የኢትዮጵያን ሕዝብ ትክክለኛ ችግር የሚያወቁና መፍትሄውን የሚጠቁሙ ሰው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ተመርጠዋል። ለመሆኑ ህዝቡ ይቀባላቸው ይሆን??

Doctor Abey Ahmed

የኢትዮጵያን ሕዝብ ትክክለኛ ችግር የሚያወቁና መፍትሄውን የሚጠቁሙ ሰው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ተመርጠዋል። ለመሆኑ ህዝቡ ይቀባላቸው ይሆን??

አንድ ጺማቸው  በጣም በጣም ብዙና ረጅም ጺም የነበራቸው መነኩሴ ነበሩ ይባላል። እኚህ አባት አንድ ጥሩ ያልሆነ ጠረን እየሸተታቸው ይቸገሩና ተማሪዎቻቸውን እባካችሁ አንድ ነገር ይሸተኛል ፈልጋችሁ አስወግዱልኝ ብለው ይጠይቃሉ። ተማሪዎችም ያንን መልካም ያልሆነ ጠረን ምንጭ ቢፈልጉ ቢፈልጉ ያጡታል። በመጨረሻም አባ ተቸገሩና ግራ በመጋባት ጺማቸውን አሸት ዳበስ ሲያደርጉ አንድ ነገር ጠጠር ይልባቸዋል። ጺማቸውን ስርስር አድርገው ሲያወጡት ከትናንት በስቲያ ምግብ ሲበሉ ድንገት ተንጠባጥባ ጺማቸው ውስጥ የገባች ትንሽ ሥጋ ያገኛሉ። ለካ እርስዋ ነበረች ካፍንጫቸው ሥር ሆና እንደዚያ በመጥፎ ጠረን ያስቸገረቻቸው።

ብዙ ጊዜ በጣም በቅርባችን ያሉ ችግሮች አይታዩንም። በምንነዳው መኪና ግራና ቀኝ ያሉት የጎን መስተዋቶች ከሩቅ ያለውን አጉልተው ሲያሳዩን በጣም የተጠጋንን መኪና ግን አያሳዩንም።  እንደዚሁም አንድ ችግር ሲገጥመን ከኛ ራቅ ባሉ ቦታዎችና ሰዎች ነው ስንፈልገው የምንውለው። በዚህ ምሳሌ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ስንመለከት የዚህ ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን። በአገሪቱ ያለው ችግር ምንጭና ምክንያት ምንድን ነው ተብሎ ሲጠየቅ ብዙኃኑ በተለይ ወጣቱ የሚሰጠው ምላሽ እጅግ የተሳሳተና ትክክለኛውን የችግር ምንጭ የማያመለክት ነው። በተለይ ወጣቱ በአብዛኛው ሁለት ችግር ይታይበታል። አንደኛ የሚፈልገውን ለውጥ አያውቅም። ለውጥ ሲፈልግ ኪሳራውንና ትርፉን አስልቶ ሳይሆን እንዲሁ መንግስት እንዲለወጥልኝ እፈልጋለሁ ብቻ ይላል። አሁን ያለውን መንግስት ያልፈለግሁት ለምንድን ነው? የሚመጣውስ መንግስት ምን አይነት እንዲሆን ነው የምፈልገው? እንዴትስ ሊመጣ ይችላል? የሚለውን ቆም ብሎ ሲያስብ አይታይም። እንዲሁ ዝም ብሎ ለውጥ እፈልጋለሁ ይላል። በእርግጥ ይህ ችግር አሁን የጀመረ አይደለም። በስድሳዎቹ ንጉሱን ያወረደው ወታደርና ወጣትም እንዲሁ እንደነበር ከውጤቱ ታይቶአል። ወጣቶቹ ንጉሱን ማውረድ እንጂ ቀጥሎ ስላለው ብዙም ስላላሰቡና ስላልተዘጋጁ ከድጡ ወደ ማጡ ነበር የሄዱት። የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭና ምክንያት ሁለተኛው ነጥባችን ነውለ። ይኸውም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሌላ የምንለው ከኛ ጎራ ውጭ ያለው ወገን አድርጎ የማየትና እኛን ከችግሩ የጸዳ አድርጎ የማየት ችግር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ወገን ወይም አንድ የሕብረተሰብ ክፍል ወይም የተወሰኑ ባለስልጣኖችን ብቻ የችግር ምንጭ አድርጎ ማየትና ያንን ክፍል ብናስወግድ ችግሩ ይፈታል ብሎ የማሰብ ዝንባሌ በብዛት ይታያል። ይህም ችግሩን ከምንጩ አይቶ መፍትሄ መስጠት እንዳይቻል ያደርጋል። ምክንያቱም ችግሩ እከሌ ነው ችግሩ ይህ ወገን ነው ተብሎአላ። በመሆኑም ትኩረቱ ሁሉ ያንን ወገን ከስልጣን ለማውረድ ስለሚሆን እውነተኛው ችግር ሳይፈታ ያልፋል። ችግርን ለመፍታት የችግሩን ምንጭ ከማወቅ ይጀምራል። ችግሩን በቅጡ ሳናውቅ መፍትሄ ለማምጣት መነሳት ግን ሌላ ችግር መፍጠር ነው። እንዲሁ በግምት አንዱን ስንቆርጥ አንዱን ስንቀጥል ብዙ ነገር እናበላሸለን። የሚገርመው ብዙዎቹ የአገራችን ፖለቲከኞች መፍትሄውን የማያውቁ ነው የሚመስለን። እውነቱ ግን ችግሩ ምን እንደሆነም አያውቁም። የአንድ ችግር ምንጭ ምን እንደሆነ አለማወቅ የአንድን ችግር ምንጭ አውቆ መፍትሄውን አለማወቅ የተሻለ ነው። ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ ከታወቀ ትኩረቱ ሁሉ መፍትሄውን ወደ ማግኘት ይሆናልና። የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ሳያውቁ መፍትሄ ለመስጠት የሚሞክሩ ሰዎች ግን በጣም አደገኞች ናቸው። ሳይለኩ ይቆርጣሉ። ያልተቀደደ ይሰፋሉ። አንዳንድ ዶክተሮች የሚፈጽሙትን የህክምና ስህተት ስንሰማ በጣም ያስደነግጣል። የቀኝ እግር ህመም ደርሶበት ቀኝ እግሩ እንዲቆረጥ ህክምና ክፍል የገባን ሰው በስህተት ችግር ያለበትን ቀኝ እግር ትቶ ጤነኛውን ግራ እግር መቁረጥ ትንሽ  ስህተት አይደለም። ታማሚውን ሁለት እግሩን አሳጡት ማለት ነው። የችግራችንን ምክንያትና ምንጭ ሳናውቅ የምንወስዳቸው መፍትሄዎች ሁሉ እንደዚህ አደገኞች ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ይህንን የሚያሳየን ታሪክ አለ። እግዚአብሔር ዮናስ የሚባለውን ነቢይ ወደ ነነዌ ሰዎች ሄዶ ንስሐን እንዲሰብክላቸው ሲልከው አሻፈረኝ በማለት ሌላ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ተርሴስ ሄደ ይለናል። ከዚያም እግዚአብሔር ዮናስ በተሳፈረባት መርከብ ላይ ከባድ አውሎ ነፋስን አመጣና ትናወጥ ጀመር። የመርከቡ ሰዎችም ነጋዴዎች ነበሩና ህይወታቸውን ለማዳን የመላ ምት መፍትሄ መሞከር ጀመሩ። ያደረጉትም የከበሩ እቃዎችን የያዙባቸውን ሻንጣዎቻቸውን እያነሱ ባህር ላይ መጣል ነበር። እቃዎቻቸውን ሁሉ ባህር ላይ ቢጥሉም ችግሩ ግን መፍትሄ አላገኘም። በመጨረሻ ሁሉን ሞክረው ሲጨንቃቸው በመርከቡ ውስጠኛ ክፍል ወደተኛው ወደ ዮናስ መጡና ይህ ሁሉ ችግር እየደረሰብን ምነው ተኝተሃል? ብለው ቢጠይቁት ችግሩ የደረሰባቸው በርሱ ምክንያት እንደሆነና እርሱን አንስተው ባህር ላይ ቢጥሉት ማእበሉ ጸጥ እንደሚል ነገራቸው። አንስተው ሲጥሉትም ማእበሉ ጸጥ አለ። አያችሁ የትኛውም ማእበል ጸጥ የሚለው ትክክለኛውን ምላሽ ሲያገኝ ነው። እኚህ ሰዎች ግን አስቀድመው ችግሩ ዮናስ መሆኑን ባለማወቃቸው ብዙ ከሰሩ። የችግሩ ምክንያት ያልሆኑትን ውድ ንብረቶቻቸውን ወደ ባህር ጣሉ።  ምናለ ነቢዩ ዮናስ ቀድሞ ቢነግራቸው ኖሮ? ዛሬም እንዲሁ ነው። በአገራችን ያለው የነውጥ ችግር ምክንያት ብዙዎቻችን በምንጠቁምበት አቅጣጫ አይደለም ያለው። ችግሩ ያለው በሰው ማለትም በሁሉም ሰው አስተሳሰብ ውስጥ ነው። የሰው አስተሳሰብ ሲበከል አገር ትበከላለች። እስኪ ቆም ብላችሁ ከትውልዱ አንደበት የሚወጣውን ቃል አድምጡ። መርዝ አይደለም እንዴ? በተለይ ችግሩን እኛ እናውቃለን መፍትሄም አለን የሚሉትማ አንደበታቸው የመርዝ መርዝ ነው። ስለዚህ እንደ መድኃኒት እየመረረን ለመዋጥ ፈቃደኞች ከሆንን  ችግሩ ያለው ሁላችንም ውስጥ ነው።  ምንም እንኳ የችግሩ ክፍፍል ሊለያይ ቢችልም ማለትም ችግሩን ከመፍጠርና ከማባባስ አኳያ የተለያዩ ሰዎች የሚጫወቱት ሚና በአንጻራዊ ሁኔታ መጠኑ ሊለያይ ቢችልም ባልተንሸዋረረና ባላደላ ዓይን ካየነው ሁሉም ለችግሩ አስተዋጽኦ አለው። ሁሉም ደግሞ ለመፍትሄው አስተዋጽኦ አለው። እያንዳንዱ ራሱን ቢያጸዳ አገር ትጸዳለች።

ዶክተር አቢይ ችግሩን አይቸዋለሁ ችግሩም የአስተሳሰብ ችግር ነው ይሉናል።በብዙ ንግግሮቻቸው እንደሰማሁት እኚህ ሰው የሰው የችግር ምንጭ በደንብ የገባቸው ይመስለኛል። እንደብዙዎች የህመሙን ውጫዊ ስሜት በህመም ማስታገሻ ለማስታገስ ከመሞከር ይልቅ የችግሩን ሥርና ምንጭ ለማግኘት አጥልቀው ቆፍረዋል። የችግሩም ምንጭ የሰው አስተሳሰብ መበላሸት ወይም ደግሞ በትክክለኛ እውቀት አለመታነጽ ሆኖ አግኝተውታል። ስለዚህ አስተሳሰባችንን እንድንቀይር የተንሸዋረረ እይታችንን እንድናስተካክል ይመክራሉ። በተለይ በአንድ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ይላሉ። ሰው አስተሳሰቡ ሲበላሽ ሁሉን ሲኦል አድርጎ የማየት ችግር ይገጥመዋል በገነት እየኖረ ሲኦል ሆኖ ይታየዋል ብለዋል። እኚህ ሰው ወደራሳችን እንድመለከትና ብዙ ነገሮች እየተበላሹ እያየን ራሳችንን እያሞካሸን እንዳንኖር ይልቅስ ችግሮቻችንን በድፍረት እንድናይ ይጋብዙናል። በአንድ ንግግራቸው በምጸት እንዲህ ይላሉ «ኢትዮጵያ ጨዋ አገር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። ኢትዮጵያ ግን መኪና ውጭ ማሳደር አይቻልም። ከጨዋነታችን ብዛት መኪና ውጭ ረስተን የገባን እንደሆነ ስንመለስ ስፖኪዮ ስለማናገኝ ማለት ነው» በማለት ተናረዋል። ይህ እንዲሁ ከላይ የለበስነውን የእኔነት ካባ አውልቀን ትክክለኛውን አሁን እየታየ ያለውን ማንንታችንን እንድናይና ለመፍትሄ እንድንነሳ የሚጋብዝ ንግግር ነው።

 

አዎ የአስተሳሰብ መበላሸት የሁሉም ችግሮች ምንጭ ነው። የአስተሳሰብ መበላሸትን እንደ ከባድ የወረርሽኝ በሽታ ቆጥረን ካልተከላከልነው በጣም አደገኛና አጥፊ ነው። አንድ ሰው ወይም የተወሰኑ ሰዎች አገርን የሚመርዝ ህዝብ በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ ሐሳብና ንግግር ሲያራምዱ ህዝቡ ተረባርቦ ሐሳባቸውን ሊያስወግድ ይገባል። አሁን እንደምናየው ግን በስመ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሰዎች ቆሻሻ የሆነና አገር የሚበክል ነገር ሲናገሩ ህብረተሰቡ ዝም ብሎ ከማለፍም አልፎ ይቀበላቸውና ይደግፋቸው ጀምሮአል። አንድ ሰው በከተማ መንገዶች በቤታችን በር አካባቢ ቆሻሻ ሲጥል ብናይ ዝም አንልም። በተለይ የኛ መኖሪያ አካባቢ ከሆነ ለጸብ መጋበዛችን የሚቀር አይመስለኝም። ካልሆነ ካልሆነ ለከተማው ህግ አስከባሪዎች ተናግረን ቆሻሻው በማይገባው ቦታ እንዳይጣልና አካባቢ እንዳይበክል ለማድረግ እንሞክራለን። ጣናን የወረሰው የእምቦጭ አረም ችግር ያሳሰበንን ያህል የህዝቡን አእምሮ እየወረሰ ያለው እንቦጭ የሆነ አስተሳሰብ ሲያስጨንቀን አይታይም። የሚገርመው ግን የከተማን ወይም የመንደርን  ንጽህና ለማስጠበቅ ይህን ያህል የምንሞክር ጀግኖች የሰው አእምሮ መርዝ በሆነ አስተሳሰብ ሲበከል እያየን ዝም ማለታችን ነው። የሰው አእምሮ በክፉ አስተሳሰብ መበከል ግን እጅግ የከፋ ነገር ነው። ለምርጫ ከቀረበ የሰው አእምሮ ከሚቆሽሽ ከተማና መንገድ ቢቆሽሽ ይሻላል።

በመሆኑም ዶክተር አቢይ ይህንን ችግር በሚገባ ስላዩ አስተሳሰባችን ላይ አተኩረው ይሞግቱናል። እይታችንን የሚያሸወርረውና መልካሙን ማየት ትተን ክፉ ነገር ብቻ እንድናይ የሚያደርገው የሐሳብ መበላሸት እንደሆነ ይጠቁሙናል። ከዚህ በፊት የተደረጉ ስህተቶችን እንኳ ለትምህርታችን ማለትም ከዚያ ስህተት ተምረን ወደተሻለ እንድንሄድ እንጂ ለቂም በቀልና ለመለያየት ልንጠቀምባቸው አይገባም ይሉናል። የኢትዮጵያ ህዝብ አኚህን ሰው ቢሰማ በብዙ ይጠቀማል ባይ ነኝ። እያንዳንዱ ወደ ሌላው ከመጠቆሙ በፊት የራሱን ችግር ቢያይ ከዚያ በኋላ በመፈራረድ መንፈስ ሳይሆን በመደጋገፍ አንዱ የሌላውን ችግር በማገዝ ቢራመድ ወደ መፍትሄ ይመጣል።  እኚህ ሰው ችግሩን ወደ ሌላ በመጠቆም አላታለሉንም። ራሳችንንም እንድናታልል አላገዙንም። ይልቅስ እያንዳንዳችን ወደ ራሳችን እንድናይ አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል በቅን ድፍረት ይመክሩናል። የራሳችን ችግር እኛ ነን። ከፈለግን ግን ሐሳባችንን አስተካክለን መፍትሄ መሆንም እንሻለን ይሉናል። በእውነት የጎልማሳ አዛውንት ብያቸዋለሁ። ስጋቴ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ይቀበላቸው ይሆን? የሚለው ነው። እኚህ ሰው ቅን ልብ ያላቸው የፍቅር ሰውና ትሁት በመሆናቸው ለአንዳንድ ሰዎች  በጣም ደግና ቅን የሆኑባቸው  ይመስለኛል። ማርም እኮ ሲበዛ ይመራል፣ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ወዘተ የሚሉትን ክፉ ምሳሌዎች መስሎ በጣም ደግ ነህና እኛን አትወክልም እንዳይላቸው እሰጋለሁ። ምክንያቱም ክፉዎች የዘሩት ክፉ ሐሳብ በብዙዎች ዘንድ ከበቀለ እኚህ ሰው ለሚያቀርቡት መልካም ሐሳብ ልቡን አይከፍትምና ነው። አንዳንድ ጊዜ መልካም መሪ ብቻ ያጣን ይመስለናል ግን እኮ ምናልባት መልካም ህዝብ መሆንም እያቃተን ሊሆን ይችላል። ህዝቡን ሁልጊዜ መልካም አድርጎ መሪዎችን ብቻ ክፉ ማደረግ ትክክል አይመስለኝም። መልካም መሪ እንደሚያስፈልገን መልካም ህዝብም ያስፈልገናል። መልካም ውጤት የሚገኘው ህዝብም መሪዎቹም መልካም ሲሆኑና እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ ነው ነው።

መልካም መሪ ለመልካም ህዝብ መልካም ህዝብ ለመልካም መሪ።

ዶክተር አቢይ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልዎ።

መልካም ዜና።

%d bloggers like this: