ወደ መሠረታችን እንመለስ

አራቱን የሂሳብ ህገጋት ሳናውቅ ወይን አልፈን የትም መሄድ አንችልም። አራቱ የሂሳብ ህገጋት የስልጣኔ ሀሁ ናቸው። ይህ የሚታየው ስልጣኔ ሁሉ የተነሳውና የተመሰረተው በነዚህ ቀላል በሚመስሉ የሂሳብ ህገጋት ነው። ሰው ወደ ጨረቃ የወጣው ከነዚህ ተነስቶ ነው። እርግጥ ነው ማቲማቲክሱ እየተወሳሰበ እየመሰጠረ ይሄዳል  ቢሆንም በሩ ይህ ነው። በዚህ በር ያልገባ የትም አይደርስም። ጋን በጠጠር ይቆማል እንደሚባለው ትልቁ የስልጣኔ ስርአት የተጀመረውና የቆመው በነዚህ መሰረታዊ ህገጋት ነው። እነዚህን ህገጋት ሳያውቅ ማለትም 1+1 2÷2 4-2 1/1 ምን እንደሆነ የማያውቅ ሰው ስለሌሎች የጠለቁ የሂሳብ ስርአቶች ሊናገር ቢሞክር ማን ይሰማዋል? ልናገርበት የፈለግሁት ዋና ጉዳይስ የሂሳብ ወይም የስልጣኔ ጉዳይ ሳይሆን ሰሞኑን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው አስፈሪ ችግርና መፍትሄ ሰጪ ነን የሚሉ ወገኖች የሚናገሩት ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ የዜግነት ግዴታየን ልወጣ ብየ  ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ አነሰም በዛ በመልካም ጉርብትና የሚታወቅና ሃይማኖት ዘርና ቋንቋ ሳይለየው ተጎራብቶ የኖረ ህዝብ ነው ወይም ነበር። ይህ ህዝብ እንደዚህ ሆኖ የኖረው በፖለቲከኞች ቀመር ሳይሆን በተፈጥሮ ያገኘውን የሰውነትና የህሊና ጸጋ እንደሚገባ በመጠቀም ከጎረቤቱ ጋር አብሮ ተሳስቦና ተዛዝኖ መኖርን ስለለመደ ነው።  እነዚህ ህዝቡ ተባብሮ የኖረባቸው የተፈጥሮ ቅመሞች መሰታዊ የሂሳብ ህጎች ናቸው። ችግር በሚፈጠርበትም ጊዜ  እነዚህን ህጎች ሽረን ሳይሆን በነዚህ ህጎች ተመርተንና ተመስርተን ችግሩን ልንፈታ እንሞክራለን። አሁን የማየውና የምሰማው ነገር ግን እነዚህ የህብረተሰብ ህጎች እየተሸረሸሩና እየጠፉ ያለ ይመስላል። ችግር በየትም አገር አለ። በማንኛውም የአለም ክፍል እንደምናየው በየጊዜው ችግር ይፈጠራል። ችግሮቹ ግን ሁሉም ማለት ይቻላል ሰው ሰራሽ ወይም ሰው ራሱ የፈጠራቸው ናቸው። ችግር ፈቺዎች እንዳሉ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎቹም ብዙዎች ናቸው። እንዲያውም ከመቶ ዘጠናው ፐርሰንት ያህል ችግር ፈጣሪ ስለሆነ የችግር ፈቺዎቹ አናሳነት ችግሩ በዚህች ምድር ላይ እንደሰደድ እሳት እንዲቀጣጠል አድርጎታል። ብዙውን ጊዜ ችግሩን እንፈታለን ብለው የሚነሱት የተማርን ነን ለህብረተሰቡ እኛ እናውቅለታለን የሚሉት ናቸው። እነዚህ ወገኖች ግን ብዙውን ጊዜ በዚህ እውቀታቸው መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን ሲያባብሱ እናያለን። ለምን?ምክንያቱም። የሰውን መሰረታዊ የህይወት ስርአት በማፍረስ ስለሚጀምሩ ነው። እነዚህ ህብረተሰብ ከህብረተሰብ ጋር አበሮ የሚኖርባቸው ስርዓቶች በተፈጥሮ ለሰው ልጅ የተሰጡ ስርአቶች ቢሆኑም ክፉ በሆነ የፖለቲከኞች ስብከትና ፕርፓጋንዳ ከሰው ህሊና ሊታጠቡና የሰው ህሊና መላጣ ሆኖ ሊቀር ይችላል። ብዙዎቹ ችግር ፈቺ ነን የሚሉት ፖለቲከኞች በክፉ የፖለቲካ ጸሐይ ህሊናቸው የተመለጠና እነዚህን መሰረታዊ የህብረተሰብ ስርአቶችን የማያውቁ ናቸው። በአራቱ የሂሳብ ህገጋት የመሰልኩት መሰረታዊውና መጀመሪያው ስርአት አንድ ህብረተሰብ ከሌላው ህብረተሰብ ጋር ለመኖር አንድም ግለሰብ ከሌላው ግለሰብ ጋር ለመኖር ሁልጊዜ መጠበቅ ያለበት ስርአት ነው። ይኸውም ሰውን በሰውነቱ ማየት ተቻችሎ መኖር ወዘተ ናቸው። እነዚህ የህሊና መላጣ የሆኑ ሰዎች በጣም መሰረታዊና ህብረተሰቡ የተሳሰረበትን ድር በመበጠስ ስለሚጀምሩ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ አንዱን ህብረተሰብ ከሌላው ጋር እንዲጣላ በማነሳሳት ያባብሱታል። ህብረተሰቡ እርሱ ያለው ያልተመለጠ ህሊና እነርሱ ይዘናል ከሚሉት ዶክትሬትና ፒችዲ እንደሚበልጥ ስለማያውቅ የተማረ ይግደለኝ ብሎ ወደሞት ይነዳል።  እኔስ የተማረ ከሚገድለኝ ያልተማረ በህይወት ቢያኖረኝ ይሻለኛል። እነዚህ ፖለቲከኞች ህሊናቸው ብቻ ሳይሆን የተመለጠው ህሊናቸው ላይ የወረደው የጥላቻ ጸሐይ አንደበታቸውም ላይ ደርሶ ምላሳቸውም የተመለጠ ነው። የሚናገሩት ነገር እጅግ ያስፈራል። ውስጣቸው ህብረተሰብ በሌላው ህብረተሰብ ላይ ተነስቶ ተፋጅቶ እነርሱ በአቋራጭ ስልጣን ላይ መውጣት ስለሚፈልጉ አንድ ጭስ ሲወጣ ሲያዩ እንዳይቃጠል ከመረባረብ ይልቅ ይህች ጭስ ተቀጣጥላ አገሩን ሁሉ እንምታቃጥል ይተነብያሉ ይመኛሉ። የብሄርን የቋንቋን ስም እየጠቀሱ ያ ብሄርና ያ ቋንቋ የኢትዮጵያ ችግር እንደሆነና ቢጠፋ ሁሉም መልካም እንሚሆን ይናገራሉ። ይህ በጣም ሰይጣናዊና ሊወገዝ የሚገባ ነገር ነው። አንድ ሰው ወይም የተወሰኑ ሰዎች ጥፋት ካጠፉ እነርሱ ላጠፉት ጥፋት በህግ ይቀጣሉ እንጂ የተወለዱበት ብሄርና ህዝብ ላይ ጥፋት ማወጅ ከባድ ወንጀል ነው። በአሁኑ ወቅት ይህንን የጥፋት አታሞ የሚመቱ ሰዎች በእጅጉ እየተጠመዱ ነው። የግለሰቦችን ዘርና ብሄር እየጠቀሱ ጥፋትን ማወጅ፡ የአንድን ብሄር ጥፋት መመኘት እነዚህ የጥላቻ ወንጀሎች ናቸው። ዲሞክራሲ ለጥላቻ ወንጀል ስፍራ የለውም። ዲሞክራሲ ማለት ጥላቻን መስበክ አይደለም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግረ ለመፍታትና ህዝቡን ያማረረውን የመልካም አስተዳደር እጦት ለማስተካከል መታገል ያስፈልጋል። ይህንን ለማስተካከል አብዛኛው ህዝብ ይፈልጋል። ይህ ግን አንገብጋቢ ችግር አይደለም። መቸም ይህንን ስል ብዙዎቻችሁ እንዴት አንገብጋቢ ችግር አይደለም ትላለህ? ብላችሁ ሳትደነቁ አትቀሩም። ለምን ይህን እንዳልኩ ልናገር። አንድን ችግር አንገብጋቢ የሚያደርገው አደገኛነቱና የሚያደርሰው ጥፋት መጠን ነው። ከዚህ አንጻር ስናየው አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጉቦኝነትና የመልካም አስተዳደር እጦት የከፋና ከዚያ የበለጠ ጥፋት የሚያደርስ አንገብጋቢ ችግር አለ። ይኸም የዘር ጥላቻ ወይም በዚህ በምዕራቡ አለም እንሚሉት Hate Crime ነው። የሚገርመው ይህ የዘር ጥላቻ የተፋፋመውና የነደደው አሁን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ እንታገላለን ብለው በተነሱት ሰዎች ውስጥ ተሸሸጎ መሆኑ ነው። አዎ ህዝቡ የዘር ጥላቻንና መለያየትን ለማምጣት ሳይሆን መብቱ እንዲከበርለት መልካም አስተዳደር እንዲኖር ፈልጎ ነው የተነሳው። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ግን ይህንን ነፋስ ተተግነው የዘረኝነትንና የጥላቻን አላማ የሚያራምዱ ፖለቲከኞች ትግሉን በቴክኖሎጂው ነፋስ ተጠቅመው ወደ ራሳቸው አቅጣጫ ጠመዘዙት። ከዚያም የሚጠሉትን ብሄርና ተወላጆቹን ለማጥፋት ለፈፉበት። አገሪቱን ለመጠበቅ ህይወቱን እየሰጠ ያለውንና ህልውናዋን ጠብቆ የሚኖረውን ሰራዊት የአንድ ብሄር ሰራዊት እንደሆነና ኢትዮጵያ ሰራዊት እንደሌላት ሰበኩ። በመሆኑም ህዝቡ ሰራዊቱን ለማጥፋት እንዲነሳ አወጁ። በሰራዊቱ መካከል ያልተመጣጠነ ክፍፍል ካለ እንዲመጣጠን መጠየቅ ወግ ነው። የአገሪቱ ተወላጆች ሁሉ ያሉበትን የጦር ሰራዊት የአገሪቱ ሰራዊት እንዳልሆነ ማወጅ ግን ገደብ የዘለለ ነው። እነዚህ ሰዎች ሰሚ ሲያገኙ ጭራሽ ብሄርን በብሄር ላይ ማነሳሳታቸውን ቀጠሉበት። ይህ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። አሁን ካለው የመልካም አስተዳደር ጉድለት ይልቅም የከፋ ነው። ጥላቻን መስበክና ብሄርን በብሄር ሰውን በሰው ላይ ማነሳሳት  ትልቅ ወንጀልና ጥፋት ነው። አንድ ለኢትዮጵያ እጋደላለሁ የሚልና አሁን ካለው የተሻለ መልካም አስተዳደር እንዲመጣ የሚፈልግ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ የጥላቻ ፖለቲካን በመስበክ አይጀምርም። እኔን በእጅጉ ያሳዘነኝ አሁን ያለውን በሙስናና በተለያየ ችግር የተዘፈቀውን መንግስት የምቀይርበት መልካም ተቃዋሚ ፓርቲ ማጣቴ ነው። ህዝቡ የተሻለ ርዕዮተ አለም ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ ማጣቱ የመልካም አስተዳደር ችግሩን ተሸክሞ እንዲኖር ያደርገዋል። ምክንያቱም ዘረኝትንና መከፋፈልን የሚሰብኩትን እንደ አማራጭ ሊወስዳቸው አይችልምና ነው። በመሆኑም አንገብጋቢው ችግር ይህ የዘር ጥላቻ ነው። ለኢትዮጵያ መልካም ነገር እፈልጋለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከሁሉ አስቀድሞ ማለትም አሁንም ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ ከመታገሉ አስቀድሞ ይህንን ሰው በሰው ላይ ብሄርን በብሄር ላይ በጥላቻ የሚያነሳሳውን የሰይጣን መርዝ መታገልና ማውገዝ አለበት። ይህ በአንድ ድምጽ ሊወገዝ የሚገባው ነገር ነው። ሌላውን ችግር ሁሉ የምንፈታው በሰላም አብረን ስንኖር ብቻ ነው። ስለዚህ አሁን የሚሰማውን ክፉ ነገር ሁሉ በጭራሽ ሊባሉ የማይገባቸውን ቃላት ሁሉ ማውገዝ አለብን። ከዚህ ክፉ ነገር ጋር የተባበረ ሁሉ ግን ችግር ፈቺ ሳይሆን ራሱ ችግር ነው። የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሄው አካል እንሁን።

መልካም ቀን።