ኢትዮጵያ እንደገና መልካም መሪ ልታገኝ ደጃፍ ላይ የደረሰች ይመስላል።

ኢትዮጵያ እንደገና መልካም መሪ ልታገኝ ደጃፍ ላይ የደረሰች ይመስላል።

መልካም ዜና

ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን የሰማን እለት በጣም ነበር ያዘንነው። መንግሥት የተለያዩ ጉድለቶች ቢኖሩበትም እርሳቸው ግን መልካምና ቀና መሪ ነበሩና። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ እንደገና መልካም መሪ ልታገኝ ደጃፍ ላይ የደረሰች ይመስላል።  ስለዚህ ኃዘናችን ወደ ደስታ ስሜት እየተለወጠ ነው።

መቸም ከተወሰኑ በጥላቻ ብቻ ከተሞሉና እነርሱ ስልጣን ካልያዙ ወይም አገር ካልተበጠበች ከማይረኩ ሰዎች በስተቀር አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካምና ቀና አሳቢ መሪ እንደሚሻ የታወቀ ነው። በተለይ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከማንኛውም ጊዜ ይልቅ ደህና መሪ የሚያስፈልጋት ጊዜ ነው። ብዙዎቻችን ለመልካም መሪ የምናስቀምጠው መለኪያ የተለያየ ሊሆን ቢችልም አብላጫው ህዝብ የሚስማማበት ግን በአስተሳሰብ መልካም የሆነና በሳል መሪ እንደሚያስፈልግ ነው። ስለ አገር ልማት ሲነገር አንድ ደጋግመን የምንለውና የምንሰማው አባባል አለ። የሰው አእምሮ ወይም   አስተሳሰብ ካልለማ እንዲሁ ፎቅ በመደርደርና መንገድ በመስራት ብቻ አገር ለማ ማለት ግንጥል ጌጥ ነው እንላለን። ይህ አባባል ብዙዎች ሊስማሙበት የሚገባና ተገቢ ይመስለኛል፡ ልማት ሁሉ መጀመር ያለበት ከአስተሳሰብ ነው፡ አንድ ህብረተሰብ ለማ የሚባለው እርስ በርስ ሲከባበር ሲቀባበል አብሮ በአንድነት ሲቆም ክፉውን ከመካከሉ ሲያስወግድና በበጎ አስተሳሰብ የተሸመነ ህብረተሰብ ሲሆን ብቻ ነው፡ በዚህ መሠረት ላይ ተመስርቶ አገርን ማልማት ቋሚ የሆነ እድገት እንዲመጣ ያደርጋል፡ የሰው አስተሳብ ሳይለማና ሳይቀየር መሰረተ ልማቶች ቢዘረጉ ግን ያው ህብረተሰብ መልሶ እንደሚያፈርሳቸው እየተከሰተ ያለው ነገር እያመላከተን ነው። በመሆኑም ከዚህ ተነስተን ቀጣዩ መሪም በአስተሳሰብ የለማና ሰፊ የሆነ አገርን የማስተዳደር ጥበብ ያለው በሳል ሰው ቢሆን እንመኛለን። ዛሬ ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ የዶክተር አቢይ የኦህዴድ ሊቀ መንበር ሆኖ መመረጥና ወደ መሪነቱ ለመምጣት አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው ሰው መሆናቸውን መስማቴ ነው።

እኔ እኚህን ሰው በተለያዩ ንግግሮች ስሰማቸው በሳልና ቅን ሰው መሆናቸውን በማየት በጣም እየተደሰትኩ የነበረ ሲሆን በምን ዓይነት ሥራ የተሰማሩ መሆናቸውን ግን አላውቅም ነበር። እንዲያውም የግላቸውን ሥራ የሚሰሩ ዜጋ እንጂ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው አላውቅም ነበር። ዛሬ ቪኦኤ ባቀረበው ዘገባ ግን የኦህዴድ ሊቀ መንበር ሆነው እንደተመረጡ ሰማሁ። ይህንን ስሰማ ይህች አገር ሊነጋላት ነው መሰለኝ ነበር ያልኩት። ምክንያቱም እንደ ዶክተር አቢይ አይነት በመልካም አስተሳሰብ የተሞላ ሰው ወደ መሪነቱ መጣ ማለት ብዙ መልካም ነገር እንደሚከተል ስለማምን ነው። ብዙ ጊዜ የለመድነው በወታደራዊ አስተሳሰብ የተካኑ ወይም ጠንካራነታቸውን በወታደራዊ ኃይል የሚያሳዩ መሪዎችን ነው እንጂ በመልካም ሐሳብ የታጠቁ በጥበብ የተካኑ ሰዎችን አልለመድንም። ለምን እንደሆነ አላውቅም አፍሪካ ጠንካራ መሪ የምትለው ረግጦ የሚገዛን መሪ ነው። እኝህ ሰው ግን ዶክተር አቢይ ማለቴ ነው ጉልበታቸው ብርታታቸው ያለው አስተሳሰባቸው እይታቸው ነው። ሰውየው ሲናገሩ ከሰማሁአቸው ውስጥ የሚከተሉትን ብንሰማ እንዴት በሳልና አስተዋይ ሰው መሆናቸውን ያሳያል። በእውነት እንደዚህ ዓይነት ሰው ይህን ያህል ወደ አገሪቱ መሪነት መጠጋጋቱ የሚያስደስት ሲሆን እንዲያው ተመርጠው እስከማይ ድረስ አልደርስ ብሎኛል። እባካችሁን የኚህን ሰው መመረጥ እውን ማድረግ የምትችሉ ማለትም በምርጫው ቀጥታ ተሳትፎ ያላችሁ ሰዎች እኚህ ሰው እንዲመረጡ በማድረግ ደስታየን ፈጽሙልኝ።

እግዚአብሔር አምላክ መልካም መሪዎችን በመስጠት ኢትዮጵያን ይባርካት።

 

 

%d bloggers like this: