵያም በመጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመናት የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሰምተው ካመኑት ጥቂት አገሮች በቀዳሚነት ተቀመጠ። ይህ ትልቅ መታደል ነበር። ወንጌሉ ሳይበረዝ ቢቀጥልና ካህናቱ እንደ ሐዋርያት ወንጌልን በታማኝነት ቢሰብኩ ኖሮ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የክርስቲያን አገር ሆና አጎራባች አገሮችን በወንጌል ባጥለቀለቀች ነበር። ብቻ ምን ያደርጋል ለሆዳቸውና ለክብራቸው ያደሩ ሰዎች ተነስተው ስምሽን የጠራ ተዝካርሽ ያደረገ ወዘተ የሚል ነገር አመጡ። የህዝቡን አለመማር አይተው ብዙ አታለሉት። ግብጻውያኑም ለብዙ ዘመናት እነርሱ እንኳን የማያምኑበትን ብዙ ታሪክ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንዲነበብ በማድረግ አሳሳቱን። መቼም አንዱ ታሪክ ከስንክሳር እንዲወጣ ባለፈው ሲኖዶስ መወሰኑን ሳትሰማ የቀረህ አይመስለኝም። ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዳይሆኑ ሐዋርያት አዘዋል የሚል ታሪክ ግብጾቹ በማስገባት ሁለት ሺህ ለሚጠጋ አመታት ካታለሉን በኋላ አሁን ገና ሲኖዶሱ ነቃባቸው። መቼም ሁልጊዜ ካለመንቃት ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላም ቢሆን መንቃት ጥሩ ነው። ግን ግን ጥያቄ የፈጠረብኝ ነገር ስንትና ስንት ከወንጌሉ ውጭ የሆነ አፈ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ሞልቶ እያለ ለይተው ያችን ነገር ከስንክሳር ለማውጣት መምከራቸው ለምንድን ነው? መልሱ የነርሱን ክብር የኢትዮጵያን ህዝብ ክብር የሚነካ ሆኖ ስለገኙት እንጂ ለእውነተኛው ወንጌል በመቆርቆር አይደለም። ምክንያቱም ለእውነተኛው ወንጌል ቢቆረቆሩማ ኖሮ ከዙፋኑ ወርዶ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት የሰራውን ድንቅ የመዳን ሥራ የሚሸፍኑና የሚቃረኑ ብዙ አፈ ታሪኮችንና ተረቶችን ያስወግዱ ነበር።  ነገር ግን ከእውነተኛው ወንጌል መሸፈን ይልቅ የራሳቸው ክብር መነካት ስለቀደመባቸው ያችን ታሪክ ለማረም ተነስተዋል። ቢሆንም ተመስገን ነው። ብልህ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል እንደሚባለው ገድልና ተአምራቶቹ ሁሉ እንከን የሌለባቸው አምላካዊ መገለጦች ናቸው ብለው ሲከራከሩ የከረሙት አሁን ከስንክሳሩ ይህ ጉድለት ተገኝቶአል ብለው ማረማቸው ሌሎቹንም ለማረም ዕድል ይከፍታል ብየ አስባለሁ። ሐሰት በግብጻውያንም ተጻፈ በኢትዮጵያውያን ያው ሐሰት ነው። በወንጌሉ እየተፈተሸ ሊጠራ ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ የዋህና እግዚአብሔርን የሚፈራ መሆኑ አድቫንቴጅ ሊወሰድበት አይገባም። ስለእውነተኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት እምነቱ ትክክሉን ሊማር ይገባል ባይ ነኝ። ለዛሬ በዚሁ ይብቃን በማለት ከጠየቅኩት በላይ የሆነ መልስ ሰጥቶኝ እብስ አለ። እኔም ይህንን ሁሉ ስሰማ ወንጌሉን የማንበብ ረሀቤ ጨመረብኝና ንባቤን ቀጠልኩኝ።

%d bloggers like this: