የባህር ዛፍ ታሪክ በኢትዮጵያ

የባህር ዛፍ ታሪክ በኢትዮጵያ

የባህር ዛፍ ታሪክ በኢትዮጵያ – አሁን አገራችን ውስጥ ያሉት የባህር ዛፍ ዘሮች መጀመሪያ ከገቡት እደሚለዩ ያውቃሉ ?

ዓጼ ምኒልክ አማካሪያቸው የነበረውን ፈረንሳያዊውን ሞንዶን ቪዳሌን ጠርተው “ዛፉ አለቀ። እንኯን ለቤት መስሪያ ለማገዶ የሚሆን ጠፋ፣ ምን ይሻላል?” አሉት። “አውስትራሊያ ውስጥ ኤካሊፕቶስ የሚባል አንድ የዛፍ ዘር አለ። ያ ዛፍ ቶሎ የሚደርስ ነው። ያ ዛፍ መጥቶ ቢተከል በ፲ አመት ውስጥ አገሪቱ ጫካ ትሆናለች” አላቸው። ምኒልክ በነገሩ ደስ አላቸው። በዛፉ ታሪክ ቢደሰቱም ባንድ ሰው አሳብ እርምጃ አይወስዱም ነበርና ቸናስኪን ኣስጠርተው የዛፉ ነገር እንዴት ይሁን? አሉትና ሞንዶን ስለነገራቸው ዛፍ ታሪክ ኣጫወቱት። ቸናስኪም በእርግጥ ጥሩ የዛፍ ዘር መሆኑን ነገራቸው። “ይሁን እንዳላችሁት ይሆናል” ብለው ከሸኙት በሇላ ለባቡር ሃዲድ መንገድ ስራ የመጣውን እንግሊዛዊውን ካፒቴን ኦብሬን ኣስጠሩትና እንደገና ስለዛፉ ጉዳይ ጠየቁት። ኦብሬም ጥሩ ዛፍ መሆኑን ኣረጋገጠላቸው። ከዚህ በሇላ ምንሊክ ሶስት የተለያዩ የውጭ ሃገር ሰዎች የመሰከሩለትን የዛፍ ዘር በ፲፰፻፹፮ 1886 ዓ/ም እንዲመጣ አዘዙ።

ችግኙ ተፈልቶ እንደደረሰ ስሙ የባህር ዛፍ ተባለ። ከባህር ማዶ የመጣ ለማለት ነው። ምኒልክ ባህር ዛፍ የሚለውን ስም ከሰየሙ በሇላ “የባህር ዛፍ የተተከለበትን መሬት ግብሩን ምሬአለሁ” ብለው አወጁ ህዝቡም በሽሚያ ይተክል ጀመር። እንዲያውም ችግኙ ተወዶ አርባ ችግኝ ባንድ ጥሬ ብር መሸጥ ጀመረ። አተካከሉም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ተስፋፋ።
በአዲስ አበባ ከተማ የተተከሉት ዛፎች ደን ሲሆኑ ውሃ እየደረቀ ሄደ። ጉድጏዶቹ፣ ምንጮቹም ደረቁ። ከራስ መኮንን ቤት በታች ያለችው ራስ መኮንን ምንጭ የምትባለዋ ብቻ ቀረች። በአዲስ አበባ ላይ ከባድ የውሃ ችግር ደረሰ። ይህን ችግር ያመጣው ባህር ዛፍ መሆኑ ስለታወቀ ባህር ዛፎች እንዲነቀሉ ታዘዘ። ማንም ሰው ካለው ባህር ዛፍ ሩቡን እያስቀረ ሌላውን እንዲነቅል ተባለ፣ ተነቀለ።

ምኒልክም “ትከል ብለንው ተከለ። አሁን ደግሞ ንቀል አልንው። ዛፍ ቀርቶ ልምጭ ከሚቸግርበት ሁኔታ ልንደርስ ነው እና ምከሩት” አሉ። በምክሩ መሰረት ሌሎች የዛፍ ዘሮች ከውጭ እየመጡ ተተከሉ። የባህር ዛፉም ጥናት አብሮ ቀጥሎ ነበርና የመጀመርያው ባህር ዛፍ ውሃዎቹን ካደረቀ በሇላ እንዲጠፋ ሲደረግ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከመጣው ዘጠኝ አይነት የባህር ዛፍ ዘር ውስጥ ተመርጦ የተሻለው እንዲራባ ተደረገ። ከዚያ በሇላም የባህር ዛፍ ተክል በመላው እትዮጵያ ተስፋፋ።
ምንጭ:
አጤ ምኒልክ
በጳውሎስ ኞኞ

%d bloggers like this: