Echo የገደል ማሚቶ አዙሪት።

Echo የገደል ማሚቶ አዙሪት።

ገደል ማሚቶ

 THE POLITICS OF REACTION(S)

ሰው የተፈጠረው ማሰብ ማቀድ መስራት የሚችል ፍጡር ሆኖ ነው። ሰው ይህን የተፈጥሮ ችሎታውን በመጠቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ነገሮችን ያስባል ያቅዳል ይፈጥራል። በውስጡ ያለው ይህ ችሎታ በሁለት መንገድ ይጠቀምበታል።

  1. የሚፈልገውን ነገር አቅዶ አስቦ ወደ ውጤት ለማምጣትና እውን ለማድረግ (Pro-action)
  2. ሁለተኛ ደግሞ ለሚገጥሙት ነገሮች ምላሽ ለመስጠት ነው። (Re-actions)

ለምሳሌ አንድ ሰው በሩጫ አሸንፎ አንደኛ ለመውጣትና ለመሸለም ሊሮጥ ይችላል። አለዚያም ደግሞ ከመጣበት አደጋ ለማምለጥ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሊሮጥ ይችላል። የመጀመሪያው አንድ ነገር ለማከናወን አስቦ አቅዶ የሮጠው ሲሆን ሁለተኛው ግን ድንገት የመጣበትን አውሬ ወይም አንድ አደጋ ለማምለጥ ያሳየው ፈጣንና ቅጽበታዊ ምላሽ ነው። ሰው አውቆትም ይሁን ሳያውቅ በነዚህ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ነው ሲመላለስ የሚኖረው። የተሰጠን የተፈጥሮ ችሎታ ሁለቱንም የማድረግ ብቃት ቢኖረውም በዋናነት የሚቀመጠው ግን የመጀመሪያው ነው። የማሰብና የማቀድ ችሎታችን የተሰጠን ከሚመጣብን ነገር ለመዳን ብቻ እንድንጠቀምበት ሳይሆን በዋናነት ህይወትን በእቅድና በዓላማእንድንኖራት ነው። በእቅድና በዓላማስንኖር ጉልበታችንን ሁሉ የምንጠቀመው የሚያስፈልገንንና የምንፈልገውን ለማሳካት በማቀድና በማከናወን ነው። ነገር ግን በጉዞአችን መካከል የሚያጋጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ ደግሞ ለሚገጥመን ነገር መፍትሄ የሆነ ቅጽበታዊ እርምጃ ለመውሰድም እንጠቀምበታለን። ችግሩ የሚመጣው የመልስ እርምጃው ሂደት አስቦ የመራመዱን ሂደት ሲተካውና ሲቆጣጠረው ነው። በዚህ ወቅት ማለትም ለሚገጥመን ችግር የምንሰጠው ቅጽበታዊ እርምጃ ሲበዛና አስቦና አቅዶ መኖርን ሲተካው አስበንና አቅደን ሳይሆን ለሚገጥመን ችግርና መሰናክል ብቻ መልስ እየሰጠን የምንኖር እንሆናለን። በሕይወታችን ሂደት ውስጥ ብዙ ያልጠበቅናቸው ተደጋጋሚ መሰናክሎችና ችግሮች ሲገጥሙን ለነዚህ ችግሮች መልስ በመስጠት ብቻ እንጠመዳለን። እነዚህ ችግሮች ካላቋረጡ ደግሞ ለነርሱ መልስ መስጠትን የመኖራችን ዋና ዓላማአድርገን እንቆጥራለን። ከዚያ በኋላ የምንኖረው ለነዚህ ነገሮች መልስ ለመስጠት ብቻ ይሆንና ዋናውን የተፈጥሮ ችሎታችንን ሳንጠቀምበት እናልፋለን። የተመኘነውንና የሚያስፈልገንን አስበንና አቅደን በመስራት ምትክ ችግሮች ባወጡልን መርኃ ግብር መሠረት ለነርሱ መልስ በመስጠት ተጠምደን የምንፈልገውን ሳናከናውን እናልፋለን። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በተደጋጋሚ ይህንን ባደረግን ቁጥር አስበንና አቅደን በዓላማልንኖርበት የምንችል ችሎታ በውስጣችን እንዳለ እንረሳና ምላሻዊ ህይወትን እንደዋና የህይወት ዘየ ተቀብለን ለመኖር መገደዳችን ነው። በችግር ላይ ችግር እየተደራረበ ለአንዱ ችግር መልስ ሰጥተን ሳንጨርስ ሌላ ችግር እየመጣ ህይወታችን በመልስ ምት ስለሚጠመድ ይህ ደለል ዋናውን አስቦና አቅዶ የመኖር ችሎታችንን ይቀብረዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ መልክ በዚህ መነጽር ልናየው የምንችል ይመስለኛል። ያለው ህገ መንግስት፣ በየእለቱ የሚወጡት ህግና አዋጆች፣ ፖለቲከኞች ለህዝቡ የሚሰብኩት የፖለቲካ አይነት ሁሉ በሰከነ ልቡና በእቅዳና በዓላማይህ ለሁላችንም ይጠቅማል ተብሎ የተረቀቀ ኦሪጂናል ነገር ሳይሆን ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ችግሮች የተሰጠና የሚሰጥ የመልስ ምት ነው። ችግሮቹ ከዘመኑ ጋር እንዲያልፉ አልፈቀድንም። ከመቶ ዓመት በፊት በደል የደረሰባቸው ሰዎች ለዚያ በደል መልስ ለመስጠት ነው የሚኖሩት። አመታቱ ቢያልፉም ችግሩ ግን ከአመታቱ ጋር እንዲያልፍ አልተፈቀደለትም። ችግሩ አመታቱን እየተሻገረ እንዲመጣና እኛም ለዚያ ችግር መልስ በመስጠት ብቻ እንድንኖር ነው የመረጥነው። ችግሮቹን ከፈጠሩአቸው ሰዎች ይልቅ ችግሮቹ ዘመናት ተሻግረው እንዲኖሩና ችግር ፈጣሪዎቹ ሲሞቱ ችግሮቹ ግን እንዳይሞቱ የሚያደርገው ትውልድ የከፋ ነው። አንድ ነገር እንዴት ከፈጣሪው የበለጠ ዘመን እንዲኖር ይፈቀድለታል? በእርግጥ ችግሩን የማንፈልግ ሰዎች ብንሆን ኖሮ እንቀብረው ነበር። በቆየ  ቁጥር ግን እየገማ ሰውን ያሳምማል። ችግሩቹን እንዲቀጥሉ በፈቀድን ቁጥር የኛን ኦሪጂናል ነገር መፍጠር የማንችል ተፈጠረ ላልነው ችግር መልስ ለመስጠት ብቻ የምንኖር ለራሳችን ሳይሆን ለችግሮቹ የምንኖርላቸው እንሆናለን። የገደል ማሚቶ ሕይወትም ይህ ነው። ገደል ማሚቶ ከዚያኛው ከአንድ ሰው ወይም ከአንድ ነገር ለወጣ ድምጽ በሌላኛው ወገን ካለው ተራራ አስተብቶና ነጥሮ የሚሰማ ድምጽ ነው። ድምጹ መጀመሪያ የወጣው ከአንድ ሰው ወይም ነገር ሲሆን በድጋሚ ያስተጋባው ግን የዚሁ ድምጽ ነጥሮ መመለስ እንጂ ሌላ ከሌላኛው ወገን የመጣ አዲስ ድምጽ አይደለም። ስለዚህ ድምጹ የአንድ ወገን እንጂ የሁለት ወገን አይደለም አንድ እንጂ ሁለትም አይደለም። ገደል ማሚቶውን መልሶ ያሰማው ተራራ የራሱ ድምጽ የለውም ከዚያኛው ወገን የሰማውን ብቻ መልሶ ያሰማል። ይህ ትውልድ ይህን ይመስላል። የራሱ ድምጽ የለውም። አስቦና አመዛዝኖ የሚያመነጨው ነገር አይታይም። እንዲሁ ብቻ ከርሱ ከረጅም አመታት በፊት የነበሩት መሪዎች ያሰሙትን ድምጽ ብቻ መልሶ ያስተጋባል። የሚያሳዝነው መርጦ ማስተጋባቱ ነው። የሰሩት መልካም ነገር ብዙም ሲስተጋባ አይሰማም። የሰሩት ስህተት ግን በብዙ እየተባዛ ይሰማል። ላለፈው የሚኖር ለአሁን የማይኖር ትውልድ ተፈጥሮአል። ከመቶ ዓመት በፊት የተቀበረ ነገር እየቆፈረ ያወጣል። ላለፈው ምእተ ዓመት ስለሚኖር ያለበት ምእተ ዓመት ምንም ውጤት የሌለው ሰው የማይኖርበት ጫካ ይሆናል። ሰዎች የማይኖሩባቸውን ብዙ አዲስ አመታትን በየመስከረሙ ተቀብለን እንሸኛለን። በአዲስ ዓመት አሮጌ ሰው አይኖርምና እኛ እየቀረን እነርሱን እናሳልፋለን። አሮጌውና ያለፈው ዓመት ያስታቀፈንን ስላልጣልን አዲሱ ዓመት ለኛ የሰነቀውን መቀበያ ክንድ አጣን።

ፖለቲከኛው ሁሉ ሲናገር ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የነበሩ መሪዎች ያደረጉትን ከመናገር ይጀምራል። አእምሮው በዚያ ስለተሞላ ንጹህ ተፈጥሮውን የራሱ  የሆነውን ማየት አይችልም። ከራሱ አእምሮ ያሰበውን ያቀደውን ያለመውን መልካም የሆነውን መናገር አይችልም። ያለፉት መሪዎች የሰሩትን ስህተት ይናገርና ከዚያ የርሱን የመልስ ምት ይሰነዝራል። ከራሱ በወጣ እቅድና ዓላማአሁን ያለውን ዘመን የሚጠቅም ነገር ማፍለቅ ያቅተዋል። ይህ ሰው ድሮ ስህተት የሰሩ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ወዮለት። ከምን ተነስቶ ያስባል ለምንስ ይኖራል? የሚራመደውና የሚኖረው ሰዎች ለሰሩት ነገር ምላሽ ለመስጠት ነውና ከርሱ በፊት አንድ ነገር የሰራ ከሌለ ግዑዝ ሆኖ መኖሩ ነው። ይህ ትውልድ ይህን አይመስልም ካላችሁ ከዚህ ትውልድ አንዱ ናችሁ ማለት ነው። በንጹህ አይን ስናየው ግን የሚሰማው የሚታየው ሁሉ የመልስ ምት ነው። ከራሱ የሆነ የራሱ  የሆነ ለአሁኑ አሁን ለሚኖርበት ዘመን የሚጠቅም ነገር ማፍለቅ አቅቶታል። የማሰብ የማቀድ ችሎታው በትናንትና ችግሮች ደለል ተውጦበታል።

ይህ ያመጣው ችግር

ያለፉት መሪዎችም ሆነ ህዝቦች የተሳሳቱት ነገር አለ እንበል። ለመሆኑ ተሳስተዋል ወይ? ምን ያህል ተሳሳቱ? የሚለውን አከራካሪ ስለሆነ እንተወውና የተወሰነ ስህተት ነበረባቸው ብለን እንለፍ። የአሁኑ ትውልድ ያንን ስህተት ለማረም ብቻ ከሆነ የቆመው የራሱ የሆነ እቅድና ዓላማ የሌለው ቆም ብሎ ተመካክሮ ለራሱ የሚበጀውን የማያመነጭ ትውልድ ነው። የሚከራከረውም ራሱ ባወጣው ነገር ሳይሆን ከዚያ ስህተት ተነስቶ ነው። ድሮ ተሰራ ለተባለው ስህተት መልስ ለመስጠት የሚያመጣው መፍትሄም የመልስ ምት እንጂ መፍትሄ አይደለምና እውነተኛውን መፍትሄ እንዳያይ አይኑን ይጋርደዋል። እውነተኛውን መፍትሄ ለማየት ችግር ከመፈጠሩ በፊት ያለውን ኦሪጂናል ነገር ማየት አለብን። የዘረኝነትን የመከፋፈልን መፍትሄ ለማግኘት መከፋፈል ወደ ጀመሩት ሰዎች መሄድ የለብንም። ወደነርሱ ከሄድን በመከፋፈሉ ሳይሆን የምንለያየው በአከፋፈላቸው ነውና አከፋፈሉን ለማረም ብቻ ነው የምንነሳው። እነርሱ አከፋፈሉ በመሳፍንት በመኳንንንቱ በላይኛውና በታችኛው መደብ እንዲሆን አርገው ነበር እኛ ግን በሌላ መልክ እናድርገው ብለን እንነሳለን። ተመልከቱ በችግሩ መሰረት ተስማምተናል መሠረቱንም እንደ ጥሩ ነገር ተቀብለናል። ሰው በሆነ ነገር መለያየት አለበት ብለን ግን እንዴት እንደሚከፋፈል ነው እየተሟገትን ያለነው። ከዚያ አልፈን ወደ ኋላ ብናይ ግን ሰው አንድ እንደሆነ እናያለን ከቅርንጫፎቹ አልፈን ግንዱን እናያለን ሰዎች ከሳሉብን የብዙ ዛፍ (ዘር) እይታ ወጥተን ሰው አንድ ዛፍ እንደሆነ እናያለን። ከዚያ በኋላ ስለዛፉ እንጂ ስለቅርንጫፍ የሚታገል አይኖርም። አለዚያ ግን ችግሩ እየባሰ ይሄዳል። አንድ ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ጥያቄው ትክክል መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉት ነገር ለዚህ በጣም ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል። ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ ብለዋል ልብ በሉ  ችግሩ ያለው መልሱ ላይ ሳይሆን ጥያቄው ላይ እንደሆነ ተረድተዋል። ብዙኃኑ ጥያቄውን እንደ ትክክለኛና ተገቢ ጥያቄ ተቀብሎ በመልሱ ነው እየተጣላ ያለው። እርሳቸው ግን ጥያቄው ራሱ ችግር ነው ወይም ችግር አለበት ነው እያሉ ያሉት። ለዚህ ማብራሪያ ሲሰጡ አንድን ሰው ሚስህትን መምታት ትተሃል ወይ ብሎ መጠየቅ ሰውየውን አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ መውጫ የሌለው ጥያቄ ነው ብለዋል። ምክንያቱም አዎ ካለ በፊት ይመታት እንደነበረ ማመኑ ነው አልተውኩም ካለም እየመታት እንደሆነ ማመኑ ነውና። ስለዚህ ጥያቄው ራሱ ጥፋተኛ ነህ አይደለህምአ? የሚል ሳይሆን ጥፋትህ ምን ያህል ነው በሚለው ላይ ያነጣጠረና ሰውየውን ጥፋተኛ አድርጎ የሚጀምር ነው። ስለዚህ ለምሳሌ ወልቃይት ወይም ሌላ ስፍራ የማን ነው ተብሎ ከመጠየቁ በፊት እኛ ማን ነን? የሚለው በአግባቡ ቢመለስ የመጀመሪያውን ጥያቄ መመለስ ሳይሆን ጥያቄውን ከጥያቄነት ይሽረዋል። ምክንያቱም ከአንድ ዛፍ እንደሆንን ሁላችንም አንድ እንደሆንን እኛ የሁላችንም ሁላችንም የኛ የኛ የሁላችን የሁላችንም የኛ እንደሆነ ካወቅን እኛ አንድ ነንና ያለን ሁሉ አንድ ነው ማለት ነው። ይህ የማን ነው? የሚለው ጥያቄ የሚነሳው አስቀድሞ ሁለትነት ስለተፈጠረና አንዱ ካንዱ ራሱን ለይቶ ስለሚያይ ነው። በአንድ ወቅት ባልና ሚስት ተጣሉና ለመፋታት ወሰኑ። በሽምግልና ለማስታረቅ ብንጥርም አልሆነም። በመጨረሻ ወደ ንብረት ክፍፍሉ ሲገባ ብዙ ክርክር ሆነ። ሁለቱም ይህ ለኔ ይገባል ይህ ለኔ ይገባል ሲሉ ተከራከሩ። ከዚያም በሁለተኛው ቀን እንደምንወስን ቀጠሮ ይዘን ሄድንና በሁለተኛው ቀን ስንመጣ እንዴት እንደሆነ በማናውቀው ሁኔታ ባልና ሚስት ታርቀው ጠበቁን። ይህ ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን ይህ ንብረት ለማን ይሁን የሚለውን ጥያቄ አጠፋው ደመሰሰው። ሁለቱ አንድ ሆነዋልና የማን ነው? የሚለው ጥያቄ በራሱ ጠፋ። ስለዚህ ይህ የማን ነው? ያ የማን ነው የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ሰአት እጅጎ ጎልቶ ይታያል። ይህ በራሱ ችግር ሳይሆን የችግር ምልክት ነው። የመለያየት የመራራቅ ምልክት ነው። ጥያቄውን ሙሉ በሙሉ የሚመልሰው ደግሞ እያከፋፈሉ መኖር ሳይሆን ሁለት የሆኑትን ወገኖች አንድ ማድረግና ያጣላቸውን ነገር ለጋራ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ነው። የማንነት ጥያቄ ካልተመለሰ ግን የማነው? ጥያቄ እየተባዛ እንጂ እየቀነሰ አይመጣም። በመሆኑም ለተሳሳተ ነገር መልስ ለመስጠትና ተሰራ ላልነው ስህተት ብቻ ምላሽ ለመስጠት ከመኖር አሁን ለኛ የሚመቸውን የሚጠቅመውን በማቀድና በመስራት መኖር የተሻለ ነው።

በተለይ የመጀመሪያው ፖለቲከኛ የተሳሳተ ከሆነ ለዚያ የሚሰጠው መልስ ደግሞ የተሳሳተ የተሳሳተ ነው። ማለትም የስህተት ስህተት ነው። ከዚያ በኋላ የሚመጣው ደግሞ የስህተት ስህተት ስህተት እየሆነ ይሄዳል። ስለዚህ ለዚህ ስህተት ምላሽ በመስጠት የሚቀጥለው ሁሉ ስህተትን በሌላ ስህተት እያረመ ይሄዳል። ይህም ከመጀመሪያው የባሰ ተሳሳች ያደርገዋል የሚቀጥለውን  ደግሞ እንዲሁ እየባሰ አንድ የነበረው ገመድ በሶስትና በአራት እየተገመደ ይሄድና የማይበጠስ ይሆናል። እከሌ እከሌን ወለደ የሚለው በታሪክም በቅዱስም መጽሐፍ አለ ሆኖም ግን የሚጀምረው ከአንድ ሰው ነው። እከሌ እከሌን ወለደ የሚለው እየረዘመ ሲሄድ ግን አያታችን ዋናው  መሠረቱ ስሩ እየደበዘዘና እየጠፋ ሄደ። ሰውም ግንዱንና ስሩን ትቶ የተወለደበትን የቅርብ ነገድ እንደ ግንድ ቆጠረ። ከዚያም የሰው ልጅ ከአንድ ዛፍ የወጣ ብዙ ቅርንጫፍ መሆኑ ቀረና እያንዳንዱ ነገድ ራሱን ዛፍ በማድረግ ብዙ ዛፎችን በአእምሮው ፈጠረ። ቀጥሎም አንዱ ዛፍ ወይም ነገድ ሌላኛውን ዛፍ ወይም ነገድ እንደ ሌላ ዛፍ ማየትና ማጥፋት መቁረጥ ፈለገ። ሌላውን ሲጠላ ራሱን ሌላውን ሲገድል ራሱን እየበደለ እንደሆነ ዘነጋ። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የእይታ ችግር እንደሆነ ተመልከቱ። ዛፉ አንድ እንደሆነና ሁላችንም የዚያ አንድ ዛፍ ቅርንጫፎች እንደሆንን ብናስብ ኖሮ ሌላ የምንለው ዛፍ ስለሌለ ለመቁረጥ አንነሳም። ሁላችንም ከአንድ ዛፍ ከአንድ ነገድ ከሰው ነገድ ከአዳም ነንና። ቅርንጫፉ ሁሉ ወንድማችን ዘራችን  ነው። ይህ አስተሳሰብ ከላይ ባየነው ሲወረስ ግን እኛና ሌሎች የሚባል ጎራ ይፈጠራል። አንድ የሚያደርገንን ግንድ ሰውነትን ትተን በጥቃቅን ልዩነቶቻችን ላይ በማተኮር በቋንቋ በቀበሌ እንከፋፈላለን እንተያያለን። በትክክል ካየነው ግን ከአንድ ሰው ጋር ከሚያለያየን ነገር ይልቅ አንድ የሚያደርገን ነገር ይበልጣል። አንደኛ ሁለታችንም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን የምንተነፍስ አእምሮ እውቀት ስሜታችን ፍላጎታችን ተፈጥሮአችን አንድ የሆንን ሰዎች ነን። ያንን ፍላጎት የምንገልጽበት ቋንቋ ተለያየ ማለት ዘራችን ተለያየ ማለት አይደለም። ማንነታችን የተመሰረተው በውስጣዊው ዘራችን እንጂ በውጫዊ ነገር አይደለም። ቋንቋ ከኛ በፊት ከነበሩ ሰዎች የምንለምደው እንጂ ይዘነው የምንወለድ ተፈጥሮ አይደለም። የመናገር የማሰብ ችሎታ ያለን ሁነን ተፈጠርን እንጂ አንድ የተለየ ቋንቋ ውስጣችን ተሰርቶ አልተፈጠርንም። አንድ ነጭ ሰው በኦሮሞ ወላጆች ቢያድግ ኦሮምኛን እንጂ እንግሊዘኛን አይናገርም። በአማርኛ ተናጋሪ ቤተሰቦች መካከል ቢያድግ አማርኛን እንጄ ሌላ አይናገርም። ሰው መሆናችን ግን ተምረን የምናገኘው ሳይሆን በተፈጥሮ ያገኘነው ነው። የማንነታችን መለኪያም ያ ሊሆን ይገባል ። በሰውነት አንድ ነን። ይህ ሲገባን ሰው የሆነ ፍጥረት ሁሉ ወገናችን ነው። እርሱ እኛ ነን እኛም እርሱ ነን። ከዚያ በኋላ የሚመጡ የአስተሳሰብ ልዩነቶች ይህንን መሰረት ሊያፈርሱት አይገባም። ሰዎች ቢከራከሩ ቢስማሙ ባይስማሙ በዚህ መሰረት ላይ ተመስርተው ከሆነ ለመጠፋፋት አይነሳሱም። ምክንያቱም አንዱ የያዘው ሐሳብ ለሌላኛው ባይስማማውም እንኳ ተመካክረው ተደራድረው ይፈቱታል እንጂ ዛፉን ለመቁረጥ ምሳር አያነሱም። ብዙዎቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን መረዳትና አስተሳሰብ ከስሩ ከምንጩ ከሰውነት ስለማይጀምር ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው። እውነተኛ ሰው ማለት የነርሱ ብሄረሰብ እውነተኛ ቋንቋ ማለት የነርሱ ቋንቋ ብቻ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ነው። ይህ አስተሳሰብ ተማርን በሚሉ ፖለቲከኞች በህዝቡ አእምሮ ውስጥ እየተንቆረቆረ ነው። ስለዚህ አንዱ ብሄረሰብ ሌላውን እጅግ ይጠላዋል። እንደርሱ ሰው ያልሆነ ያህል ከአንድ ግንድ ያልሆኑ ያህል አርቆ ይመለከተዋል። ብዙዎች ለአንደበታቸው ያህል ሰውን ሁሉ እወዳለሁ በሰው ላይ ጥላቻ የለኝም ብለው ቢናገሩም በተግባራቸው ግን ያንኑ አያሳዩም። ይህም ከስር ያለው የእይታ መበላሸት ያመጣው ችግር ነው። ይህ ቢገባን ኖሮ ለአንድ ብሄረሰብ ለአንድ ነገድ ጥብቅና አንቆምም ይልቅስ ያለምንም ድንበርና ስም ለሁሉም የሰው ዘር እንቆማለን። ድንበርና ስም ከፈለግንም በዋናው ግንድና ዛፍ ስም እንጠራለን ይኸውም ሰው ነው። ዛሬ በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ። ከአንዱ ብሄረሰብ የሆኑ ሰዎች ሌላውን ብሄረሰብ በደሉ ብለው የሚነሱ ሰዎች እነርሱም በዚያው ወጥመድ ተይዘው የራሳችን የሚሉትን ብሄረሰብ ወክለው ነው ሲነሱ የሚታዩት። የመጀመሪያው ትክክል አይደለም ከተባለ ሁለተኛው ትክክል ሊሆን አይችልም። ሁለቱም ተሳስተዋል ሁለቱም የእይታ ችግር አለባቸው። ትክክለኛ እይታ ያለው ለሰው ልጆች ሁሉ የሚቆም ሁሉንም ሰው ወንድሙ ዘሩ እንደሆነ የሚያውቅ ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ሰው የተጣሉ ሰዎችንም እንኳ ሊያስታርቅ ሲሄድ ልቡ ንጹህና ከአድልዎ የጸዳ ነው። ለምን? ሁሉም የርሱ ከሆኑ ለማን ያደላል? ሁለቱ ልጆቹ እንደተጣሉበት አባት ወይም ሁለት ወንድሞቹ እንደተጋጩበት ወንድም እውነተኛ ሽማግሌ ሆኖ ይቆማል። ሁለቱንም ማጣት ስለማይፈልግ ሁለቱንም የሚያስማማለትን ነገር ነው የሚያደርገው። በሰው ልጆች መካከል የምናየው ግን ይህ አይደለም። መከፋፈል መጠላላት ወገን መለየት እጅጉን በዝቶአል። በጣም የተማርን የሚሉና  ህዝብን ለመምራት የሚሹት እንኳ ይህ በጣም መሰረታዊ የሆነው ነገር አይታይባቸውም። እንዲያውም ለህዝቡ ጥቅም እንታገላለን ከሚሉት ይልቅ እንታገልልሃለን የሚሉት ህዝብ በዚህ እጅጉን የተሻለ ነው። ሰውን በፖለቲካ እይታ ሰዎች በፈጠሩት ዘርና ድንበር ሳይሆን በተፈጥሮው ሰው በመሆኑ ብቻ ስለሚያይ በፖለቲከኞቹ ካልተመረዘ በቀር የተሻለ እይታ አለው። በድሮ ዘመን መማር መማር ነው ይባል ነበር እኔ ግን ተማርን ከሚሉት ሰዎች ከነዶክተር እከሌ ከነፕሮፌሰር እከሌ አንደበት የሚወጣውን ቃል ስሰማ መማር መመረዝ ነው ልል ትንሽ ነው የቀረኝ። ሰው የሚያስታርቅ ሳይሆን የሚያጣላና የሚያጋድል መርዝ ሲረጩ ነው የሚውሉት። የሰላም የእርቅ ቃል ከአፋቸው አይወጣም። ወጣቱ ትውልድም መርዝ መጠጣት ጀግንነት ይመስለዋል መሰለኝ ሲጋተው ይውላል። ታላላቆቹ ጠጥተው ብዙም ያላሰከራቸው መርዝም ወጣቱ ሲጠጣው ያንገላውደዋል ለምን? አዲስ ጠጪ ነውና ገና መስከርን እስኪለምድ ድረስ አንድ ብርጭቆ ሲጎነጭ አናቱ ላይ ይወጣበታል። መርዛቸው ውጤታማ መሆኑንና ብዙዎችን ማስከሩን ያዩት ምሁራንም ተግተው እየቀመሙ ነው። በወጣቱ ትውልድ ለነገ ተስፋ እንዳይደረግ ወጣቱ ትውልድ የነገ አይደለም። ያሳዳጊዎቹን የክፋት ካባ ተላብሶ የክፋታቸው ወራሽ ስለሆነ የነርሱን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ እንጂ የሚያስቆም አይደለም። ሰው ዛሬ በበደሉት መሪዎች ምትክ ነገ በሚመጣው አዲስ ትውልድ ተስፋ እንዳያደርግ ሽማግሌዎቹ ወጣቱን ክፉ ታሪካቸውን በማጠጣት አሰከሩት። እነርሱ በርሱ እንዲቀጥሉ እንጂ እርሱ ለራሱ እንዲኖር እንዲያስብ አይሹም። እንደ ዳዊት ሰው ሁን ብለው ከመምከር ይልቅ እኔን ሁን ይሉታል። በቃ ካልተባለ ይህ የገደል ማሚቶ ይቀጥላል።

ትውልድ ሆይ ከገደል ማሚቶ ውጣ። የራስህን ሐሳብ ድምጽ አፍልቅ። ታሪክን እንደመማሪያ ማወቅ ጥሩ ቢሆንም ወደፊት ለመሄድ ብቻ ሊያገለግል እንጂ ወደኋላ ለመመለስ ከሆነ አይጠቅምም። ከታሪክ ጥሩውን ወስደህ ተጠቀምበት ክፉውን ተምረህበት ጣለው። ክፉ ነበር ካልከው በበጎ ነገር ለውጠው።

ቸር ይግጠመን።

 

%d bloggers like this: