የኢትዮጵያ ገንዘብ በሚኒሊክ ጊዜ።

የኢትዮጵያ ገንዘብ በሚኒሊክ ጊዜ።

ዓፄ ምኒልክ የመጀመሪያዎቹን የብር ኖቶች በህዝብ ዘንድ ቶሎ ተቀባይነት አለማግኘትን አስመልክተው ያስነገሯቸው ፈገግ የሚያደርጉ አዋጆች።

ዳግማዊ ዓጼ ምኒሊክ የመጀመሪያዎቹን የመገበያያ ገንዘቦች ወደ ገበያ ባስገቡበት ጊዜ ልክ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ በህዝብ ዘንድ አዲስ ነገር ያለመቀበል ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ከዚህ በፊት በነበረው ነባር ብር ላይ ያለው የማርትሬዛ መልክ ተለውጦ የምኒልክ መልክ በመተካቱም ህዝቡ ሌላ ገንዘብ እየመሰለው አልገበያይ አለ። በዚህም ምክንያት አጤ ምኒልክ በ፲፱፻ ዓ/ም (1900) ነሃሴ ፪ (2)ቀን የሚከተለውን አዋጅ አወጁ።

“ለገበያ መገበያየት እንዲመች ብዬ በኔ መልክና በኔ ስም ያሳተምኩትን ብርና ሩብ የሌላ መንግስት ነው፣ በዚህ አልገበያይም እያልክ እርስ በርስህ ትጣላለህ አሉ። አልቀበልም ማለትህ ከቀድሞው ብርና ሩብ ምን የጎደለ ነገር አለና ነው? አሁንም የፊተኛውም ያሁኑም ብርና ሩብ ትክክል ነውና በዚያው በቀድሞው ልክ መገበያየት ነው። እንግዲህ በዚህ በአዲሱ ብርና ሩብ ነገር የተጣላ ሰው መቀጫህን ባንድ ብር ፲ ብር፣ ባንድ ሩብ ፭ ብር ትከፍላለህ። ከዚህ ወዲህ ይህንን የሇለኛውን ብርና ሩብ አልቀበልም የሚለውን ሰው እጁህ ይዘህ ኣምጣልኝ። ገንዘቡን እመርቅልሃለሁ።”

አጤ ምኒልክ ይህንን አዋጅ ቢያውጁም አሁንም ቢሆን ተቀባይ አጣ። እንዲያውም ሁሉንም ትቶ እንደጥንቱ በጥይት ይገበያይ ጀመር። ይህንንም የሰሙት ምኒልክ ህዳር ፳፪ (26) ቀን ፲፱፻፩ 1901 ሌላ አዋጅ አወጁ።

“ከዚህ ቀደም ነጋዴው፣ ወታደርም፣ ባላገርም የሆንክ ሰው ሁሉ በየገበያውና በየመንገዱ በየስፍራው ሁሉ በጥይት ስትገበያይ ትኖር ነበር። አሁን ግን በኔ መልክና ስም የተሰራ ብር፣ አላድ፣ ሩብ፣ ተሙን፣ መሃለቅ አድርጌዋለሁና በዚህ ተገበያይ እንጂ እንግዲህ በጥይት መገበያየት ይቅር ብያለሁ። የሚሸጥም ጥይት ከቤቱ ያለው ሰው ሁሉ እጅምሩክ እየወሰደ ለጅምሩክ ሹም ይስጥ። ጥይትም ለመግዛት የፈለገ ሰው እጅምሩኩ እየሄደ ይግዛው። ይህንንም አዋጅ አፍርሶ ጥይት እርስ በራሡ ሲሻሻጥ እና ሲገዛዛ የተገኘ ሰው ገዢውም ሻጩም ስለቅጣታቸው ባንድ ጥይት አንድ አንድ ብር ይክፈሉ። ይህንንም አዋጅ አፍርሶ በጥይት ሲሻሻጥ አግኝቶ ወደዳኛ ያመጣ ሰው በቅጣጥ ከሚከፍሉት ገንዘብ እኩሌታውን ለያዢው መርቄለታለሁ።”

ምንም እንኯን አጤ ምኒልክ እነዚህን አዋጆች ቢያውጁም ህዝቡ በቀላሉ ሊቀበላቸው እና የቀድሞውን መገበያያ ሊተው አልቻለም። ገዢና ሻጭም ሲገናኙ “በጃንሆይ ብር ነው ወይስ በሴት ብር?” እያሉ ይለዩ ጀመር። የሴት ብር የሚባለው በብሩ ላይ የንግስት ማርትሬዛ መልክ ስላለበት ነበር። በህዝቡ እምነት መሰረት በሁለቱ ብር ላይ ትንሽ ልዩነት አለ። ሁለቱን ብር ለያይተው በሚዛን ላይ ሲያሥቀምጡ የማርትሬዛ ብር ትንሽ ደፋ ያረጋል – ከምኒልክ ብር የማርትሬዛ ብር ከበድ ይላል ማለት ነው። በተጨማሪ ሁለቱን ብሮች ተራ በተራ ድንጋይ ላይ ሲጥሏቸው የማርትሬዛው ብር ክልል ያለ ድምፅ ሲያሰማ የምኒልክ ብር ግን ዶፍ የሚል ድምፅ ስለሚያሰማ ህዝቡ ንፁህ ብር አይደለም በማለት በውዴታ ቀርቶ በግዴታም አልቀበለው አለ።

ምንጭ:
አጤ ምኒልክ
በጳውሎስ ኞኞ

%d bloggers like this: