ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሰባኬ ወንጌል ሆነ።

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሰባኬ ወንጌል ሆነ።

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሰባኬ ወንጌል ሆነ።

መጋቤ ሐዲስ ተብሎም ተሰይሞአል። ( በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ)

ካህናቱና ጳጳሳቱ ወንጌሉን ካላስተማሩን ከምእመናኖቻችን ብንማርስ? ወንጌል በሁለት ዋና ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው። የአምላኩን ህግ አፍርሶ ለሞት የተዳረገውን የሰው ልጅ ሊያድን የመጣውን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ማመንና በፍቅር መኖር ናቸው።

ስለዚህ ወንጌል በመድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑትን አህዛብ አምነው ከኃጢአታቸው እንዲድኑ ይሰበካል። አምነው ክርስቲያን የሆኑት ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲኖሩ ያስተምራል።  የቤተ ክርስቲያንና የወንጌል አባቶች ዓላማም እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማድረግ ማገልገል ነው። ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ብዙ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ይህንን ተልእኮ በሚገባ በመፈጸማቸው ዛሬ እኛ ክርስቲያኖች ለመባል በቅተናል። ቅዱሳን አባቶቻችን ነፍሳቸውን እስከመስጠት ድረስ በዓለም ዙሪያ እየዞሩና መከራን እየተቀበሉ ወንጌልን የሰበኩ ሲሆን በወንጌሉ አምነው ክርስቲያኖች የሆኑት ምእመናን ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲኖሩ አስተምረዋል። ማስተማር ብቻም ሳይሆን ራሳቸው ምሳሌ በመሆን አሳይተዋል። ለምሳሌ በየገዳማቱ ያሉ አባቶችና አርድእት የሚኖሩት የፍቅር ኑሮ ለዚህ ማሳያ ነው። ከተለያየ ማህበረሰብና አካባቢ የመጡ ብዙ መናንያን እንደ አንድ ቤተሰብ መቁነን እየተካፈሉ መኮሬታ እየቆረሱ ለረጅም ዘመናት መኖር የፍቅር ህይወት ነው። ዛሬ ሁኔታው እየተለወጠና ፍቅር እየቀዘቀዘ ቢመጣም ይህንን ኑሮ የኖሩ ብዙዎች አሉ። አሁን ያሉት ብዙኃኑ ጳጳሳትና ቀሳውስት ግን ይህንን የአባቶቻቸውን ፈለግ እየተከተሉ አለመሆናቸውን እያየን ነው። እንደ ቀዳሚ አባቶቻቸው ንጹሁን ወንጌል መስበክ ትተው ራሳቸው የደረሱትንና ምድራዊ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን ተረት ይሰብካሉ። እንኳንስ ወንጌልን ሊሰብኩ  ለራሳቸው አያውቁትም። ሁለተኛ በዘር በስልጣን በፖለቲካ እርስ በርስ ሲነካከሱ ይታያሉ። በዚህም ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ከነርሱ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር እያዩ አይደሉም። ይልቅስ ሌት ተቀን እነርሱን ለማስታረቅና ቤተ ክርስቲያንዋን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ የሚታዩት አልተማሩም የሚባሉት ምእመናን ናቸው። ከጳጳሳቱና ከካህናቱ የፍቅርና የወንጌል ቃል ጠፍቶ አንዳንድ ጊዜ ከነዚሁ ምእመናን ወንጌሉ በተለያየ መንገድ ሲሰበክ እናያለን። ለዛሬ ለዚህ ምሳሌ አድርጌ የማቀርበው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁንን ነው። ምናልባት እንዴት ዘፋኝ የሆነን ሰው ለወንጌል ተልእኮ ምሳሌ አድርገህ ታቀርባለህ? የሚል ሰው ብዙ መሆኑ አይቀርም። እውነቱን ለመናገር እኔ ዘፋኝ ወንጌልን መስበክ ይችላል ወይ? ለመሆኑ ክርስቲያንስ ይዘፍናል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ አይደለም የተነሳሁት። እንዲሁ በዘፈኑ ውስጥ ካካተታቸው ቃላቶች አንዳንዶችን ወስጄ እንዴት ከካህናቱ የበለጠ ወንጌልን እንደተናገረ ለማሳየት ብቻ ነው እንጂ ስለድምጻዊው ማንነት ወይም የእምነት አቋም ለመናገር አይደለም። ነገር ግን ካህናቱ ሊሰብኩት የሚገባውን ፍቅር ሲሰብክ እንደዚሁም ካህናቱ የሚደብቁትና እንዲያውም በራሳቸው ተረት የከደኑትን እውነተኛ የመዳን ወንጌልም በዘፈን አስመስሎ ገልጦታል። እውነቱን ለመናገር አንድ ነገር ዘፈን ወይም ዝማሬ የሚባለው በይዘቱ ተለክቶ ቢሆን ኑሮ የዚህ ሰው አንዳንድ ዘፈኖች መዝሙር መባል ነበረባቸው የብዙ ዘማሪያን ዝማሬዎች ደግሞ ዘፈን መባል ነበረባቸው። ነገር ግን የዝማሬ መለኪያችን በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የተቀረጸ ከሆነ ዘማሪው ወይም ዘማሪትዋ ነጠላ አጣፍተው ያዜሙት ከሆነ መዝሙር ብለው ከሰየሙት ዝማሬ ይባላል። እንደ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ከውጭ ከተዜመ ግን ዘፈን ይባላል። የህብረተሰባችን መለኪያ ይህ ስለሆነ እንጂ ከብዙ ዘማሪያን ፍሬ የሌለው ገለባ ዝማሬ የዚህ ድምጻዊ ዘፈኖች ዝማሬ ቢባሉ የሚሻል ነው። ዛሬ ሁለቱን ዜማዎቹን አንስተን እንመልከት። በመጀመሪያ ከማንኛውም ትክክለኛ ስድር ካለው ቅኔ ትምህርት ወስደን ወንጌልን ልንሰብክበት እንደምንችል ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ግሪክ ባደረገው የወንጌል ጉዞ ወደ አቴና እንደመጣ ግብረ ሐዋርያት ይናገራል። በዚያም ሲደርስ ጨርሶ እግዚአብሔርን የማያውቁና እንዲያውም በመሰዊያቸው ላይ ለማይታወቅ አምላክ የሚልን ጽሑፍ የጻፉ ሰዎች አገኘ ይለናል። አይ… እንዴት ደስ የሚሉ ሰዎች ናቸው። የማያውቁትን አናውቅም የሚሉና እስኪያውቁ ድረስ የሚጠብቁ ሐቀኞች። እንደዛሬው ዘመን እንዲሁ በግብዝነት አይኔን ግንባር ያድርገው እኔ አምላክን አውቀዋለሁ የማይሉ ሰዎች ነበሩ። እኛም የማናውቀውን አናውቅም ብንል ኖሮ ይህንን ሁሉ ድርሳን ከልባችን አውጥተን ባልጻፍንም ነበር። ባልተረጋገጠና የወንጌሉ ድጋፍ በሌለው ታሪክ እምነታችንን ባልመሠረትን ነበር። እነዚህ ሰዎች ለማይታወቅ አምላክ እያሉ ሲጠብቁ አንድ ቀን ደጉ እግዚአብሔር ሳያውቁ የሚያመልኩትን እንዲያሳውቃቸው ቅዱስ ጳውሎስን ላከላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው

ግብረ ሐዋርያት 17

23 የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና፦ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።

24 ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤

25 እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።

26-27 ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።

28 ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።

29 እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።

ይህንን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ ካለ በኋላ  ስለእግዚአብሔር ማንነት ለማስረዳት የጠቀሰውን ተመልከቱ።  «ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።» ከእነርሱ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ የተቀኙት ነገር በወንጌሉ ሲፈተሽ ትክክልና ከወንጌሉ ጋር የሚስማማ ነበር። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን ሳያውቁ ያዜሙትን በመጥቀስ ነው እንግዲህ ስለ እውነተኛው አምላክ ያስተማራቸው።

ስለዚህ እኛም ለጊዜው ቴዲ አፍሮ ዘፋኝ ነው የሚለውን ክርክር እንተውና የተናገረውን ከወንጌል ጋር የሚስማማ ቃል እንመልከት። እውነት እላችኋለሁ ከብዙ ቀሳውስትና ጳጳሳት የተሻለ ነገርን ነው የሰበከው።

አንደኛ።

«ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ

ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ።»

ብሎ ያዜመው መዝሙሩ ከወንጌሉ ቃል ጋር በእጅጉ የሚስማማ ነው። መዝሙር ያልኩበት ምክንያት ይዘቱ የወንጌል ቃለ ስለሆነ ነው። በዚህ መዝሙሩ ቴዎድሮስ ካሳሁን ትክክለኛውን የሰው በሽታ ምን እንደሆነ አሳይቶናል። ጥላቻ የውስጥ በሽታ ነው። ሰው በጠና መታመሙ የሚታወቀው ፍቅር ሲያጣ ነው። የጤንነት ብቸኛ መለኪያ ደግሞ ፍቅር ነው። ወንጌሉም የሚለው ይህንኑ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ትእዛዝ አንዲት ስትሆን ያችም ፍቅር ናት።

«እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።» ዮሐ.13፡34

እንዲያውም የርሱ ተከታዮች  መሆናቸውነ ዓለም የሚያውቃቸው በፍቅር ብቻ እንደሆነ እንዲህ በማለት ነገራቸው። «እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።» ዮሐ.13፡35

ለመሆኑ እግዚአብሔር ብዙ ትእዛዝና ህግ የለውም እንዴ? እንዴት ነው አንዲት ትእዛዝ ብቻ የሚሰጣቸው? የዚህን ሚስጢር ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደዚህ በማለት ይነግረናል

«እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።» ሮሜ.13፡8-10

ስለዚህ በእግዚአብሔር ስም ብዙ ትእዛዝና ወግ የምናበዛውና መንፈሳዊ ለመምሰል የምንሞክረው ፍቅር ስለሌለን ነው። ፍቅር ከሌለን በጣም ብዙ ነገር ያስፈልገናል። የፍቅርን ቦታ ሊሞላ የሚችል ምንም ነገር ስለሌለ የውስጣችንን ጥማት ለማርካት ብዙ መንፈሳዊ ወጎችንና ባህሎችን ለመፈጸም እንሞክራለን። ፍቅር ቢኖረን ግን ፍቅር ሁሉንም ጠቅልሎ ስለያዘ አንዲት ትእዛዝ ብቻ የምትገዛን ሰዎች እንሆናለን። ፍቅር ስላለን ለባለንጀራችን ክፉ አናደርግም። አናመነዝርም አንሰርቅም በሐሰት አንመሰክርም አንመኝም። ይህንን ሁሉ የማናደርገው ፍቅር ስላለንና ወንድሞቻችንን እህቶቻችንን ስለምንወድ ነው። መስረቅ መመኘት በሐሰት መመስከር ወዘተ ሁሉ የሚፈጸመው በባለንጀራ ላይ ነው። ስለዚህ ባለንጀራችንን በእግዚአብሔር ፍቅር መውደዳችን እነዚህን ሁሉ በርሱ ላይ እንዳንፈጽም ያግደናል ማለት ነው። ለዚህም ነው ፍቅር የህግ ፍጻሜ ነው የተባለው።

ይህ በሚገባ ይገባን ዘንድ አንድ የምናውቀውን ምሳሌ እንውሰድ። የቴክኖሎጂው ስልጣኔ እንደዚህ ባልበዛበት ዘመን እያንዳንዱ የሚሰሩ እቃዎች አንድ የራሳቸው የሆነ ስራ ለመስራት ነበር የሚሰሩት። ለምሳሌ የፎቶ ካሜራ ሲሰራ ፎቶ እንዲያነሳ ብቻ ነው። ስልክ ሲሰራ ሰውን ለማናገር ብቻ ነበር። ቴሌቪዥን ሲሰራ ዜና ለማድመጥ ብቻ ነበር። መኪና ሲሰራ ለመጓጓዣ ብቻ ነበር ወዘተ። አሁን ግን አንድ ስልክ ማናገሪያ ብቻ ሳይሆን የፎቶ ካሜራም ነው የቪዲዮ ካሜራም ነው መጽሐፍም ነው ጋዜጣም ነው የባትሪ መብራትም ነው ራዲዮም ነው ብቻ ምኑ ተቆጥሮ። በእጃችን ያለው አንድ ስልክ በጣም ብዙ ነገሮችን ጠቅልሎ የያዘ ነው። በመሆኑም ስልክ ካለን ሬድዮ የፎቶና የቪዲዮ ካሜራ ጋዜጣ ወዘተ መግዛት አያስፈልገንም። አንዱ ስልካችን እነዚህን ሁሉ ይሰጠናልና። ሌሎችም ከላይ የጠቀስናቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደ ድሮው አንድ ሥራ ብቻ እንዲያከናውኑ ሆነው አይደለም እየተሰሩ ያሉት። በውስጣቸው የተለያየ ነገር እንዲሰሩ ሆነው እየተሰሩ ነው። እንደዚሁም ፍቅር ካለን ሁሉ አለን። ፍቅር ከሌለን ግን ምንም የለንም ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ይህንን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል

«በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።» 1.ቆሮ.13፡1-3

ይህ ቃል እጅግ የሚገርም ነው። ሰው ፍቅር ሳይኖረው በመላእክት ልሳን ሊናገር ትንቢት ሊናገር እውቀትን ሁሉ ሊያውቅ ተራሮችን እስኪያፈልስ ድረስ እምነት ሊኖረው ድሆችን ሊመግብ ያለውን ሁሉ ሊያካፍል ስጋውን ለእሳት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል እያለን ነው። ይህ ለሰው አእምሮ የሚከብድና የማይመስል ነገር ነው። ሰው እንዴት ፍቅር ሳይኖረው ይህንን ሁሉ ሊሆንና ሊያደርግ ይችላል? አዎ ሰው በተሳሳተ የሃይማኖት አስተምህሮ ተሞልቶ ለመጽደቅና በሰማይ ወርቅ ቤት ለማግኘት እነዚህን ሁሉ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ግን ያለ ፍቅር ከንቱ ናቸው አለን እውነቱ የበራለት ሐዋርያ። ስለዚህ እውነተኛው ወንጌል ሲበራልን ሁሉንም ነገር የምንመዝነው በፍቅር ነው። የምናደርገው ነገር ሁሉ በፍቅር ማሽን እየተፈተሸ ሊያልፍ ይገባል። በፍቅር ውስጥ ተፈትሾ ካላለፈ ከንቱ ነው። የምትችሉትን ነገር ሁሉ ቁጠሩ መንፈሳዊ ሥራና ስም ሁሉ ደርድሩ ያለ ፍቅር ከንቱ ነው። እኛ ግን ተስፋ የማንቆርጥ ሞኞች ይህንን ምክር ችላ ብለን ፍቅር ሳይኖረን ብዙ ነገሮችን እናከማቻለን። አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተማርኩትና ከሌሎች አገሮች ለየት ያለ ነገር ትዝ ይለኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁልጊዜ ምን ያህል ኪሎ ይዘን መግባት እንደሚፈቀድልን ይነግረናል። አብዛኛው ሰው ግን ይህን እያወቀ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ትርፍ ኪሎ ይዞ ይመጣል። ስለዚህ በአየር ጣቢያው እቃ መመዘኛ አካባቢ ብዙ እቃ ተርፎ ሲፈስና ሲመለስ እናያለን። የተነገረንን ልብ ብለን ለክተን ስለማንሄድ እዚያ ስንጨናነቅና ሰራተኞችንም ስንለምን ይታያል። በሌሎች አገር ዜጎች የኛን ያህል እንደዚህ የበዛ ትርፍ እቃ አላየሁም። እንደዚሁም ቅዱሱ ወንጌል ፍቅር ከሌላችሁ ማለፍ አትችሉም እያለን እኛ ግን ፍቅር ባይኖረኝም ፍቅርን የሚያካክሱ ብዙ ነገሮች አሉኝ ብለን ለማለፍ እንሞክራለን። እውነት ልንገራችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍቅርን የሚያካክስ ምንም ነገር የለም። የቱንም ያህል  መንፈሳዊነት ቁጠሩ ሃምሳና ስድሳ ዓመትም በገዳም ኑሩ ፍቅር ከሌለ ከንቱ ነው። ሐዋርያው ለዚህ ነው ጠንከር ባለ ቃል ስጋየን ለመቃጠል አሳልፌ ብሰጥ እንኳ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ የሚለን። በመሆኑም ከእግዚብሔር ጋር ህብረት እንዳለን ምልክቱ እግዚአብሔርን እንደምንወድ ምልክቱ ወንድሞቻችንን መውደዳችን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ከጳውሎስ ጋር በመስማማት «ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።» 1.ዮሐ.4፡20-21

ሐዋርያው እዚህ ጋር ያስቀመጠው የብዙዎቻችን ስንፍናና ባህርይ ነው። የምናየውን ወንድማችንን ሳንወድ የማናየውን እግዚአብሔርን የምንወድ ይመስለናል። እንደምንወደውም እንናገራለን። ሐዋርያው ግን ቁርጡን ነገረን። የማናየውን እግዚአብሔርን መውደዳችን ምንም ማስረጃ የለውም። የምናየውን ወንድማቸንን መውደዳችን ግን የማናየውን እግዚአብሔርን ለመውደዳችን ማስረጃ ነው።  ስለዚህ እኔም ልጨምርላችሁ። ወንድሞቻችሁን ሳትወዱ መላእክትን ጻድቃንን እንወዳለን እያላችሁ የምትናገሩ እንዲያውም በነርሱ ስም እያመካኛችሁ ወንድሞቻችሁን የምታሳድዱ እውነቱን ስሙኝ። የምታዩትን ወንድማችሁን ካልወደዳችሁ ያላያችኋቸውን ቅዱስ ገብርኤልን ቅዱስ ሚካኤልን…አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አቡነ አረጋዊን.. እንዴት ልትወዱ ትችላላችሁ? በማይታየው እግዚአብሔር ተሸፍነን እንዴት የሚታዩትን ወንድሞቻችንን እንጠላለን? በመሆኑም ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ወንጌሉን የዘመረ ሰው ነው ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። ድሀ ከሆንኩ አካላዊ ጤንነት ካጣሁ አንድ ነገር ከጎደለኝ ሳይሆን ያለው «ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ፣» ነው ያለው። ይገርማል ድምጻዊው በተጠቀመበት መለኪያ መለካት ከጀመርን አቤት ስንት በሽተኛ እናገኝ ይሆን? ለካ እውነተኞቹ በሽተኞች በየጠበሉና በየሆስፒታሉ የተኙት አይደሉም። ለካ በከባድ በሽታ የተጠቁት በየመንገዱ በየፓርላማው በየቤተ ክርስቲያኑ ያሉ እርስ በርሳቸው ሲናከሱ ጥላቻን ሲሰብኩ የሚውሉት ናቸው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ሰው በተለያየ ቦታ እየሸነሸኑና ያለ መልኩ መልክ እየሰጡ ስንቱን ጎዱ። እኔም እግዚአብሔር እስኪያበራልኝ ድረስ  ለጥቂት ጊዜ የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደነበርኩ አልረሳውም። የተወለድኩበት ብሄር ከሌላው የተለየ ታማኝ ሐቀኛ እንደሆነ እየተነገረኝ ስላደግሁ ብዙ ዓይነት የሰው ዘር ያለ ይመስለኝ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገረው ግን የሰው ዘር አንድ ነው። ሁሉም ሰው የተወለደው ከአንዱ አዳም ነው። ስለዚህ ሁላችንም የሥጋ ወንድሞች ነን። ወንጌሉ ሁለት አዳሞች እንዳሉና የፊተኛው አዳምና የኋለኛው አዳም እንደሚባሉ ይነግረናል። (ሮሜ.5፡12-14 1.ቆሮ.15፡45) ሁሉም ሰው ከፊተኛው ሰው አዳም ኃጢአትን ወርሶ የተወለደ ሲሆን በወንጌሉ የሚያምኑት ደግሞ የኋለኛው አዳም ከተባለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በመወለዳቸው በመንፈስ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ። እንግዲህ ሰው ከነዚህ ሁለት ጎራዎች ውጭ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም በፊተኛው ዘር ስንቆጥር አንድ ትግሬ ከአንድ ትግሬ ጋር ያለው ቅርበትና አንድ ትግሬ ከአንድ ኦሮሞ ጋር ያለው ቅርበት አንድ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም የአዳም ልጆች ናቸውና። ስለዚህ ትግሬ እንደዚህ ነው አማራ እንደዚህ ነው ጉራጌ እንደዚህ ነው እየተባለ ብዙ የተለያየ የሰው ዘር እንዳለ የሚያስመስለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። እንደዚህ እያሉ በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረውን ሰው በራሳቸው መልክ ቀለም እየቀቡ መለያየትን የሚፈጥሩ ሰዎች የጥላቻ በሽታ ተጠቂዎች ናቸው። ከበሽታው ነጻ ስንሆን ሰውን ሁሉ በአንድ አይን ማየት እንጀምራለን። ችግሩ ግን እንደ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ጥላቻ በሽታ መሆኑን ካላወቅን ለመፈወስ አንሻም። እንዲያውም መለያየትን እንደመልካም ነገር እንደጌጥ አክሊል ራሳችን ላይ እንጭነዋለን። ሌላው አሳሳቢው ነገር ከዚህ በሽታ የሚፈውስ ጠበል አልፈለቀም ሳይሳዊ ህክምናው የለውም። ብቸኛው መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ብቻ  ነው። እርሱ ነው በዘር በቋንቋ እያለያየ የሚያጣላንን አሮጌ ሰዋችንን በመስቀል ላይ ጠርቆ ያስወገደው። ወንጌሉን ስናምን በዚህ መድኃኒት እንፈወሳለን። በዘመኑ በእስራኤላዊነቱ ከብንያም ነገድ በመወለዱ እጅግ ይመካ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ በሽታ በክርስቶስ ከዳነ በኋላ እንዲህ ብሎ ጻፈ « አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።» ገላ.3፡28። ይህ እጅግ የሚያስገርም በዘመኑ ብዙዎችን ያስደነገጠ ቃል ነው። ምክንያቱም አይሁዶች ከኛ ወዲያ ላሳር እኛኮ እግዚአብሔር የመረጠን ህዝብ ነን። አይሁዳዊነት እኮ ቅዱስነት ነው እያሉ ሲመኩ ግሪኮች በጥበብ በኩል ከኛ ወዲያ ላሳር ከምድር አልፈን ምህዋረ አለሙን እየተመራመርን ነው ስለዚህ እኛ ከሌላው ለየት እንላለን ሲሉ ባሮችን የሚገዙ ጌቶች ባሪያዎቻቸውን እንደሰው ሳይሆን እንደ ንብረት በሚቆጥሩበት ጊዜ እንደዚህ ብሎ መጻፍ ታላቅ ብርሃንን ይጠይቃል። ሐዋርያው ግን እግዚአብሔር በብርሃን ተገልጦ ይመካበት ከነበረው ምድራዊ ነገር አድኖታልና ከዚህ ነጻ ወጥቶአል። ስለዚህ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ ይላቸዋል። አዎ ግሪካዊውን ከጥበብ ትምክህት አይሁዳዊውን ከሃይማኖት ትምክህት ነጻ አውጥቶ አንድ ሰው የሚያደርግ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። አንድ የምንሆንበትን ፍቅር የሰጠንም የሚሰጠንም እርሱ ነው። ሰባኪ ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን እውነት ነው ያዜመልን። ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ። አዎ ለራሳችን እውነተኞች ከሆንን እና እውነቱን በድፍረት ከተናገርን ዛሬ የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ችግር የፍቅር ማጣት ነው። ማህበረ ሰብ ሲዋደድ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሲሆን ሲከባበር አገር ሰላም ይሆናል። ፍቅር ሲኖረን ሁሉ እንደሚኖረን ሁሉ ፍቅር ከሌለን ደግሞ ሁሉ የለንም። ስለዚህ ፍቅር ለአገርም ለህዝብም ለመንግስትም ጤንነት ነው።

ሌላው መጋቤ ሐዲስ ቴዎድሮስ ካሳሁን ያዜመው ዜማ ከዚህም በበለጠ መንገድ የአዲስ ኪዳንን ወንጌል በሚገባ የገለጠ ነው ። ስለዚህ በግሌ እኔ በስልጣኔ መጋቤ ሐዲስ የሚለውን ስም ሰጥቸዋለሁ። ማን ይከለክለኛል? ስንቶቹ ፖለቲካንና መለያየትን እየሰበኩ መጋቤ ሐዲስ ተብለው የለም እንዴ? እውነተኛውን የአዲስ ኪዳን ሚስጢር የሰበከው ቴዎድሮስ ካሳሁንማ መጋቤ ሐዲስ መባል አለበት። እስኪ መጋቤ ሐዲስ ያልኩበትን ዜማ ደግሞ እንመልከተው።

ሁለተኛ

«ሳዋህድ ከኖርኩት ቅኔን ከደብተሬ

ተሽሎኝ ተገኜ ባላገሩ ገብሬ

ለካ ሰው አይድንም በደገመው መፃፍ

እንደ ሰም አቅልጦ ፍቅር ካረገው ጧፍ

ለካ ሰው አይድንም በኦሪት በገድል

 ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካረገ ድል።»

መጋቤ ሐዲስ ቴዎድሮስ ካሳሁን በዚህ ዜማው በፍቅር እስከመቃብር ላይ ስለምናያት ሰብለ ወንጌል ወይም ስለወደዳት የጎጃም ኮረዳ የሚያዜም ቢመስልም አስተውሎ ለሰማው ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እየተናገረ ነው። በተለይ «ለካ ሰው አይድንም በኦሪት በገድል ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካረገ ድል።» የሚለው ስንኝ አጠቃላይ የአዲስ ኪዳንን ሐሳብ በአንድ ስንኝ ቋጥሮ ያስቀመጠ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር ሰው ኃጢአተኛ በመሆኑ ህግን በመፈጸም ሊጸድቅ አለመቻሉንና እግዚአብሔር ግን የሚወደውን አንድ ልጁን ልኮ በፍቅር እንዳዳነው ይተርክልናል።  በሮሜ መልእክቱ ምእራፍ ሶስት ላይ ስለሰው ልጆች ኃጢአትና በደል ብዛት ከዘረዘረ በኋላ በዚህ ምክንያት ዓለሙ ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች መዘጋቱን እና ሥጋን የለበሰ ሁሉ ህጉን በመፈጸም ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ እንደማይችል ያረዳንና ከዚያም የምስራቹን ደግሞ ያበስረናል። እናንብበው።

ሮሜ.3

19 አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤

20 ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።

21 አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥

22 እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤

23 ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤

24 በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።

25 እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥

እንግዲህ መጋቤ ሐዲስ ቴዎድሮስ ጥላሁን ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመስማማት ነው «ለካ ሰው አይድንም በኦሪት በገድል ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካረገ ድል» ብሎ የሰበከን።

እግዚአብሔር እንደ እርሱ ይህንን እውነተኛ ወንጌል የሚሰብኩ ሰባክያንን በቤተ ክርስቲያናችን ያብዛ። ዛሬ የጠፋው እኮ ይህ ነው። ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያቱ ሰው የህግን ሥራ በመፈጸም አይድንም በገድላት በሰዎች ሥራ አይድንም ሰው የሚድነው መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው ሥራ በማመን ነው ብለው እያስተማሩን ከኋላ የመጡ ብዙ ሐሳውያን ግን ወንጌሉን ትተው ሰው በኦሪትና በገድል ይድናል እያሉ ማስተማር ጀመሩ። በጽላቱ ላይ የተቀረጹትስ ቢሆኑ ለሙሴ የተሠጡት አስርቱ ቃላት አይደሉምን? ለመሆኑ አስርቱን ትእዛዛተ ኦሪት በጽላት ጽፎ እንዴት የአዲስ ኪዳን ጽላት ይባላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ጽላት አላስቀረጸም እንጂ ቢያስቀርጽ ኖሮ ከላይ ያየናትን ሁሉን ጠቅልላ የያዘችውን ህግ ነበር የሚጽፍበት። እርስዋም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የምትል ናት። ምክንያቱም ይህች አዲስ ትእዛዝ ሁሉን ጠቅልላ ስለያዘች ሌላ መጻፍ አያስፈልግም። ህግ ሁሉ በዚህች ትእዛዝ በዚህች ቃል ተሰቅለዋል። ዛሬ ዛሬ የሚሰማው ግን ወንጌሉ ተሸፍኖ ኦሪትና ገድል እየተሰበከ ነው። ቀሳውስቱና ጳጳሳቱ በየጊዜው እየተጻፈ ወንጌሉን የሸፈነውን ነገር እንዳይነኩ ህዝቡን ስለሚፈሩ ያልተናገሩትን መጋቤ ሐዲስ ቴዎድሮስ ካሳሁን ግን በድፍረት ተናገረ። ሰው በኦሪትና በገድል አይድንም ፍቅር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ይዞ መጥቶ ድል አድርጎአል እያለ በቅኔ እየነገረን ነው። አሜን ብያለሁ መጋቤ ሐዲስ። ይህንን የእውነት ወንጌል በግልጽ እየተናገርክ ግን ተሐድሶ ብለው አለማውገዛቸው ገርሞኛል። ምክንያቱም እንዲዚህ ብለው የሚያስተምሩትን ጥቂት የወንጌል ሰባኪያን ተሐድሶ ብለው ሲያወግዙአቸው ሳትሰማ የቀረህ አይመስለኝም። የተወገዙት ሰባኪያን አንተ ያልከውን ነው የተናገሩት። ሰው በወንጌል እንጂ በገድልና በኦሪት አይድንም ነው ያሉት። ለዚህ ነው እነርሱን ሲያወግዙ አንተን እንዴት ማሩህ?  ብየ የጠየቅኩት። ምናልባት ጳጳሳቱ ዘፈን ስለማይሰሙ አልሰሙህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ብዙ ህዝብ ስለሚወድህ ፈርተውም ሊሆን ይችላል። እነርሱ እኮ ጥበበኞች ናቸው። የሆነ ሆኖ እነርሱ ባይሰሙህም የሰበከውንም ባይቀበሉ የኢትዮጵያ ህዝብ እየሰማ ስለሆነ ደስ ብሎኛል። ህዝቡም ወንጌል ያልሆነ መዝሙር ከሚሰማ ኦሪትና ገድል ያድናል የሚል ዝማሬ ከሚሰማ ሰው የሚድንበትን ትክክለኛ ወንጌል በዘፈንም ቢሆን ቢሰማ ጥሩ ነው ባይ ነኝ።

እውነት ለመናገር ወንጌልን የሚክድ መዝሙር ከመዘመር ወንጌልን የሚገልጥ ዘፈን ሳይሻል ይቀራል ትላላችሁ? ለዚህ እኮ ነው ዘፋኝ ተብሎ የሚታወቀውን ቴዎድሮስ ካሳሁንን መጋቤ ሐዲስ ያልኩት። ይቀበለኝ አይቀበለኝ አላውቅም እኔ ግን አልሽረውም እውነተኛውን አዲስ ኪዳን እውነተኛውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በዘፈን አስመስለህ ሰብከሃልና ከዚህ በኋላ መጋቤ ሐዲስ ብየሃለሁ። አደራ እንደ ገላትያ መምህራን ተመልሰህ ወደ ኦሪትና ወደ ገድል እንዳትመለስ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሰበከውን ወንጌል ብቻ በመስበክ ቀጥል። ዘፈኖችህን መስማት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ስለፍቅርና ስለአንድነት እንጂ ስለጥላቻና መለያየት ስታዜም ስላልሰማሁ መጋቤ ሐዲስ ልትባል ይገባሃል ብያለሁ። በቤተ እግዚአብሔርና በጳጳሳቱና በቀሳውስቱ መካከል እንኳ የፍቅር ድርቅ በተከሰተበት ሰዓት አንተ ፍቅርን መስበክህ የአዲስ ኪዳን ትእዛዝ አንዲት ብቻ እርስዋም ፍቅር መሆንዋን ስለተረዳህ ይመስለኛል። ዜማህም በዘፈን ለሚጽናኑ ለዓለማውያን ሳይሆን ፍቅርን ለተጠሙ ሁሉ የሚያገለግል መካሪ ዜማ ነው። እግዚአብሔር በመጋቤ ሐዲስነትህ እንድትቀጥል ይርዳህ።

*  አንባቢዎቼ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን ጽሑፍ አላየውምም አልተስማማበትም። ሙሉ በሙሉ የጸሐፊው ምልክታ መሆኑን እወቁልኝ።

%d bloggers like this: