Let us correct our standard መለኪያችንን እናስተካክል።

Let us correct our standard መለኪያችንን እናስተካክል።

የተሳሳተ መለኪያና መዘዙ።

መለኪያ ሲሳሳት አደገኛ ነው ። የሚለካው ቢሳሳት በመለኪያ ተለክቶ ይስተካከላል። መለኪያ ራሱ ከተሳሳተ ግን በርሱ የሚለካው ነገር ሁሉ የተሳሳተ ልክ ይዞ ይወጣል። ለዚህም ይመስለኛል የጥንት ሰዎች ሲተርቱ «ውሀ ቢያንቅ በምን ይውጡ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ» የሚሉት። አንድ ሰው ምግብ ትን ቢለው ውሀ ጠጣ ይባላል። ውሀ ጠጥቶ ከሆነ ትን ያለው ግን ምን ይጠጣል? እንደዚሁም አንድ ሰው በድሮ ዘመን እንደሚደረገው እብጠት ነገር ቢገጥመው በምላጭ ይበጣል ( የድሮ ኦፕራሲዮን ማለት ነው።) ምላጩ ካበጠ ግን በምን ይበጣል? ማለታቸው ነው። በአጠቃላይ የመለኪያ መበላሸት ከሁሉም መበላሸት የባሰ እንደሆነ ለማስረዳት የተነገረ ፈሊጥ ነው። እውነት ነው የሚዛን ወይም የመለኪያ መሳሳት በጣም አደገኛ ነው። ሁሉ ነገር እንዲለካበትና እውነቱን ከሐሰት ትንሹን ከትልቅ ከባዱን ከቀላሉ  ረጅሙን ከአጭሩ ለይቶ ለማሳየት የተቀመጠው መለኪያ የተበላሸ ከሆነ በርሱ ተለክተው የሚቆረጡት ሁሉ በርሱ ተሰፍረው የሚሸጡት ሁሉ የተሳሳቱ ናቸው። በተለይ መለኪያው የሰውን ህይወት ወይም ሰውን ራሱን የሚመለከት ከሆነ ደግሞ አደጋው የከፋ ነው። አንዳንድ ነገሮች ተሳስተን የምናስተካክላቸው አይደሉም ስለዚህ ጥንቃቄ  ይፈልጋሉ። አንድ ዶክተር የአንድን በሽተኛ አካል ሊያክም ቢጠራና ከህመምተኛው ተቆርጦ መወገድ ያለበት ነገር እንዳለ ቢያውቅ የትኛውን ብልት እንደሚደቆርጥ ካልተጠነቀቀ አደጋው የከፋ ነው። የተመረዘውን ብልት እቆርጣለሁ ብሎ ጤነኛውን ቢቆርጥ ከባድ ስህተት ነው። ለዚህም ነው የህክምና ባለሞያዎች ስራ ከፍ ያለ ጥንቃቄን የሚጠይቀው። ስለዚህ ለመለኪያ ትኩረት መስጠት አለብን። በተለይ ህይወታችንን ሐሳባችንን ዓላማችንን ለምንለካበት መለኪያ ጥንቃቄ ካላደረግን አስተሳሰባችን የተበላሸ ይሆናል። በዚህ ጽሑፍ ወጣት ኢትዮጵያውያን ላይ አተኩረን እንነጋገርና ዛሬ የብዙኃኑ መለኪያ ምን ያህል ፈር እየለቀቀ እንዳለ በማየት ከስህተታችን እንማር። አስቀድሜ  እንዳልኩት የመለኪያ ስህተት ዘላቂ ጉዳትን የሚያስከትል ነገር ነው። ስለዚህ አስተሳሰባችንንና ዓላማችንን በአጠቃላይ ርዕዮተ ዓለማችንን የምንለካበትን መለኪያ መፈተሽ አለብን።

ለምሳሌ የተሳሳተ የውበት መለኪያ ስንት እህቶቻችንን እየጎዳ እንዳለ ተመልከቱ። ቆንጆ ማለት አፍንጫ ሰልካካ ቀጭን ተክለ ሰውነታ ያላት  ናት የሚል መለኪያ ስለተሰራጨ በዚህ መለኪያ ራሳቸውን በመለካት የተለያየ አላስፈላጊ ቀዶ ጥገናና የመድኃኒት ቅመም እየተጠቀሙ መልካሙን ተክለ ቁመናቸውን ያበላሻሉ። በዚህ መለኪያ ሐሳባቸው የተበላሸ ብዙ ሴቶች የራሳቸውን የተፈጥሮ ሰውነት እንደ ጠላት በማየት መስተዋት እንኳ ለመመልከት እስከመፍራት ደርሰዋል። አንዳንዶቹም ወፍራም ነኝ ቆንጆ አይደለሁም በሚል በህይወታቸው ላይ አሳዛኝ እርምጃ እስኪወስዱ ደርሰዋል። ይህ ሁሉ የተሳሳተ መለኪያ ውጤት ነው።

ሌላው ጥቁር አሜሪካውያንን እንደምሳሌ ብንወስድ ራሳቸውን በተሳሳተ መለኪያ እንዲለኩ ስለተፈረደባቸው በዚህ ነጮች በሰሩላቸው መለኪያ ራሳቸውን እየለኩ ብዙ ተጎድተዋል። ለምሳሌ ብዙ ወጣቶች ጸጉራቸው ከርዳዳ መሆኑና እንደ ነጮች ዘርፈፍ ያለ ሉጫ ባለመሆኑ ስለሚያሳፍራቸው ከዚያ ለማምለጥ ብዙ ሞክረዋል። አንዳንዶቹ ለስላሳ ጸጉር ለማግኘት ብዙ መድኃኒቶችን ሞክረዋል አንዳንዶች ደግሞ ቆዳቸውን የሚልጥና ነጭ የሚያደርጋቸውን መድኃኒት እስከመጠቀም በመሄድ አካላቸውን አበላሽተዋል። ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? ከርዳዳ ጸጉርና ጥቁር ፊት ጥሩ አይደለም ያላቸው ማነው? ይህንን የተሳሳተ መለኪያ ያወጡላቸው እነርሱን እንደሰው የማይቆጥሩአቸው ነጮች ናቸው። እየቆየ ሲሄድ ግን እንደ ትክክለኛ መለኪያ ተቀብለውት ራሳቸውን ይለኩበትና ይከረክሙበት ጀመር።  ።እነዚህ በጣም ጥቂቶቹ ምሳሌዎች ናቸው።    ጥቁር የያዘው ነገር ሁሉ እንደማይረባና ሁሉን ነገር ከነርሱ መማር እንዳለብን የሚሰብኩን ነጮች ብዙዎች ናቸው። የሚያስገርመው ግን የነርሱ መስበክ ሳይሆን የኛ አሜን ብሎ መቀበልና እነርሱ ባወጡት መለኪያ ራሳችንን እየለካን አስተሳሰባችንን ሁሉ ስንከረክም መዋላችን ነው። ይህ ነገር ገና ብዙም ሳይገባኝ በነበርኩበት በአንድ ወቅት ከአንድ አሜሪካዊ አለቃየ ጋር ስነጋገር አንድ ነገር ተማርኩ። በንግግራችን መሃል ስለሥራ ጉዳይ ላስረዳው ስሞክር አንድ ቃል ጠፋብኝና ከዚያ በሌላ ቃላት ተክቼ አስረዳሁት። ከዚያ በኋላ እንግሊዘኛውን አቀላጥፌ በመናገር ቶሎ ሳላስረዳው በመቅረቴ ቅር አለኝና ጉድለት ስላለበት እንግሊዘኛየ ይቅርታ ጠየቅኩት። እርሱም በመገረም ያልጠበቅኩትን ምላሽ ሰጠኝ። አንተኮ ተምረህ ያልተወለድክበትን ቋንቋ ሰማንያ በመቶ ትናገራለህ እኔ ግን ካንተ ቋንቋ አንድ ቃልም አልናገርም ስለዚህ ግማሽ መንገድ ባለመምጣቴ ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ እኔ እንጂ አንተ አይደለህም አለኝ። እውነትም ነገሩ ገረመኝ ለምን እንደዚያ አላሰብኩትም? ምክንያቱም የተሳሳተ መለኪያ ሰለባ ሆኞለሁዋ። አያችሁ አንድን መለኪያ ሳናጣራ ዝም ብለን ከተቀበልነው ከዚያ በኋላ በዚያ እየለካን ብዙ ነገር እናበላሻለን። ብዙዎቻችን ከአንድ ነጭ ጋር ስንገናኝ እኛ እንደምንም የቃረምናትን እንግሊዘኛ ተጠቅመን ልናናግረው እንሞክራለን እንጂ እርሱ በኛ ቋንቋ ያናግረናል ብለን አንጠብቅም። እሺ ወሰ  ነጮቹ አገር ከሄድንስ ያው የአገሩ ቋንቋ ነውና መናገር ግዴታችን ነው። እኔ ችግሬ ከመናገራችን ጋር ሳይሆን ከአስተሳሰባችን ጋር ነው። ወደ እኛ አገር የመጣው እርሱ ሆኖ ሳለ። መንገድ ጠፍቶት ሊጠይቀን ያሰበው እርሱ ሆኖ ሳለ ለመናገር ስንቸገር የምንታየው ግን እኛ ነን። እነርሱም በዚህ የተሳሳተ መለኪያ ውስጥ እንደሆንን ሲያውቁ ጥቂት መግባቢያ ቃሎችን ሊያጠኑ ያሰቡትን እርግፍ አድርገው እኛ የነርሱን ቋንቋ ተምረን እንድናገለግላቸው ይጠብቁናል። ድሮ በእንግሊዝ ጸሐይ አትገባም ይባል ነበር አሁንም በእንግሊዘኛ ላይ ጸሐይ እንዳትገባ እየታገልን ያለን ይመስላል። ችግሩ ይህ ብቻ በሆነ ጥሩ ነበር። በዚህ ትንሽ ነገር የጀመረው  የተሳሳተ አስተሳሰብ ግን አገርን እስኪያናጋ ድረስ ስሩን እየሰደደ ነው። ዛሬ እንደምናየው በዋርካ ስር በሽምግልና ስርዓት በእድር በሰንበቴ በቤተ ክርስቲያን በወበራ በገዳ ስርዓት ራሱን በራሱ ሲያስተዳደር ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረው ህዝብ የኑሮ ስርዓት ተንቆ ትናንት ከተወለዱ ምእራባውያን የተሸመተ «ዲሞክራሲ» የሚባል ስሙን እንጂ ትርጉሙን በማያውቅ ትውልድ እየተለፈፈለት ነው። አሜሪካ የሁለት መቶ አመት አገር መሆንዋ ተረስቶ ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ራሱን በራሱ ሲያስተዳደር የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም እንደማያውቅ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር ካልሸመትክ አትጠቅምም እየተባለ ያለ ይመስላል። ምእራባውያን ባወጡልን መለኪያ ተለክተን አልፈን ካልተገኘን ወዮልን እየተባልን ነው። ለመሆኑ እነርሱ እነማን ናቸው? በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ያለው ህሊና የዋህነት አብሮ መኖር መልካም ጉርብትና ሽምግልና የጠነከረ ማህበራዊ ህይወት በነርሱ ዘንድ ይገኛል? በምእራቡ አለም ያለው ስርአት እኮ እንደ ማሽን ህሊና የሌለው ሰውን እንደ ፋብሪካ ምርት የሚሰፍርና የሚያስተዳደር ነው። በኢትዮጵያ ያለው ለዘመናት የተሸመነ ግሩም ማህበራዊ ሕይወትኮ በምዕራባውያን ሰርዓት የመጣ አይደለም። እንግዲህ ይህንን የምእራባውያንን መለኪያ የሁሉ መለኪየ አድርጎ መውሰድና ኢትዮጵያ ከእግር እስከራስ ሁለ ነገርዋ በርሱ ተለክቶ ካልተከረከመ የሚል ትውልድ ነው አሁን እየተሰማ ያለው። ወዶ ገብ ሀሞት የሌለው የራሱን ሁሉ ጥሎ የሌላውን ሊያነሳ የሚሮጥ። ጤና ይስጥልኝን ሳያውቅ How are you doingን የተማረ ክልስ ትውልድ እየታየ ነው። ለመሆኑ ማነው የምእራባውያን ዲሞክራሲና ስርዓት ትክክለኛ መለኪያ ነው ያለን? እነርሱ ሳይኖሩ ለዚህ ሁሉ ዘመናት የተመራንበት ስርዓት ምን ሆነና ነው የነርሱን የምንሸምተው? በዚህ መለኪያ ተከርከመው የተነሱ ብዙዎች ግን የሐሳብ ባንዳ ሆነው በኢትዮጵያ ላይ ተነስተዋል። ሰው እንዴት እንደሰው ከማይቆጥረው ፖለቲከኛ ጋር ሆኖ በአገር ላይ ይነሳል? ለናንተ እንቆማለን ብለው ከሚያታልሉአችሁ ነጮች ይልቅ በሐሳብ ያልተስማማችሁት ኢትዪጵያዊ ይሻላል። በሐሳብ መጋጨት ያለ ነው በሐሳብ ብንጋጭ በውይይት እንስማማለን። ከውስጥ ከልባችን ግን አንድ የሚያደርገን ነገር አለ ኢትዮጵያዊነት። ማቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ያልጠበቅከኩትን ነገር ሰማሁ። እኚህ ሰው ጨቋኝ የሆነውን የደርግ መንግሥት ለመጣል የወጣትነት እድሜአቸውን ሁሉ በጦርነት ያሳለፉ ናቸው። የአፍሪካ ህብረት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሌላ አፍሪካ አገር እንዲዛወር ከአንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች  ሐሳብ በቀረበበት ወቅት ግን ንጉሥ ኃይለ ሥላሴንና መንግስቱ ኃይለ ማርያምን በማሞገስ ተናገሩ። እንዲህም አሉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ቢሆን በአገር ውስጥ አምባገነን ይሁን እንጂ ለአፍሪካ ነጻነት የታገለ ሰው ነው። ዚምባብዌ ነጻ እንድትወጣ የታገለው ማነው? በማለት በጎውን ጎን ተናግረዋል። መንግሥቱን ከሚመስል አስተዋይነት የሌለው ጨካኝ መሪ በጎ ነገር ያገኛሉ ብየ አልጠበቅኩም ነበር። እውነትም በደንብ ስናስብ ሁለቱም ለአንዲት አገር የሚያስቡና የሚታገሉ ሰዎች ነበሩ። መንግሥቱ ወደ ስልጣን ከመጠ በኋላ በችሎታ ማነስ ብዙ ችግር ያድርስ እንጂ መነሻው ግን ለተበደለው ህዝብ መልካም አስተዳደር ለማምጣት ነበር። ለማለት የፈለግሁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተለያየ ሐሳብ ቢለያዩ ግን ኢትዮጵያዊ ናቸው። የሐሳብ ልዩነታቸውን በውይይትና በመስማማት በመፍታት ወደ አንድነት ሊመጡ ይገባል እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደጠላት ቆጥሮ ከነጭ ፖለቲከኞች ጎን ቆሞ የነርሱን የሻገተ ዲሞክራሲ በህዝቡ ላይ ለመጫን መጣር ተላላኪነት ነው። ምንም ብሎ ይጥራው ህዝቡ ለብዙ ሺህ ዘመናት የተመራበትና አብሮ የኖረበት ስርአት አለው። የግዴታ ዲሞክራሲ ተብሎ ስላልተጠራ ብቻ ምንም እንደሌለው ሊታሰብ አይገባም። ምንም ይሁን ምን ህዝቡ በራሱ ፈቃድና ሐሳብ መመራት አለበት። ስለዚህ የፖለቲካ መለኪያችን የኢትዮጵያ ይሁን። የሶቪየት ህብረት መለኪያ አመጣን አልጠቀመንም። አሁን ደግሞ አንዱ የአሜሪካን ሌላው የቻይናን ለማስገባት መሞከሩ አይጠቅምም። ኢትዮጵያ የራስዋ ነጻ ሕዝበ ያላት አገር ናት ብለን ካመንን ነጻ ህዝብ ነጻ ሐሳብ አለው። ስለዚህ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ አመራርና አሰራር በምእራባውያን እየለካን ለመቁረጥ አንሞክር። አንድ ሰው የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ከፈለገ መጀመሪያ ራሱ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት በወረቀት ሳይሆን በአስተሳሰብና በዓላማ ኢትዮጵያዊ የሆነ በኢትዮጵያውያን የአመራር ዘይቤ ኢትዮጵያን የሚያገለግል ሊሆን አይገባም። ብዙዎች ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ያለው ስርዓቱ በምእራባውያን ሜትር ተለክቶ ስላልተቆረጠ ነው ሲሉ ይሰማሉ። እውነቱ ግን ችግሩ እየተባባሰ ያለው የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ መለኪያ ትተው በምእራባውያን መለኪያ ለክተው ለመቁረጥ እየታገሉ ስለሆነ ነው። ችግሩ መለኪያው ነው። መለኪያችንን እንለውጥ።

quna

%d bloggers like this: