ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን መልቀቅ እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን መልቀቅ እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ዛሬ ማታ ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር አስታወቁ። ኢትዮጵያ እንደገና በለውጥ ሂደት ያለች ይመስላል። እኔን የሚገርመኝ ግን ስንለውጥ ወደ ባሰ ሳይሆን ወደ ተሻለ የምንለውጠው መቼ ይሆን? ያ እንደዛሬው በስሜት ተነሳስቶ ንጉሡን ከስልጣን አውርዶ የገደለው የስድሳዎቹ ለውጥ ከንጉሡ የተሻለ መልካም ነገር አመጣን? ከዚያ በኋላ ይከው እስከ ዛሬ ድረስ ለአርባ ዓመት የማያቋርጥ እልቂትና እርስ በርስ መጠላላቱ ቀጥሎአል፡ አሁን ደግሞ ያለውን መንግስት አልፈልግም አሻፈረኝ እያለ ያለው ህዝብ ምን እንደሚፈልግ እንጃ? ምክንያቱም የሚታየው ነገር ንጹህ የሆነው ለውጥን የመፈለግ ነገር ሳይሆን ከጀርባው ብዙ ክፉ ነገር ያለበትና በብዙ ምክንያት ተጎዳን የሚሉ ወገኖች ሌላ በቀል የሚሰብኩበት ነገር ስለሆነ ነው። ለውጡ ወደ ተሻለ ቢሆን እጅግ መልካም ነው። ወደ ባሰ ከሆነ ግን ያሳዝናል። ይህንንም ማድረግ የሚችለው ህዝቡ ይመስለኛል። ዓላማ እንደሌላው ለውጥ ፈላጊዎች የህዝቡ ሐሳብ አጭርና ያለው መንግሥት ስልጣን እንዲለቅ ብቻ መጠየቅ መሆን የለበትም። ስልጣኑን እንፈልጋለን ብለው ከጀርባ የህዝቡን ብሶት ተንተርሰው እየመጡ ያሉትን አንዳንድ ሰዎች ሊገታቸውና የሚፈልገውን መልካም አስተዳደር ራሱ ሊያመጣ ይገባዋል። አለዚያ አሁንም ህዝቡ የተሳፈረበትን የለውጥ ምኞት አውሮፕላን ጠልፈው ህዝቡ ባልፈለገውና ባላሰበው ምድረ በዳ የሚያሳርፉ ጎበዝ ጠላፊዎች የበዙበት ዘመን ነው። በውኑ ንጉሡ ሲወርዱ ደርግ የሚባል ሥርዓት እንደሚመጣ ያ ሁሉ ወጣት እንደሚያልቅ ህዝቡ አውቆ ነበርን? በጭራሽ። ህዝቡ የፈለገው ልማትን ነጻነትን መሬትን እንጂ ሌላ አልነበረም። ነገር ግን በህዝቡ ጥያቄ ሰረገላ ላይ ተሳፍረው ሰረገላውን ወደሌላ አቅጣጫ የሚዘውሩ ሰዎች ተነሱና ሁሉም አቅጣጫውን ሳተ። አሁንም ህዝቡ ምክንያታዊ ቢሆን እንዲሁ በጭፍን ያለውን መንግሥት መቃወም ሳይሆን መስተካከል የሚገባውን እያሰተካከለ ቢሄድ መልካም ይሆንለታል እላለሁ።

ለማንኛውም መልካም ዜና።

%d bloggers like this: