MESSAGE OF PEACE FOR ETHIOPIANS

MESSAGE OF PEACE FOR ETHIOPIANS

ለኢትዮጵያ ህዝብና ለኢትዮጵያ መንግስት ያለኝ መልእክት።

አንድ ኢትዮጵያዊ ተራ ዜጋ ነኝ። በአገሬ ጉዳይ ላይ ብዙም ድምጼን አሰምቼ  አላውቅም። አሁን በዚህ ወቅት ላይ እየሆነና እየተባለ ያለው ነገር ግን እንደ አንድ ዜግነቴም ቢሆን ድምፄን ማሰማት አለብኝ ብየ እንድነሳ አስገድዶኛል።

በአሁኑ ወቅት ከመልካሙ ነገር ይልቅ ክፉው ነገር ጎልቶ እየተሰማ ያለ ይመስላል። የሰላም የፍቅር የአንድነት ድምጾች በክፉ ድምጾች እየተዋጡ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። መልካሙን ቸሩን በጎውን የሚናገሩ ሰዎች ብዙም ድምጻቸው አይሰማም። ድህረ ገጾች ሁሉ በጥላቻና በጦርነት አዋጅ የተሞሉ ሆነዋል። መልካሙን የሚያስደስተውን የፍቅርና የአንድነት ወሬ እንደ መስቀል ወፍ በብዙ ጥበቃ የሚመጣና ወዲያው ደግሞ የሚጠፋ ሆኖአል።  መልካሙና በጎው ድምጽ ጠፍቶ ምናልባት እንደኔ ለመልካሙና ለበጎው ድምጻቸውን ማሰማት የሚገባቸው ሰዎች ዝም ስላሉ ይሆናል ብየ  ድምጼን ላሰማ ተገደድኩ። አምላኬ ሆይ ድምጼን በክፉ ወሬ ከመበላትና ከመዋጥ አድነህ መልካሙን ነገር መስማት ወደ ተራቡ ወደ ብዙዎች ጆሮ ታደርስልኝ ዘንድ እማፀንሃለሁ።

ለኢትዮጵያ ህዝብ

  • ካለፈው ስህተት እንማር

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከውጭ ጠላት ጋርና በአገር ውስጥ ባሉ መንግስታት በሚደረጉ ጦርነቶች ያደረገቻቸው አስፈላጊና አላስፈላጊ ጦርነቶች እንደነበሩ ከታሪክ እንማራለን። ከውጭ ኃይሎች ጋር የተደረጉት ጦርነቶች የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አስፈላጊ የነበሩ ቢሆኑም በኢትዮጵያውያኑ መካከል የተደረጉት ግን አብዛኛዎቹ በሌላ መፍትሄ ሊወገዱ ይገባቸው የነበሩ ናቸው። ሌላውን ትተን ያለፉትን ሁለት የመንግስታት ለውጥ ብንመለከት ያለምንም ጦርነት ሊፈቱ ይችሉ የነበሩ ችግሮች በጦርነት ሲቋጩና ስንት ወጣት ሲያልቅ አይተናል። የዓጼ ኃይለ ስላሴን መንግሥት ብንወስድ ብዙዎች የተጨቆኑበት በአገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የኖሩበት የላይኛው የመሳፍንት ወገን ብቻ የተጠቀመበት ከዚያም አልፎ የባሪያ ስርዓት የነበረበት ዘመን ነው። ይህ ሁሉ ግን ከንጉሱ የአስተዳደር ጉድለት ብቻ የመጣ ሳይሆን እርሳቸው ሳይወለዱ የነበረ የቆየ በሌላውም ዓለም የነበረና ከዘመኑ አለመሰልጠን የተነሳ የመጣ ስርአት ነበር። ስለዚህ የነበረውን የኑሮ ስርዓት የአንድ ንጉስና የባለሟሎቻቸው ችግር ብቻ አድርጎ መውሰድ ሚዛናዊ አይመስለኝም። ምናልባት ንጉሱ ከተወቀሱ ያንን ስርዓት ለመለወጥ እንደሚገባ አልተራመዱም ተብለው እንጂ ሙሉ በሙሉ የዚያ ዘመን የኑሮ ሁኔታና ማህበረሰባዊ ልማድ ምንጭ እርሳቸው አይደሉም። እኚህ ሰው ሁሉንም ነገር በአንድ ጀምበር ባያጠፉም አገሪቱ ወደተሻለና ወደ ሰለጠነ የኑሮ ስርዓት እንድትራመድ ግን ብዙ አጽተዋጽኦ አድርገዋል።  የአገሪቱን ህልውናና ነጻነት ለማስጠበቅ ብዙ እልህ አስጨራሽ  ዲፕሎማሲያዊ ሥራን ሰርተዋል። ከህዝቡ ጋር ሆነውም ለአገሪቱ ነጻነት የሚችሉትን ያህል ተዋግተዋል። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች መብትና ነጻነት ትልቅ ተጋድሎን እንዳደረጉ የሚጠሉአቸው እንኳ ይመሰክራሉ። የኢትዮጵያ ጠቅየላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ንጉሱን ስላደረጉት ስለዚህ መልካም ተጋድሎ ሲያመሰግኑአቸው በመስማቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዓይናቸው ሙሉ በሙሉ በፖለቲካ ሸማ እንዳልተሸበበና አጮልቀው ማየት እንደሚችሉ አሳይቶኛል። ሌሎችም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች  ከርሳቸው የበለጠ የታሪክን እውነታ አጉልተው በማየት ከግል ጥቅምና ጉዳታቸው ይልቅ ታሪክን በአገር ታሪክነቱ ብቻ በመቀበል የነዚህን በዘመናቸው ታሪክ ሰርተው ያለፉትን ኢትዮጵያን ዜጎች ስም የሚያስጠራና ወጣቱ ትውልድ የሚማርበትን ሁኔታ በሚያመቻች መልካም ነው እላለሁ። እነዚህ ሰዎች ከነጉድለታቸውም ቢሆን የቻሉትን ሁሉ አድርገው ኢትዮጵያ የምንላትን ውድ አገር ያቆዩልን ሰዎች ናቸው። መለካት ያለባቸውም በዚያን ዘመን ስልጣኔና ሁኔታ እንጂ በአሁኑ ዘመን መነጽር ሊሆን አይገባም። መልካሙ ስራቸውን ብቻ ሳይሆን ጉድለታቸውንም እኮ ልንማርበት እንችላለን። ኃይለ ስላሴም ሆነ ከርሳቸው በፊት የነበሩት ነገስታት ለውጥን ሊያመጡ የታገሉት ስልጣኔ ካልነካው የህብረተሰብና የሃይማኖት አስተሳሰብ ጋር እንዲሁም ያንን የድሮ ስርዓት እንዳይፈርስ ከሚታገሉ ጥቅመኞች ጋር እየተሟገቱ ስለሆነ ነገሩ በአንድ አዋጅ የሚፈራርስ ነገር አልነበረም። ዘጠና ከመቶ መልካም ሰርቶ አስር ከመቶ ጉድለት ያለበትን ሰው መልካሙን ትቶ ክፉውን በማጉላት ማስጠላት በአገሪቱ የተለመደ ስለሆነ እንጂ እኚህ ሰው ላደረጉት መልካም ነገር ምስጋና ይገባቸው ነበር። ለመልካሙም ለክፉም ነገራቸው በዚያን ዘመን ስልጣኔ መለኪያ እንጂ በአሁኑ ዘመን ስልጣኔ ሊመዘኑ የሚገባ አይመስለኝም። ይህንን የምለው የርሳቸው ስርአት ተጠቃሚ ስለሆንኩ አይደለም። እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ነው የተወለድኩት። ነገር ግን ከታሪክና ከሰሩአቸው ስራዎች ስመለከት የሚገባቸውን ምስጋና ያገኙ አይመስለኝም። በአሁኑ ሰአት በምኖርበት አገር የምከበረው በርሳቸው ስራና ስም ምክንያት እንጂ በአሁኑ መሪዎች ስም አይደለም። ኢትዮጵያ ከርሳቸው ስም ጋር ተያይዛ ስትነሳ ወይም ኢትዮጵያዊ መሆኔን ስናገር ያንን ዘመን የሚያውቁ የእድሜ ባለጸጎች ከኃይለ ስላሴ ስም ጋር በማያያዝ የሚሰጡኝ አስተያየት አገሪቱ በዚያ በጨለማው ዘመን ጥቁር እንደ ሰው በማይቆጠርበት ዘመን ምን ያህል መልካም ገጽታ እንደነበራት የሚያሳይ ነው። ይህንን ስል በዚያን ዘመን የተደረገው ጭቆናና ዘውዳዊ ስርዓት ሁሉ ትክክል ነበር ማለት ሳይሆን ነገር ግን ከኢትዮጵያም አልፎ ለጥቁር ህዝቦች የተደረገ መልካም ምሳሌነት ያለው ስራ ነበር ማለቴ ነው። ከዚህም ውስጥ ኤርትራን ለማስመለስ የተደረገው ረጅም የሰለጠነና ከኞ ወዲያ ላሳር የሚሉትን ነጮች ያሳፈረ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ነው።  ለሃምሳ አመታት ከኢትዮጵያ ተነጥላ የነበረችን አገር ያለምንም ጦርነት ማስመለስ ቀላል ነገር አይደለም። ጥቁር እንደሰው በማይቆጠርበት በዚያ ዘመን አክሊሉ ሀብተ ወልድ ያደረገውን ይህንን ታላቅ የዲፕሎማሲ ስራ የማያደንቅ ሰው ያለ አይመስለኝም። ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የተነሳው ትውልድ ግን ለውጥን ለማምጣት እነዚህን ብርቅየ ልጆች በመግደል ነበር የጀመረው። ሌላው ዓጼ ኃይለ ስላሴ ወጣቶችን ለማስተማር ያደረጉት ጥረት ነው።  የሚያሳዝነው የርሳቸው ጠላት ሆነው የተነሱትና አግባብ ያለው ሞት እንኳ የነፈጉአቸው ወጣቶች በርሳቸው ጥረት የተዘረጋው የትምህርት ገበታ ተካፋዮች የሆኑት ነበሩ። የግል ቤታቸውን ሳይቀር ዩኒቨርስቲ በማድረግ ብዙዎችን ወደ ውጭ በመላክ ያስተማሩና አገሪቱን የሚመሩ ተተኪ ወጣቶችን እንዲማሩ ያበረታቱ የነበሩት እኚህ ንጉሥ ይህ ሁሉ መልካም ነገር እንደሚገባ አልተነገረላቸውም ባይ ነኝ። ሁልጊዜ ጉድለትን ብቻ ለማየት የሰለጠነ ዓይን ካለን ግን ይህን ማየት አንችልም። ምንም እንኳ ያ የዘውድ ስርአት ጠቃሚ የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን ሁሉም ቢገነዝብም ንጉሱ ከፍተውት በነበረው የትምህርትና የአስተዳደር ለውጥ ክፍተት ተጠቅሞ እርሳቸውን በክብር ካነሱ በኋላ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ነገሮች በማስተካከል እርሳቸውን ግን እንደ አንድ ዜጋ በክብር መሸኘት ይቻል ነበር። ለብዙ ዓመት ብዙ መልካም  ነገርን የሰራን ሰው እንደ ውጭ ጠላት ማየት መልካም አልነበረም። ሰለጠነ በሚባለውና እንደምሳሌ በምንጠቅሰው ዓለም የሚደረገውን ተመልከቱ። ለምሳሌ በአሜሪካ ብዙ መልካም ያልሆነ ነገር የፈጸሙ ፕሬዚደንቶች አሉ። ያ ግን ከታሪክ መዝገብ እንዲፋቁ አላደረጋቸውም። ህዝቡ ካደረጉት ክፉ ነገር ተምሮ የሰሩትን መልካም ነገር ደግሞ ተቀብሎ ሲዘክራቸው ይኖራል። እነዚህ መሪዎች በኃይለ ስላሴ ከተደረገው ክፉ ስራ ሁሉ የባሰ ስራ የሰሩ ናቸው። ብዙ ኢትዮጲያውያን የነዚህን ሰዎች ሀውልት ለመጎብኘት ይሄዳሉ የኢትዮጵያን ነገስታት ሀውልት ግን አይተው አያውቁም። ለመሆኑ ያ ንጉስን የሚያስታውሰኝ ብቸኛ ነገር ስማቸው የተጻፈበት የቤተ መንግሥት አጥር አለ ይሆን? የደርግ መንግሥት ያንን ባለማፍረሱ ሳላመሰግነው አላልፍም። ከጥላቻው ጥልቀት የተነሳ ከርሱ በፊት የነበሩትን መሪዎች ፈለግና አሻራ ሁሉ መደምሰስ የሚፈልግ ትውልድ እጅግ ያስፈራል። የርሱም በሌላው እንደሚደመሰስ አያውቅም። ታሪክ ስንደመስስ እኛም ሌላ ታሪክ ደምሳሽ ትውልድ እየፈጠርን ነውና ጊዜውን ጠብቆ የኛም ይደመሰሳል። ከዚህ ጋር አያይዤ የማነሳው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው። መንግሥት የሃይማኖትን እኩልነት ሲያውጅና እምነቶችን ሁሉ በፖለቲካው መቀስ እኩል አድርጎ ሲከረክማቸው የአንድ ሺህ ሰባት መቶ አመታት ታሪክ ያላትንና የኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን እኩል ሲያስቀምጣት በጣም ነው የገረመኝ። ይህችም ቤተ ክርስቲያን እንደ ንጉሱ ነው የተደረገችው። እውነታውን ስናይ ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን ከነገስታቱና ከኢትዮጵያ የመንግሥት ስርአት ጋራ ከነበራት ግንኙነት የተነሳ እንደ አንድ ቤተ እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ቅርስና እንደ ታሪክ ቤተ መዛግብት ታይታ በዚህ ብቻ የተለየ ትኩረትና ቦታ ሊሰጣት ይገባ ነበር። ምክንያቱም ወደድንም ጠላንም ያለፈው ረጅም የኢትዮጵያ ታሪክ ተሰፍሮና ተመዝግቦ ተቀርጾ ያለው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያንዋ አስተምህሮ ባያምንም እንኳ በያዘችው አገራዊ ታሪክ ግን ድርሻ አለው። ታሪኩ የራሱ ነው ታሪኩ የኢትዮጵያ ነው። ቤተ ክርስቲያንዋ መንግስታትን አገራቸውን እንዲጠብቁ በማስተማርና አብራ በመቆም አገር እንዲጠበቅ አድርጋለች። ለምሳሌ አጼ ዮሐንስ አገሪቱን ከእስልምና ወራሪ ለመላከል ህይወታቸውን እስከመስጠት የታገሉት ከፖለቲካ መሪነት አንጻር ብቻ ሳይሆን የአገሪትዋን የሃይማኖት ባለቤትነት በማወቅና ያንንም ለማስጠበቅ መሆኑን ከታሪክ ድርሳናት እንማር። አጼ ሚኒሊክም የአድዋን ጦርነት ሲያውጁ የተናገሩትን ስናይ ጦርነቱ አገርን ከመጠበቅ ብቻ የተደረገ የአንድ ፓለቲካ መሪ ንግግር ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልብ የሚያሳይ ነው። ለሃይማኖትህ ተነስ የሚለው ቃል ለየትኛው ሃይማኖት እንደሆነ የታወቀ ነው። ሲዘምቱ እንኳ ታቦት አሸክመው ነው የዘመቱት። ይህንን የምጽፈው ሰው እምነቴ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አባል ነኝ። ምንም እንኳ በወንጌል አንድ ብንሆንም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባይኖሩ የምላቸውና ከቃሉ ውጭ ናቸው ብየ የማስባቸው ብዙ አስተምህሮዎች አሉ። ይህ ግን ቤተ ክርስቲያንዋ ለኢትዮጵያ ያደረገችው ረጅምና ሰፊ የታሪክ ጉዞ እንዳላይ አላደረገኝም። የአገሬን የኢትዮጵያን መልክ ከርስዋ ውጭ ማየት አልችልም። የኢትዮጵያን የአንድ ሺህ ሰባት መቶ አመት መልክ የምናይባት መስተዋት ናት። ስለዚህ ትናንትና ከተመሰረቱ ቤተ እምነቶች እኩል እንያት ስንል እያዳላን ያለን ይመስለኛል። ይህ ማለት የሌሎቹ ቤተ እምነቶች እምነት ትክክል አይደለም ወይም ዝቅ አድርገን እንየው ማለት አይደለም። ነገር ግን በሌሎቹ ቤተ እምነቶች ውስጥ የማይገኝ የታሪክ አሻራ አላትና ለዚህ ማንነትዋ የተለየ ትኩረትና ድጋፍ ያስፈልጋታል ባይ ነኝ። ፊደልን በመጠበቅዋና በማስተማርዋ የእውቀት ምንጭ ናት። እስከ ዓጼ ኃይለ ስላሴ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎችና ሹሞች ሁሉ ተምረው የተመረቁትና ህዝቡን ያገለገሉት ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ባገኙት እውቀት ነው። በሌሎች ቤተ እምነቶች የሌሉ ብዙ የታሪክ ድርሳናት የሚገኙት በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። ስለዚህ ከቤተ እምነቶቹ ሁሉ እንደ አንዱ ሳይሆን በተለየ ሁኔታ እንደ የአገሪቱ ታሪክ እንደ የህዝቡ ሀብት ልትታይ ይገባል ባይ ነኝ። ሳላስበው ወደዚህ ገባሁ። አሁን ወደ ወቅቱ ጉዳይ ልመለስ። ለማለት የፈለግሁት እያፈረስን መጀመር ማቆም አለብን። የደርግ መንግሥት ያንን ሁሉ የማፍረስ ስራ ማድረስ አያስፈልገውም ነበር። ንጉሱ ለይስሙላ ተቀምጠው አስተዳደራዊ ስርአቱን መቀየር ይቻል ነበር። እነዚያ የአገር ሀብት የሆኑት ስድሳ ባለስልጣናት መገደል አልነበረባቸውም። ጳጳሱ መገደል አልነበረባቸውም። ቀይ ሽብር አስፈላጊ አልነበረም። ያ ሁሉ ወጣት ማለቅ አያስፈልገውም ነበር። መጀመሪያ ለህይወት ክብር ከመስጠት የማይጀምር ሽግግር ሁሉ ጤነኛ አይደለም። የሰው ደም እያፈሰሱ ልማትን ስለማምጣት መናገር እብድነት ነው። ይህንን ሁሉ ያነሳሁት ከነዚህ ሁሉ ስህተቶች የተማርን ስላልመሰለኝ ነው። አሁንም ያ ደመና እንዲመጣ ብዙ ወጣቶች እንዲያልቁ የሚፈልጉ ረጅሙን ሰላማዊ የድምጽ ትግል ሳይሆን አቋራጭ የጦርነት መንገድ የሚመርጡ እየተሰሙ ስለሆነ እንዳታምኑአቸውና ወደዚያ ሸለቆ እንዳትወርዱ ትምህርት ይሆነን ዘንድ ነው ያንን ዘግናኝ ነገር መልሼ የማስታውሰው። ያንን ሁሉ ወጣት የፈጀው የደርግ ስርአት ሌላ ደግሞ እርሱን የሚያፈርስ መጣበት። አሁንም ከዜሮ ተጀመረ። ቢሆንም አሁን ያሳለፍናቸው ሃያ  ዓመታት የተሻሉ መሆናቸውን እንመለከታለን። ቢሆንም  አሁን ያለው መንግሥትም ብዙ ድክመት አለበት። እንደ ድሮው ቀይ ሽብር ተብሎ በጅምላ መጨረስ ባይኖርም አሁንም ሰዎች ይሞታሉ ፍትህ ሲጓደል ይታያል። ይህንን ያዩ አንዳንድ ሞኞች አሁንም ከዜሮ አሁንም ከደደቢት መጀመር ይፈልጋሉ። ለምን ስትሉአቸው ሰው ስለሞተ ፍትህ ስለታጣ ይላሉ። እውነቱ ግን በኢትዮጵያም ሆነ ሰለጠኑ በምንላቸውም አገራት በየእለቱ ሰው ይሞታል አስተዳደራዊ ጉድለት ይታያል። ፍትህ ይጓደላል። አሁን ያለውን መንግሥት ገልብጣችሁ ስልጣን ብትይዙም ሰው ይሞታል ፍትህ ይጓደላል። መልካም መንግሥትማለት ምንም ችግር የሌለበት አገርና ህብረተሰብ የሚመራ ማለት ሳይሆን ያንን ችግር በአግባቡ የሚያስተናግድና የሚፈታ ስርአት ማለት ነው። በምታመልኩአት በአሜሪካ በየእለቱ ሰዎች በግፍ ይገደላሉ ሰው በተገደለ ቁጥር ግን መንግሥት አይለወጥም። ያንን ያደረገው ሰው ይጠየቃል ይቀጣል ህይወት እንደድሮው ይቀጥላል። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርገው ቢሆን ኖሮ የከፋ ችግር ሊያደርሱ ይችሉ የነበሩ ነገሮች በአሜሪካ ተደርገዋል ግን መንግሥት መገልበጥ ጦርነት የሚባል አይታሰብም።  የፍትህ ስርአቱ ያለ አግባብ የሚበድላቸውና የበደላቸው ሰዎች አሉ። ይህንን የሚያስወግዱት ግን መንግሥትን በመገልበጥ ሳይሆን ረጅምና አድካሚ የሆነ የማህበረሰብ ተጋድሎ በማድረግ ነው። አንድ ማወቅ ያለብን ነገር የስልጣኔ ሁሉ ቁንጮ መንግሥትንም ሆነ ስርአትን ያለ ትጥቅ ትግል መለወጥ ነው። ይህንን ማድረግ እስከምንችል ድረስ ምንም አልሰለጠንንም ማለት ነው። በጣም የሚገርመኝ አሁን የጦርነትን አታሞ እየመቱ ያሉትና መንግሥትንና የማይፈልጉትን ስርአት በጦርነት ለመገልበጥ እየቀሰቀሱ ያሉት ሰለጠንንና ተማርን የሚሉት ሰዎች መሆናቸው ነው። ስልጣኔና መማር ይህ ከሆነ መማር ይቅርብኝ መሰልጠን ይቅርብኝ የሚያስብል ነው። አሁን አሁን ሳየው አልተማረም የምንለው ህዝብ ከኛ በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑን ነው። ግብታዊና ስሜታዊ አመጾች ሁሉ የሚመነጩት ከዩኒቨርስቲዎች መሆኑን የህዝቡን አእምሮ የሚበክሉ ክፉ ትንተናዎች የሚሰራጩት ከነዚሁ ተማሪዎችና ከፕሮፌሰሮች መሆኑን ሳይ መማር ለምኔ ያስብላል።  ደሊላ የሆነችው ዓለም መማርና ስልጣኔ በሚባለው ምላጭዋ  የተፈጥሮ ጸጋውን ሙልጭ አድርጋ እየላጨች ትእግስትና ፍቅር መቻቻልና የዋህነት የሚባል ነገር የማይበቅልበት መላጣ የሆነ የጭንቅላት ምድረ በዳ ታሸክመዋለች። የድሮው ጠቅላይ ሚኒስቴር  በመላጣነታች ብዙ ይባል ነበር። እኔ ግን የሚታየኝ የተማሩት ሁሉ መላጦች መሆናቸው ነው። የርሳቸውስ የውጭ ጸጉር መሸሽ የውጭ በረሀነት ነበር። የተማርን ነን ብለው አገር እያመሱ ያሉት የብዙ ምሁራኖች መላጣነት ግን የልብ የውስጥ የአእምሮ መላጣነት ነው አፍጥጦ እየታየ ያለው። ከህዝቡ ያገኙት መልካም እሴት መከባበርን መቻቻልን አንተ ትብስ አንተ ትብስ መባባልን መቀራረብን ሁሉ በፖለቲካ ምላጭ ሙልጭ አድርገው አስላጭተው ምድረ በዳ ለምለም ነገር የማይበቅልበት አእምሮ ይዘዋል። መቻቻል መደጋገፍ በክፉም በደጉም አብሮ መቆም መልካም ጉርብትና በጎ ህሊና ያለው አልተማረም በምንለው ህዝብ ውስጥ ነው። ይህ ህዝብ አስተዋይ ነው። ደም የተቃባን እንኳ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ የሚያስታርቅ ለዘመናት በቀሰመውና የሚገባውን የፕሮፌሰርነት ማእረግ ባላስገኘለት ከካሪኩለም ውጭ በሆነ ጥበብ የሰለጠነ። ጥበቡና ማስተዋሉ ሁሉ ወረቀት ላይ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል በልቡ የተጻፈለት ራሱ መጽሐፍ የሆነ ህዝብ ነው። ይህንን ህዝብ አልተማረም ብሎ ንቆ ተማርኩ የሚለው ምን አደረግ? አገር ለማፋጀት ጦርነትን የሚለፍፍበትን እውቀት ነው የሚመካበት? ትህትህና ፍቅር መቻቻል ትእግስት የሌለበት ትምህርት ለምን ሙልጭ ብሎ አይጠፋም። ሰላም ይምጣ እንጂ ለምን አገሪቱ በጣቱ በሚፈርም  የአገር ሽማግሌ አትመራም። በእውነት የአገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ መንግሥት አወቃቀር ውስጥ ስፍራ ሊሰጣቸው አይገባም ትላላችሁ? እነርሱ እኮ እኛ በእስክርቢቶ የማንፈታውን በጭራ በክላሽ የማንፈታዎን በከዘራ በወታደራዊ የማእረግ ኮከብ ብዛት የማንፈታውን በለበሱት ነጭ ነጠላ ተጀቡነው የሚፈቱ። ከምላሳቸው ርዝመት ይልቅ የሚበልጠውን ዠርጋጋ ጢማቸውን እያሻሹ የሚያፈልቁት የጥበብ ቃል ትውልድን ይመራል። ፊደል የቆጠሩ ልጆች  ያልተማሩ ወላጆቻቸው የሚነግሩአቸውን እየሰሙ ደብዳቤን እንደሚጥፉላቸው ተማርኩ የሚለው ትውልድ ከነዚህ አባቶች እግር ስር ቁጭ ብሎ እነርሱ የሚሉትን እየጻፈ የነርሱ ጣፊ ብቻ ቢሆን ይሻላል። የአገር ሽማግሌዎች ለጥበባቸውና ለምክራቸው እውቅና ተሰጥቶት በፓርላማም ሆነ በተለያዩ የማህበራዊ ደርጅቶች ውስጥ ስፍራ ሊሰጣቸው ይገባል። ህዝቡም ቢሆን በማያውቀው የምእራባውያን ጉራማይሌ ቋንቋ እየለፈፈ ጆሮውን ከሚያደነቁረው ይልቅ ከራሱ የሆኑት የርሱን ነገር የሚያውቁት ነገርን በምሳሌ በሚያቀርቡለት በአገሬው ሽማግሌው ቢመራ ይመርጣል። ከሚከፍለው ግብር ለነርሱ ቢቆረስላቸው ደስ ይለዋል። ለወጭውም ቢሆን የሚሻለው ለነርሱ የሚከፈለው ነገር ነው። ህሊና ስላላቸውና ደግሞም ያለኝ ይበቃኛል የሚሉ ስለሆኑ በሙስና ህዝቡን የማማረራቸው ነገር ካሁኑ ያነሰ ባይሆን ምን አለ በሉኝ።

ያለፉት መንግስታትም ሆነ አሁን ያለው መንግሥት ችግር ውስጥ ችግር ውስጥ የሚወድቀው የነዚህን በሳል ሽማግሌዎች ምክር ስለማይሰማና እነርሱን ንቆ ከምእራባውያን ጎረምሶች ስለሚማር ነው።  ስለዚህ አሁን የተማረ ነው ብለን ጦርነት የሚያውጀውን ከምንሰማ እነዚህን ልበ ሰፊዎች እንስማ መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ የሚደረገው ትግል ለአገሪቱ አይጠቅምም የተሻለ መንግሥት ለማግኘት የግድ መገልበጥ የለብንም መልካሙን ይዘን መታረም የሚገባውን ማረም መንግሥትን መለወጥ ነው። መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም። እየተሰሩ ያሉት ስህተቶች ሁሉ እንዲታረሙ ነው መስራት ያለብን። ይህ ደግሞ ጫካ መግባትን አይጠይቅም። በዚህ መንግሥት ደግሞ በቁማችን የሚያስገባን በርም ባይኖር ጎንበስ ብለን መግባት የሚያስችለን በር አለ። በር ካጣንም በመስኮት እንገባለን እንጂ ቤቱን አናቃጥልም። ቤቱን ካቃጠልን ወዴት እንገባለን? ምናልባት የሚደረጉትን ብዙ ግፎች የሚያዩ ሰዎች እንዴት መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም ይላል? ብለው ሊሞግቱኝ ይችሉ ይሆናል። እኔ ይህንን ስል ለተጎዱት ወገኖች አለማዘኔ ወይም ልጅዋን በጥይት ላጣችው ልጅ ከልብ አለማዘኔ አይደለም። ይህ ግፍ ነው መንግሥት መጠየቅ መከሰስ አለበት። ተጠያቂ የሆኑ ወገኖች ሁሉ መጠየቅ አለባቸው። መንግሥት ግን መፍረስ የለበትም። በነዚህ ምክንያቶች መንግስር መፍረስ አለበት ብለው የሚለፍፉትና የጦርነት እምቢልታ የሚነፉት ወገኖች አብዛኛዎቹ የሚኖሩት በአሜሪካና በአውሮፓ ነው። እውነት ሰው በግፍ ስለሞተና ፍትህ ስለተጓደለ መንግሥት በጦርነት መገልበጥ አለበት ብለው የሚያምኑ ከሆነ የሚኖሩባትን የአሜሪካን መንግሥት ለመገልበጥ ጫካ መግባት ነበረባቸው። አፍንጫቸው ስር ሰው በግፍ ሲገደል ሲጨቆን የገደለው ነጻ ሲለቀቅ ነው የሚውለው። አንድ ሰው ሲጋራ ሸጥክ ተብሎ በጠራራ ጸሐይ በከተማ አደባባይ መተንፈስ አቃተኝ እያለ እየጮኸ በፖሊስ አንገቱን ታንቆ ሲሞት እያዩ መንግሥትን ሊገለብጡ አልወጡም። አሜራካዊ ሆነዋል ዜጎች ናቸው ከኢትዮጵያ ይልቅ ለአሜሪካ ይገዳቸዋል። ዜግነታቸውን ሲቀይሩ አሜሪካን ከጉዳት ለመጠበቅ ቃል ገብተው ነው የቀየሩት። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ትንፍሽ አይሉም። እንዲያውም ለሰብአብዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉት እነዚህ በሚኖሩበት ከተማ ጥቁርም ሆነ የሌላ አገር ዜጋ ተገድሎ ወይም ፍትህ ተጓድሎ ሲያዩ ከአገሬው ህዝብ ጋር ለሰልፍ አይወጡም። ለምን? እዚህ የሞተው ሰው አይደለም? ይህንን ያደረገው የአሜሪካ መንግሥት አይጠየቅም? ለነርሱ የአሜሪካ መንግሥት ፍጹም እንከን የሌለበት ነዋ እንዴት ይጠየቃል። እዚሁ እፊት ለፊታቸው ሰው በግፍ እየተገደለ ምንም ሳይመስላቸው ከኢትዮጵያ የሐሰትና ያልተጣራ ወሬ ሲያነፈንፉ ይውላሉ። እውነተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቢሆኑ ግን ሰው ባለበት አገር ሁሉና በሰው ልጅ ላይ በሚደርስ ግፍ ሁሉ ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ነበር። እንደ ቼ ጎቤራ በሰው አገር ለሰው መብት ይጋደሉ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጋራን እያዞረ በመሸጥ የእለት ጉርሱን የሚያገኝ ሰው አይገደልም። ውለታ ቢስና ወገነተኛ ሆነን አባረርናቸው እንጂ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት አርከበ ዕቁባይ መልካም መሪ ነበሩ። እንዳሁኑ ባለስልጣኖች ዓይናቸው ሁሉ በሀብታም ነጋዴዎች ቁጥጥር ስር የዋለ አልነበረም።  ለሊስትሮ ጠራጊዎችና ለሱቅ በደረቴዎች ኮንቴነሮችን በማቅረብና በማበረታታት ያደረጉትን አስተዋጽኦ አስታውሳለሁ። እነዚህን በጥቃቅን ስራዎች በመሰማራት የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙትን ፖሊስ አይደለም የላኩባቸው። የተሻለ እገዛ ነው ያደረጉላቸው። ምን ያደርጋል ለእንደዚህ አይነቱ ሰው የሚሆን ልብ የለን። ወገንተኝነት፣  የፖለቲካ ጎጠኝነት፣ አሸነፈንና ይህን ሁሉ መልካም ሥራ እያየን ከወንበራቸው አነሳናቸው። ለማለት የተፈለገው በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የምናየው የአስተዳደር ጉድለትና ኢፍትሃዊነት በአሜሪካም አለ። ያውም ባይብስ ነው? መቸም እዚህ መጥቶ ያላየ የሐሰተኞችን ዲስኩርና ተመርጦ የሚቀርበውን የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ብቻ ለሚከታተል ሰው ይህ እውነት ላይመስለው ይችላል። እውነቱ ግን ይህ ነው። በምኖርበት ከተማ አጠገብ አንዲት ጥቁር ሴት በቅርቡ የደረሰባትን አስታውሳለሁ። ፍሬቻ ሳታበሪ መስመር ቀየርሽ ብሎ ፖሊስ አስቆማት። ፖሊሱ ውጭ ቆሞ  ትኬት እየጻፈ ሳለ እርስዋ መኪናዋ ውስጥ ሆና ትንባሆ ታጨስ ነበር። በህጉ ውስጥ ፖሊስ አጠገባችሁ ቆሞ ሳለ ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው የሚል የለም። ፖሊሱ ግን እንዳልተከበረ ተሰማውና ጎትቶ በኃይል አስወጣትና ወደ እስር ቤት ወስዶ አንድ ክፍል ውስጥ ቆልፎባት ሄደ። የድረሱልኝ ጥሪ ብታሰማ ሰሚ ያጣችው ሴት ከዚህ ሁሉ ብሞት ይሻላል ብላ ራስዋን አንቃ ገድላ ተገኘች። ይህ ግፍ አይደለም? ግፍ ነው ነገር ግን ጉዳዩ ወደ ፍትህ ተመራ እንጂ ፕሬዚዳንት ኦባማ አልተነሱም ሪፐብሊካንም ፓርቲ ከስፍራው አልለቀቀም። በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ጉድለት በተፈጸመ ጊዜ ሁሉ ጦርነትን የሚያውጁት የኛው ጀግኖች ግን የሚኖሩት እንደዚህ አይነት ኢፍትሃዊነት በገነነባት አገር ነው። መኖር ብቻ ሳይሆን በየእለቱ እያሞካሽዋት ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ እንድትሆን ይመኛሉ። እውነቱን ለመናገር አንዱ ሁላችንም የወደቅንበት ጉድጎድ የኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ንቀንና ትተን የሌላውን መመኘታችን ነው። እስካሁን ከውጭ ያልተበደርነውና ያልተመኘነውን አየሩን ብቻ ይመስለኛል። የፖለቲካ መሪዎቻችንን መናናቅና አለመቀባበል ሁሉ የሚመጣውም ከዚህ ነው። በአገር ውስጥ ያለውን የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ በማድ ቤትና በጓሮ በር እያስተናገድን የውጭ አምባሳደሮችንና ፖለቲከኞችን በቀይ ምንጣፍ በክብር በፊት ለፊት በአጀብ እናስገባለን። ብቻ ከውጭ መጣ ይባል እንጂ ከዚያው ከድሮው ግዛቶቻችን ከሱዳን ከጅቡትም ከሱማሌም የመጣ መሪ ከኢትዮጵያውያኑ የፖለቲካ መሪዎች በተሻለ ክብር አቀባበል ይደረግለታል። ምናለ ለአገሬው ፖለቲከኞች የራት ግብዣ የክብር አቀባበል ቢደረግ? መግባባቱም ውይይቱም የሚጀመረው እኮ ከዚያ ነው። ለዚህ ግን ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ብቻ ነው ማለት አይደለም። እኔ ቤተ መንግሥት የምገባው መንግሥት ሲወድቅና እኔ ስሾም ብቻ ነው ብለው ለራሳቸው ቃል ኪዳን የገቡና ከስልጣን በቀር ሌላ ማህበራዊ ግንኙነት ጨርሶ የማይታያቸው ቢጋበዙም የማይመጡ ጠባብ ፖለቲከኞች እንዳሉም መርሳት የለብንም። ስለዚህ ይህንን መከባበርን የተሞላ ግንኙነት ለማድረግ ከሁለቱም የሚጠበቅ ነገር አለ። እንዲሁ ከማን አንሼ ማን ከማን ይበልጣል በሚል የፉክክር መንፈስ ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ስልጣኑን እስከያዘ ድረስ የነርሱም መንግሥት መሆኑን እውቅና በመስጠትና በማክበር ሊቀርቡ ይገባል። እኩል የሚሆኑት ለስልጣን በሚወዳደሩበት ጊዜና እንደ አንድ ዜጋ እንጂ ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ እነርሱ ፓርቲ እርሱ መንግሥት መሆኑን መርሳት የለባቸውም። ስለዚህ ይህ የኛ የሆነውን እየናቁ የሌላውን ማሞጋገስ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነት አይደለም። ቅኝ ግዛት አለመገዛታችን ይመስለኛል ይህንን የወለደው። ምክንያቱም በነጮች ስር የነበሩና ቅኝ ግዛቱን የቀመሱ አገሮችና ዜጎች የነጮች የሆነውን አይወዱትም። ተገደው ቋንቋቸውን ስለጣሉና እንግሊዘኛ ተናጋሪ ስለሆኑ እንጂ የራሳቸውን ቢያገኙት እጅጉን ነው የሚመኙት። ጥቁር አሜሪካኖች ሁልጊዜ የሚገርማቸው የኛ አገራችንን ጥለን አሜሪካ መሄዳችን ነው። ሁልጌዜ አገርህን ጥለህ ለምን መጣህ ይሉናል። ለምን እነርሱ አገራቸውን ጥለው አሜሪካዊ የሆኑት ወደው ሳይሆን ተገደው ነው። አገራቸውን ቢያውቁ ወይም እንደኛ አገሬ የሚሉት ቢኖራቸው ኖሮ እዚያ ለዘመናት ካሰቃያቸውና አሁንም በሚደረገው ውስጣዊ አድልዎ ባርነታቸውን እያስታወሱ መኖር አይፈልጉም። ችግሩ ግን የመጡበትን አገር ቋንቋቸው ምን እንደነበረ በጭራሽ አያውቁም። በስማቸው የጥንት አገራቸውን እንዳያውቁ እንኳ ስማቸው ተቀይሮ ጆርጅ ጀምስ ዋሺንግተን ዊሊያም ወዘተ ተብሎ በገዢዎቻቸው ስም ተቀይሮአል። ስለዚህ የኛ በፈቀደኝነት ስማችንን ዜግነታችንን መኖሪያችንን ቀይረን መምጣትና የኛ የሆነውን ሁሉ ጥለን የሌላውን ለመያዝ መሮጥ እጅጉን ያስገርማቸዋል። ከገብረ ማርያም ከወልደ ሚካኤል ከግርማ ወደ ጀምስ ጃክ ወዘተ ስምን መቀየር ስልጣኔ የመሰለው አዲሱ ትውልድ ስሙን ሲቀይር ይውላል። የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ራሳቸው ደርግ ስልሆኑ ለምን ደርግን እንደተዋጉ ይገርመኛል። ለነገሩ አሁን ሲገባኝ ደርግን ለመጣል ሳይሆን ከኢትዮጵያ ለመለየት ነው የታገሉት። በአገራቸው ላይ በሚከተሉት ፖሊሲ መልካም መሪ እንዳልሆኑ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። ብዙ ክርስቲያኖችን  አስረዋል። የአገሪቱን ወጣት ከአገር አስወጥተው በትነዋል ለወጣቱ ያዘጋጁለት ነገር ቢኖር ወታደራዊ ካምፕ ብቻ ነው። ስለዚህ ህይወቱን እየከፈለ ወደ አራቱም አቅጣጫ ሲበተን ግድ ያላቸውም አይመስልም። ይህም ሁሉ ሆኖ በአንድ ነገር ግን ሳላሞግሳቸው ባልፍ ህሊናየን የወቅሰኛል። ይኸውም ስለውጭ መንግስታት ያላቸው አስተሳሰብ ነው። የውጭ መንግስታትን ከኢትዮጵያ መንግሥት የበለጠ የተረዱአቸው ይመስለኛል። ለሀምሳ አመት በጣልያንና በእንግሊዝ መገዛታቸው ይህንን በሚገባ ያስተማራቸው ይመስለኛል። ስለዚህ በውጭ እርዳታ ከሚገኝ ቀልጣፋ ብልጽግና ይልቅ ድህነትን መርጠዋል። ምክንያቱም በእርዳታና በሰብአዊነት ካባ ተጀቡነው የሚገቡት ተኩላዎች ስንት ጊዜ እንደነከሱአቸው ያውቃሉና ነው። ስለዚህ አገራቸውን ለነዚህ ተኩላዎች ላለመክፈት እንዲህ መጠንከራቸው ከባርነት ይልቅ ድህነትን እንደመረጡ ያሳያል። አሁን ሲገባኝ ለካ እውነተኛ ነጻነታቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከምእራባውያኑ ነው። ይህ ከሆነ ማክበር ያለባቸው አመታዊ የነጻነት በአል ከኢትዮጵያ የተለዩበትን ሳይሆን ከነዚህ ክፉ የውጭ ኃይሎች ነጻ የወጡበትን ሊሆን ይገባል። ይህም ቀን ከአራተኛ ክፍል ያለፈ እንዳይማሩ በር ዘግቶ ከተማቸውን ብቻ በማሳመር የባርነትን ጥሩ መልክ አሳይባቸዋለሁ ብሎ የቅኝ ግዛት ሰርቶ ማሳያ ሊያደርጋቸው ብዙ ከጣረው ከጣልያንና ከአጎቱ ከእንግሊዝ ነጻ ወጥተው ወደ እውነተኛ አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበትን ቀን  ነው።  ይህም መልካም የነጻነት ቀን  194 በመሆኑም እኚህ ሰው ለውጭ አታላዮች በር አልከፍትም ከእጅ አዙር ቅኝ ተገዥነት ይልቅ ድህነት ይሻለኛል ብለው እስካሁን ቆመዋል። ኢትዮጵያ እንደርሳቸው በርዋን ትዝጋ ባይባልም ሁሉን ነገር ከውጭ ለማስገባት የሚደረገው ርብርብ ግን ቢቆም ይበጃል። ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ነገሮች ከውጭ ይምጡ እንዴት ባህልና ታሪክ ከውጭ ይገባል? እኔ እስከዛሬ ያልተመለሰልኝ ጥያቄ ኦሮምኛ በላቲን ቋንቋ እንዲጻፍ መደረጉ ነው። ለመሆኑ ለኦሮሞ የአማርኛ ፊደል ይቀርበዋል ወይስ ላቲን? ይህ በእውነት የሚያሳዝንና ገና ቀና ማሰብ አለመጀመራችንን የሚያሳይ ነው። ይህ ምሳሌ ይሁነን ብየ እንጂ አጠገባችን ያለ ኢትዮጵያዊ ምሁር ኢትዮጵያዊ ፓለቲከኛ ተጠልቶና ተንቆ ሁሉም ከውጭ ፖለቲከኞች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያደርገው ሩጫ በላቲን የመጻፍን ያህል ነው።

ህዝቡን የሚጎዱ ነገሮችን እያስወገዱ የሚጠቅም ስርአት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ለውጥ ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም መንግሥት ጥሩ ያልሆነውን ነገር ለመለወጥ ፈቃደኛ ሆኖ ሳለና ህዝብን ለመስማት ጆሮ ከፍቶ እያለ መንግሥትን ለመገልበጥ መጣርና ካልገለበጥኩ አልረካም ማለት ችግሩ ሌላ መሆኑን ያሳያል ሌላ ስንል ምን? ጥላቻ ጠባብነት እልከኝነት ያለውን እየጠበቅን የሌለውንና  የጎደለውን ለማግኘትና ለማሻሻል መጣር ልማትን ማምጣት ያለውን የለማውን የተሰራውን ከመጠበቅ ነው የሚጀምረው ያለውን አፍርሶ ከዜሮ መጀመር ኢትዮጵያን አይጠቅምም የማንወዳቸው ሰዎችም እንኳ የሰሩትን መልካም ነገር ለመቀበል ልባችን ሰፊ መሆን አለበት። ሁሉ ነገር ከከረረ ጥላቻ ከጀመረ መልካም ውጤት የለም።

የትክክለኛ ዜጎች ድርሻ

በአሁኑ ሰአት በከረረ ጥላቻ የተያዙና ስርአቱ ካልፈረሰ የማያቆሙ ስርአቱ እንዲፈርስ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ

በሌላ በኩል ደግሞ በአስተዳደር በደል የተበደሉ መንግስታቸው መልካም አስተዳደር የነፈጋቸውና ያንን መልካም አስተዳደር የሚፈልጉ አሉ።

ስርአቱን በኃይል ከመጣል በቀር ሌላ አላማ የሌላቸው ሰዎች እነዚህ በመንግስታቸው ላይ የአስተዳደር በደል ቅሬታ ያለባቸውንና ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንገድ እያሰሙ ነገሮች እንዲስተካከሉላቸው የሚጠይቁትን ሰዎች ከነርሱ ጎራ በማሰለፍ የበለጠ ተፅዕኖ ለመፍጠር ወጥመዳቸው ውስጥ ለማስገባት ቀን ከሌሊት እየጣሩ ነው።

በመጀመሪያ ለነዚህ አገራቸው ኢትዮጵያ በሰላም እንድትኖርና መንግሥት በህዝቡ ላይ በደል እያደረሱ ያሉትን አሰራሮች በማስተካከል ልማቱን ከሞላ ጎደል ሚዛናዊ ለማድረግ እንዲሰራላቸው ብቻ ለሚፈልጉ ዜጎች ምክሬ

በመጀመሪያ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥትን እየተቹና እየወቀሱ እየሞገቱም አስተዳደራዊ ጉድለቶችንና ማህበራዊ ኑሮን ለማሻሻል የሚደረግን ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የተከፈተ በር አለ። ይህን ማድረግ የማንችልበትና ድምጻችንን በጭራሽ ማሰማት የማንችልበት ጊዜ እንደነበረ የሩቅ ትዝታ አይደለም። ምናልባት አንዳንድ ሰዎች እንደሚያናፍሱት በደርግ ጊዜም ሰው ተገድሎአል አሁንም እየተገደለ ነው ይሉ ይሆናል። በቅንነት ከፈረድን ግን ሁለቱ በፍጹም የማይመሳሰሉ ነገሮች ናቸው። እውነት ነው በምንም ሁኔታ ቢሆን ሰው መሞት የለበትም። በዚህ እንስማማና ነገር ግን አንድ ሰው መንግሥት የሚያደርሰውን በደል በሰላማዊ መንገድ ለመቃወምና ድምጹን ለማሰማት ብቻ ወጥቶ ስለገባ ሲገደልና አንዱ ደግሞ ተቋማትን በማፈራረስ በማቃጠል በጦር መሳሪያ በማውደም እንደዚሁም በዜጎች ላይ አደጋ በማድረስ ላይ ስለተገኘ ያንን ለማስቆም በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ሲገደል አንድ አይደለም።

በነፍስ ግድያ የተከሰሱ ሰዎች ሁሉ በአንድ አይነት ዳኝነት እንደማይከሰሱ ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ በአሁኑ ሰአት መንግሥት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በሰላማዊ መንገድ ለመቃወም የሚቻልበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ። የዚህ አይነቱ ትግል በጣም አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም በደም መፋሰስ ከሚመጣ ነገር ግን የተሻለ ነው። በደም መፋሰስና አላስፈላጊ የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎ በአንድ ቀን ከሚመጣ ለውጥ በሰላማዊ የህዝብ ትግል በ ዓመታት ውስጥ የሚመጣ ለውጥ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ሰላማዊው ትግል አገሪቱ የደረሰችበትን የልማት ደረጃ ሳያፈራርስ ወደ ሌላ ልማት የሚያሻግር ስለሆነ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ሄዶ የሚጀመር አይደለም። ስለዚህ ይህንን ሰላማዊ ትግል የመረጡ ሰዎች ናቸው ሊደገፉ የሚገባቸው። ዜጎች ሁሉ የተሻለች ኢትዮጵያን ማየት ከፈለጉ በዚህ የትግል ጎራ በመሰለፍ መንግሥት መልካም ሲሰራ ይበል በማለት ሲያጠፋና በደል ሲደርስ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዞ የድምጽን ጉልበት በመጠቀም ነው አገርን ማልማት የሚቻለው። ብዙ ጊዜ መንግሥትን የመገልበጥ አላማ ብቻ ይዘው በሚንቀሳቀሱ ዜጎች የሚታየው ነገር ስሙ ሰላማዊ ሰልፍ ይባል እንጂ መልኩ እንደ ስሙ አይደለም። ቤት እያቃጠሉ ሰው እየገደሉ ሰላማዊ ሰልፍ እንዴት ይባላል?

በአሁኑ ሰአት ግን አንድ ሰላማዊ  ዜጎች ሁሉ ሊያዩት የሚገባ የታዘብኩት ነገር። መንግሥትን በኃይል ገልብጦ የራሳቸውን ምኞት ለመፈጸም የሚጥሩት ወገኖች ይህንን አፍራሽና አገርን የማይጠቅም ምኞታቸውን ለማሳካት ቀን ከሌሊት ሲሰሩና አንዳንድ ጊዜ መንግሥትንም ሲያስጨንቁ እያየን ሰላማዊውና ከነርሱ ጋር ያልተሰለፈው ዜጋ ግን ተመልካች ሆኖ እያየ ያለ ይመስላል። በጥቂቶቹ ጦርነት ፈላጊዎች ጎራ የሚሰማው ጩኸት የአገራቸውን ሰላምና ልማት ከሚፈልጉት ዜጎች በእጅጉ የበለጠ ይመስላል። ጦርነት ፈላጊዎቹ ጥቂቶች ከሆኑ ጩኸታቸው ለምን አየለ? የሚል ጠያቂ ይኖር ይሆናል። የኔም ጥያቄና ትዝብት ይህ ነው። መቸም በራሱ አንደበት ከሚጮህ ብዙ ህዝብ ይልቅ በከባድና በሚያስተጋባ ዘመናዊ ድምጽ ማጉያ የሚጮህ ሰው የበለጠ ይሰማል። እንደሚመስለኝ ነገሩ እንደዚህ ነው። አንደኛ እነዚህ ጦርነት ናፋቂዎች እንቅልፍ በማያስወስድ ዘረኝነትና ጥላቻ የተሞሉ በመሆናቸው ጩኸታቸው ሌሊትም ቀንም አያቋርጥም። ሁለተኛ ያለውን የመገናኛ ብዙኃን መረብ ሁሉ በተቻላቸው መጠን ለዚህ ክፉ አዋጃቸው ይጠቀማሉ። በነርሱ ዘንድ ሞያ  በልብ ነው የሚል ነገር የለም። ምንም ሞያና ሰርቶ ማሳያ ስለሌላቸው ስራቸው ጦርነት ማወጅና ሐሰትን መርጨት ብቻ ነው። ያላቸው መሳሪያ ይህ ብቻ ስለሆነ ሁልጊዜ የሚተኩሱት ይህንን የሐሰት ፕሮፓጋንዳና የጦርነት አዋጅ ብቻ ነው። የሚገርመው ይህንን አዋጃቸውን የሚያዳምጠው ሰው ብዛት ነው። ይህ ለምን እንደሆነም ትንሽ የራሴን ምርምር ቤጤ አድርጌ ነበር። ያገኘሁት ምክንያት ለብዙዎች የተሰወረ ይመስላል። ይኸውም የሰው ተፈጥሮ የሚገድለውን መውደዱና መልካሙንና የተፈቀደለትንት ትቶ የተከለከለውን ለመስማትና ለመንካት የተቃኘ በመሆኑ ነው። ገና ከኤደን ገነት የጀመረው የናታችን የሄዋን ባህርይ ብዙዎቻችንን እየተከተለ ያሳድደናል። የገነትን ዛፍ ሁሉ እንዲበሉ ተፈቅዶላቸው ሳለ ከተከለከለችው  ከአንዲት ዛፍ ላይ አይናቸውን ማንሳት አልቻሉም። የዚያን ጊዜው የሞት መልእክተኛ ዲያብሎስ የሐሰት አዛኝና ለነርሱ ተቆርቋሪ መስሎ ሐሰትን ሰበካቸው። አመኑት ያችንም ዛፍ በሉ ሞቱም። ዛሬም እንዲሁ ነው። ትውልዱ ሰላምን ከሚሰጠው ኑሮውን ከሚያሻሽልበት በሰላምና በፍቅር በመቻቻል ከሚኖርበት አዋጅ ይልቅ  እንደ እባቡ አዛኝ መስለው ወደ ሞት የሚነዱትን የሚወድ ይመስላል። ጆሮው መልካም ዜና ከመሳብ ይልቅ ክፉ ዜና መሳብ ይቀናዋል። ክፉ ዜና ከሆነ ሐሰትም ይሁን እውነት በፍጥነት ስቦ ያስገባዋል። እስኪ ራሳችሁን በዚህ መዝኑ። ሆስፒታል ተከፈተ፣ መንገድ ተሰራ፣ አገር ለማ፣ ወዘተ የሚሉት ወሬዎች ናቸው ልባችሁን ቶሎ የሚስቡት ወይስ ሰው ተገደለ፣ ሆስፒታል ፈረሰ መንገድ ተደረመሰ ጦርነት ጀመረ..የሚሉት? መልካሙ ዜና የሚስባችሁ ከሆነ በእውነት ብጹአን ናችሁ። ብዙኃኑ ግን ሰላም ለማየት ከመርጥ ግርግር ለማየት መርጥን የሚመርጥ ነው። የሰላም ጥሪ ከሚስበው ይልቅ የጦርነት እምቢልታ የሚስበው ይበልጣል። ስለዚህ ሌት ተቀን ደክመው ሆስፒታል መንገድ ትምህርት ቤት ከፍተው የሚያስመርቁትን ሰዎች ንግግር መቶ ሰው ካዳመጠ ያልሞተውን ሞተ ያልተቃጠለውን ተቃጠለ እያሉ ጦርነት የሚያውጁትን ግን የሚሰማቸው እልፍ ነው። መቸም ፍትህ ሲጓደል ሰው ሲበደል አንስማ አንቃወም ማለት ሳይሆን ያንንም ቢሆን በጠቃሚ መልኩ የምናደርገው ከጥላቻና ከጭፍንነት ወጥተን ነገሩን በማጣራትና በሰከነ በጎ ህሊና መፍትሄውን ስንፈልግ ብቻ ነው። አንድ ነገር ተደረገ በተባለ ቁጥር ሳያጣራ ለፍርድ የሚሮጠው ማንነታችን ግን አደገኛ ነው። በእውነት ይህንን ተፈጥሮችንን መጥላትና መሸሽ ያለብን ይመስለኛል።  በመሆኑም ይህንን የሰው ተፈጥሮ የነፈስ አቅጣጫ ተከትለው ክፉ መርከባቸውን ለሚቀዝፉ ይህ የሰው ተፈጥሮ  ደጋፊ ነፋስ የሆነላቸው ይመስለኛል። እንግዲህ ሰላምን ፈላጊውና በሰላማዊ መንገድ ለውጥን ለማምጣት የሚታገለው ትውልድ ሰላሙን እያደፈረሱ ወዳላስፈላጊ ብጥብጥ የሚጎትቱትን እነዚህን ክፉዎች ለመመከት ድምጻቸውን ሊውጥና ሊያሸንፍ በሚችል ጪኸት ድምጹን ማሰማት ያለበት ይመስለኛል። ሞያ በልብ ነው የሚለው ኢትዮጵያዊ ባህል የማይሰራበት ዘመን መምጣቱን ማወቅ ይገባናል። ዘመኑ የመረጃ ዘመን ስለሆነ በልብ ያለውና የተሰራው ሞያ  በመረጃም ለህዝቡ መውጣት አለበት። ወደ ምእራቡ አለም ስመጣ ያስተዋልኩት አንዱ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የመልካም ባህልና እሳት መግለጫ የሆኑ አንዳንድ ነገሮች በምእራቡ አለም ሌላ ትርጉም እንደሚሰጣቸው ነው። ለምሳሌ በአገር ቤት ዝምተኝነትና አንገት ደፊነት የጨዋ ልጅ ምልክት ሲሆኑ በምእራቡ አለም ግን እንደዚህ አይደለም። ትኩር ብሎ እያየ መልስ የማይሰጥና አንገቱን የሚደፋ ሰው እንደ ትሁት ሳይሆን እንደ ሐሰተኛ እንደ ትኩስ ሽሮ ቱግ ቱግ እያለ የማይናገር ሰው እንደ አባይ ነው የሚታየው። እነዚህ ሐሰትን እየዘሩ ጦርነትን የሚያውጁት ክፉ ሰዎችም የዚህን የምእራባውያንን ልማድ በደንብ እየተጠቀሙበት ነው። አፍ እንጂ ስራን ለማይመዝኑት ምእራባውያን ፖለሪከኞች በደንብ አድርገው የጋገሩትን የሐሰት ወሬ ዳቦ ይመግቡአቸዋል። ከድሀው ህዝብ ጋር ሆኖ ልማትን እያፋጠነና እየደከመ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ስራው ሳይታይለትና ሳይነገርለት  ምእባውያኑ ፖለቲከኞች እዚህ እጓሮአቸው ሆነው በየጠዋቱ ሐሰትን የሚመግቡአቸውን ሰዎች ወሬ በመስማት የኢትዮጵያን መንግሥትና ህዝብ ሲወቅሱ ይታያል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ በየጠዋቱ ለምእባውያኑ ፖለቲከኞች የስራውን ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ባይኖርበትም በዚህ ሐሰት ቀድሞ እየፈረጠጠ የሰውን ጆሮ በሚያበላሽበት የኢንፎርሜሽን ዘመን ግን በዚህም አቅጣጫ ቀድሞ መገኘት ብዙ የዋህ ዜጎችን የሐሰት ሰለባ ሆነው ከክፉዎች ጋር እንዳይሰለፉ ያድናል። ስለዚህ መንግሥትም ሆነ ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሳላም ድምጹን አጉልቶ በማሰማት የሐሰትን ድምጽ መሻር ያስፈልገዋል እላለሁ። በዚህ ጉዳይ ዝምታ ወርቅ ነው፣ ዝም አይነቅዝም የሚሉትን አባባሎች ሳይሆን ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል የሚለውን ብንመርጥ የተሻለ ነው። ታዋቂው የወንጌል ሰባኪና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ከተናገራቸው አባባሎች ሁለቱ ለኛ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እንድትለማ ለምንፈልግ ዜጎች ጠቃሚዎች ይመስሉኛል። አንደኛው «የአንድ ሰው ትክክለኛ መለኪያ በምቹ ጊዜ ያለው አቋም ሳይሆን በችግርና በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የሚወስደው አቋም ነው።» የሚለው ሲሆን በአስቸጋሪ ጊዜ ልንይዘውና ልንገልጸው ስለሚገባ አቋም የሚናገር ነው። ሁለተኛው ደግሞ « እጅግ የከፋውና አሳዛኙ ነገር በክፉ ህዝብ አማካኝነት የሚደርሰው ጭካኔና ጭቆና ሳይሆን የመልካም ሰዎች ዝምታ ነው።» የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ህብረተሰብንና አገርን የሚጎዳ ነገር ሲደረግ ከንፈርን በመምጠጥ ብቻ ሀዘናችንን የምንገልጥ እንዲሁ ጥግ የያዙ ታዛቢዎች እንዳንሆን የሚሞግተን ነው። ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚያደርሳቸውን አስተዳደራዊ ጉድለቶች ሙስናና ኢፍትሃዊ ፍርዶች የምንቃወምና ድምጻችንን ማሰማት ያለብን ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ህብረተሰብ ከህብረተሰብ እንዲበጣበጥ ከዚያም አልፎ ተርፎ እስላማዊን መንግሥት ለለመስረትና ኢትዮጵያን እንደ አረብ አገራቱ በእስልምና ህግ የምትመራ አገር ለማድረግ የጦርነት አዋጅ የሚያውጁትን ከመንግሥት ጎን ሆነን ልንመክታቸው ይገባል።   የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የሆንኩት እኔ ይህንን የዜግነት ድምጼን ሳሰማ ለመጀመሪያ ጊዜየ ነው። በዚህ መንግሥትም ሆነ በፓርቲዎች ውስጥ ምንም አይነት ንክኪም ሆነ ተሳትፎ ኖሮኝ አያውቅም።  አሁን ካለው የመንግሥት አሰራር ጋር መቶ በመቶ በሆነ ሁኔታ አልስማማም። በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለች በጦርነት በደቀቀችና ብዙ ዜጎችዋ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ በሚኖሩባት አገር የሙስና እንዲህ መንሰራፋት እጅግ የሚያሳስበውና በሙሰኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ የምፈልግ ነኝ። ይህ መንግሥት ለኔም ሆነ ለቤተሰቤ አደረገው የምለው ጥሩ ነገር የለም። አንድ የስጋ ወንድሜ የዛሬ አስራ አምስት አመት አካባቢ የቀበሌ ቤት ለማግኘት አመልክቶ አምስት መቶ ብር ጉቦ እንዲሰጥ በመጠየቁና ህሊናው ስለማይፈቅድለት እንደማይሰጥ በመናገሩ ቤቱን ሳያገኝ ቀርቶአል። ይህ ወንድሜ ይህ መንግሥት ከገባ ከሃያ አመት በኋላ ሳገኘው በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤት የሌለው ሆኖ ነው ያገኘሁት። በተለያዩ ዜጎች ላይ በሚደርሰው የፍትህ መጓደል መዘግየትና ማጣት እጅግ አዝናለሁ። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን መንግስታዊ አሰራርን ማሻሻል እንጂ ማፍረስ መልካም እንዳልሆነ አምናለሁ።  መንግሥትን የምመዝነው ግን ለኔ ካደረገልኝ ወይም ካላደረገልኝ ነገር አንጻር ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ካመጣው ለውጥ አንጻር ነው። በየትኛው መንግሥት ቢሆን የሚጎዱ ፍትህ የሚያጡ ሰዎች መኖራቸው የማይቀር ነው። ሆኖም መንግሥት መመዘዘን ያለበት ከአጠቃላይ የአገሪቱ ገጽታ አንጻር እንጂ ከኔ ወይም ከጥቂት ግለሰቦች አንጻር አይደለም። ይህንን ምንም ያላደረገልኝን መንግሥት ነው መሻሻል እንጂ መፍረስ የለበትም የምለው ያለሁት። አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረግሁላት በል የሚለው የኬኔዲ አባባል ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ስሜት ይመስለኛል። ጦርነት ክፉ ነው። ይህንን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው ይገባል። ሁሉ ነገር መሻሻል ያለበት በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው። በተለይ አንድን ብሄር ከሌላው ብሄር   የዚህ   ይህ ጉዳይ እኮ የመንግሥትና የነዚህ መንግሥትን በኃይል ለማፍረስ የሚጥሩት ሰዎች ጉዳይ  ብቻ አይደለም። ጥፋቱ ሲመጣ እኮ ሰላማዊው ዜጋ ነው የሚጎዳው። ስለዚህ እነርሱ በሙሉ አቅማቸው ለማፍረስ ሲተጉ ሰላማዊው ዜጎች የተገነባው ነገር እንዳይፈርስ የሚታገሉት የታለ? ምንም የለም ባይባልም ከአፍራሾቹ አንጻር ሲታይ ግን የሌለ ያህል ይመስላል። በተለይ በውጭው አለም ድምጹ አይሰማም። መንግሥትና የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና የሚወዱ ዜጎች ሁሉ መንግሥትን በድካሙ እየወቀሱና እንዲያስተካክል ጥሪ እያቀረቡ ነገር ግን የአገሪቱን ደህንነትና ሰላም ደግሞ መጠበቅ አለባቸው። ለማፍረስ ከተነሱት ሰዎች ባነሰ ሳይሆን እጥፍ በሆነ መንፈስ አገሪቱን ከመፍረስና ካላስፈላጊ ጦርነት ለመጠበቅ ህዝቡ መነሳት ያለበት ይመስለኛል። የአገሩን ሰላምና ልማት ለመጠበቅ ቆመ ማለት እኮ ከመንግሥት ጉድለቶች ጋር ተስማማ ማለት አይደለም።  ስለዚህ በተለይ በውጭው ዓለም ካሉት ዜጎች ጋር በቅርበት መስራት በመገናኛ ብዙኃን እንደሚገባ መጠቀምና አገር እንድትፈርስ በብዙ ሐሰት ሰዎችን የሚያታልሉትን ሰዎች በእውነተኛው መረጃ ማጋለጥ ያስፈልጋል። እነርሱ ሐሰቱን ሲዘሩ እውነቱን የሚናገር ከሌለ ግን የነርሱ ሐሰት በህዝቡ ዘንድ እውነት ሆኖ ይታይላቸዋል። በዚህ በኩል መንግሥት በውጭ ሚዲያዎች እያደረገው ያለው ግንኙነት በጣም ደካማ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ያሉትን የህብረተሰብ መገናኛ መረቦችን ሁሉ የተቆጣጠረው የነርሱ ሐሰትና ደም የጠማው ፉከራ ብቻ ነው።

የመንግሥት ድርሻ

አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ካለፈው የደርግ መንግስት የተሻለ ነው ባይ ነኝ። ሁልጊዜ ከደርግ ጋር ብቻ ለመነጻጸር መፈለጉና ራሱን ካለፈው አስከፊ ስርዓት ጋር እያወዳደረ እኔ እሻላለሁ እያለ በማስፈራራት ለመግዛት መሞከሩ ግን ደካማ ጎኑ ነው። የድሮው መሪ መንግስቱ ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ቢያነጥፉለት.. አሉ እንደተባለው ምንም ቢነጠፍ የማይረኩ የተወሰኑ ሰዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ያመጣውን የተሻለ ልማትና ሰላም ዓይኔን ግንባር ያርገው ብለው ቢክዱም ይህ መንግስት ያከናወነው ብዙ መልካም ነገር አለ ባይ ነኝ። አጥፍተውም ሆነ ሳያጠፉ በዚህ መንግስት ታስረው የተፈቱት ብዙ ተቃዋሚዎች ቢያንስ ባለመገደላቸው ከደርግ የተሻለ መንግስት እጅ እንደነበሩ ሊያውቁ ይገባል። ያለፍትህ የሞቱት ግን ይህን መንግስት ከደርግ ጋር ቢያመሳስሉ እውነታ አላቸው። መሞት ያው መሞት ነውና።

በኔ እይታ ይህ መንግስት በጣም የተሻለ ስር ሰርቶአል። ብዙ መሰረተ ልማቶችን እያካሄደ አገሪቱን እየቀየረ ነው። የልማት ስርጭቱ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው የሚለው ቢያጠያይቅና ሊስተካከል የሚገባ ብዙ ቀዳዳ ቢኖርበትም ልማት ግን እየታየ ነው። ብዙ ኮሌጆች ተከፍተዋል ብዙ መንገዶች ተሰርተዋል ብዙ ግንባታዎች ተካሄደዋል እየተካሄዱም ነው። አገሪቱ ራስዋን እንድትችል የሚደረገው ትግል ቢያንስ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዞአል ማለት ይቻላል። ጥራቱ እየተጠበቀና ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ እንዲቀጥል ከፍተኛ ርብርቦሽ እንደሚጠይቅ ግን የታወቀ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን እኔ እንደ አንድ ዜጋ ይህ መንግስት አስቀድሞ መስራት የነበረበትን የመሰረት ስራ እንደሚገባ አልሰራም እላለሁ። ከላይ ከዘረዘርኩአቸው መልካም ስራዎች ሁሉ ቀድሞ መሰራት ያለበት ጽኑ መሰረት ነበር። ይኸውም አገሪቱን በትክክለኛና ቢያንስ ሰማንያ ከመቶው በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍን ባገኘ በማያጠያይቅ ህገ መንግስት ላይ መመስረትና የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ ደረጃውን የጠበቀ የፍትህ አሰራር መዘርጋት ነው። ያሁኑ መንግስት ይህንን ሁሉ አላደረገም እያልኩ ሳይሆን ይህ መሰረት ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅና ታሪካዊ በብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ቋንቋዎች የተሸመነችን አገር ሊሸከም የሚችልን መሰረት አልጣለም ባይ ነኝ። የነ ቶሎ ቶሎ ቤት እንደሚባለው በጊዜው የነበረውን የሚታይ የቅርብ ችግር ብቻ ለመፍታት የወጣው ህገ መንግስት ከሃያ አመታት በኋላም እንኳ ብዙ ዜጎች አያውቁትም አይቀበሉትም የኔ ብለው ጥብቅና ሲቆሙለት አይታይም። ይህ የሆነበት ምክንያት የህዝቡ ቀጥታ ተሳትፎ ሳይኖር ህዝቡ እንደሚገባ ሳይረዳው ብዙ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች  ሳይመክሩበትና ስፍራ ሳይሰጣቸው እንዲሁ በፖለቲካ ትኩሳት እየተንተከተኩ በነበሩ ወጣት ፖለቲከኞች ግፊት የጸደቀ ህገ መንግስት ስለሆነ ይመስለኛል። ብዙ ምሁራንና ያገር ሽማግሌዎች የኢትዮጵያን ሁኔታ ከወጣቱ ትውልድ ይልቅ የሚያውቁና የበሰሉ ሰዎች ያቀረቡት ሐሳብ አልተደመጠም። የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር ሊያመጣ የሚችለውን የጎን ችግር አስቀድመው ያዩና ያስጠነቀቁ ችላ ተብለው ነበር። ያ የፈሩትና ያስጠነቀቁት ነገር አልቀረም አሁን በቅሎ አፍርቶ አገር እያስጨነቀ ነው። ቢሰሙ ኖሮ ይህንን ችግር ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ይደረግና ያ እንዳይሆን መከላከያ አጥር ይሰራ ነበር። እንደምገምተው ህገ መንግስቱ እንዲረቀቅ ታላቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰዎችም ቢሆኑ በእድሜና በአአምሮ እየበሰሉ ሲሄዱ በህገ መንግስቱ ውስጥ ያካተቱአቸው አንዳንድ ነገሮች ሳይጸጽቱአቸው የቀሩ አይመስለኝም። ሆኖም አሁንም ቢሆን መንግስት በህገ መንግስቱ ውስጥ ባሉ አንዳንድ አንቀጾች ብዙኃኑ ያልተደሰቱ መሆኑን ካየና የአገሪቱን መፍረስ የሚፈልጉ ሰዎችም ያንን ቀዳዳ እየተጠቀሙ አገር ወዳድ በምመሰል ብዙዎችን ለጦርነት የሚያነሳሱበት ከሆነ በጥንቃቄ ማስተካክል ያለበት ይመስለኛል። ይህ እኮ ህገ መንግስታዊ ሰነድ እንጂ ሃይማኖታዊ ሰነድ አይደለም። ሁለተኛውና ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው በዚህ ህገ መንግስት መሰረት መተግበር ያለበት የፍትህ ስርዓቱ ነው። ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ የረኩና ያለ አድልዎ የተፈረደላቸው ከሆነ ሌላ የዓመጽ መንገድ አይመርጡም። ለሐሰት ቅስቀሳም ጆሮ አይሰጡም።ስለዚህ የፍትህ ስርዓቱን ከወረቀት አልፎ በየእለቱ የህዝቡ ህይወት ትክክለኛውን ፍትህ ለመስጠት የተዘረጋ ሁሉንም የሚያገለግል ሆኖ መመስረትና መጠናከር ነበረበት። ይህም የዳኞችን ከፖለቲካ ገለልተኝነት ማረጋገጥ ፖሊስና ጸጥታ አስከባሪዎች መብትና ግዴታቸውን ተጠያቂነታቸውን ማሳወቅና ማሰልጠንን ይጠይቃል። እኔ እንደታዘብኩት በፌዴራል ወታደሮቹና በብዙ ፖሊሶች ውስጥ የድሮው የወታደራዊ ዓይነት አስተሳሰብ አለ። አንድ ነገር ሲያደርጉ ራሳቸው ዳኛ  ራሳቸው ጠበቃ እንደሆኑ ነው የሚሰማቸው። እነዚህ ጠቃሚ የአገልገሎት ሰራተኞች ከሚሰጣቸው ትጥቅና ማእረግ በፊት የሰብአዊ መብት ትምህርትና ተጠያቂነታቸው ለህዝቡ መሆኑን በማይረሱት መንገድ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ እስኪገባ ድረስ ሊነገራቸው ይገባል። አለዚያ የማያስፈልግ የኃይል እርምጃ እየወሰዱና ዜጎችን እየጎዱ መልሰው መንግስትን የሚያስወቅሱት እነርሱ ናቸው። ስለዚህ ደኞች የመንግስት ቅጥረኞች ሳይሆኑ የህዝቡ እንደሆኑ በማወቅ ህግ አስፈጻሚዎችም ህግ አስፈጻሚዎች እንጂ ራሳቸው ህግ እንዳልሆኑ አውቀው ህዝቡን በትክክል የሚያገለግሉበትን ጠንካራ መሰረት መጣል ነበረበት። ጠንካራና የብዙኃኑን ድምጽ ያካተተ ህገ መንግስት እና ለዜጎች መብት የቆመ የፍትህ ስርዓት የአገሪቱ መሰረት ነው። ይህ መሰረት ህዝቡ መንግስቱን የሚወድ እንዲሆን በሚሰራው የልማት ስራ የሚዋጋው ሳይሆን የሚደግፈው እንዲሆን ያደርገዋል። ከላይ የዘረዘርኩአውን ይህ መንግስት አመጣቸው ያልኩአቸውን ልማቶች ሁሉ ጎዶሎና የሚነቃነቁ የሚያደርጋቸው ይህ መሰረት እነርሱን  ሊሸከምና ህዝቡን ሊያረካ የሚችል ሆኖ ስላልተመሰረተ ነው። መሰረት ዋና ነገር ነው። መሰረት ቤቱን ደግፎ አጽንቶ የሚይዝ ነው። መሰረቱ የሚነቃነቅን ቤት በወርቅና በእምነተ በረድ የሚሰራ ሰው ሞኝ ብቻ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ ልማት ለምን ተሰራ ባይባልና ልማቱ መቀጠሉ መልካም ቢሆንም መንግስት ግን ይህንን የሚነቃነቀውንና የሰራውን ልማት የሚያፈርስበትን መሰረት ማጠናከር አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስቀድመው ሆዱን ሳይሆን ማንነቱንና ክብሩን ነው። በፍትህ መጓደል ማንነቱን እየነኩ ልማት አለ ቢሉት አይረካም። ቆሎ በልቶ ነጭ ጋቢ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄዱ ይህንን የሚመሰክር ነው። ይህንን ማንነቱን አሁን ደርስን መቀየር አንችልም መቀየርም የለበትም። ለሰለጠኑት ለውጭ መንግስታት አልገዛም ብሎ የተዋጋው እኮ ይህ ማንነት ስላለው ነው። የውጭ ኃይላት በየጊዜው የነበሩትን የኢትዮጵያን መሪዎች በተለያየ ስጦታ ሊደልሉ ቢሞክሩም የኢትዮጵያን ህዝብ ግን ሊደልሉ አልቻሉም። መንግስት ይህንን ባህርይ ተረድቶ ፍትህን ማጠናከር አለበት። ፍትህ የህዝብ ምግብ ነው። ዜጎች ዳኛ ፊት ሲቀርቡ መሸማቀቅ የለባቸውም። ዳኛው ለነርሱ የቆመ መሆኑ ሊታይ ይገባል። ዳኞች የመንግስት ደጋፊዎችና ለመንግስት የሚያዳሉ መሆን የለባቸውም። እንዲህ ዓይነቱን ጠንካራ መሰረት ጣልን ማለት ከኛ አልፎ ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ የሚሆን አስተማማኝ ቤት ሰራን ማለት ነው። ልማት ማለት ይህ ነው። ጥሩ ስርአትና መንግስት ወይም አገር ማለት ችግር የሌለበት ማለት ሳይሆን ችግሩን የሚፈታበት ጠንካራና አስተማማኝ የፍትህ ስርአት ያለው ማለት ነው። ይህ ካለ በየጊዜው የሚፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ወደዚያ ሄደው ይጣራሉ። አገርንና ህዝብን የሚጎዱ ነገሮችን የያዙ ሰዎችም እንኳ ቢነሱ መፍትሄ የሚያገኙት በነዚሁ የፍትህ ተቋማት ይሆናል። እስር ቤቶች እየቀነሱ የፍትህ ተቋማት እየጨመሩ ሊሄዱ ይገባል። በዚህን ጊዜ ዜጎችም እንኳ በመንግስት ላይ ሲቆጡና ሳይስማሙ ሲቀሩ ሮጠው የሚሄዱት ወደዚህ የፍትህ ስርአት ይሆናል። ይህ አማራጭ ከሌላቸውና ፍርድ ቤቱም ሆነ የፍትህ ስርዓቱ የይስሙላ ከሆነ ለሌላ አላስፈላጊ ምርጫዎች ይዳረጋሉ። ጦርነትን ፈላጊ ወገኖችም ብዙ ምልምል የሚያገኙት በዚሁ ጊዜ ይሆናል።

ሁለተኛ አሁን ያለው መንግሥት እስካሁንም ድረስ ከደርግ ጋር እየተዋጋ ያለ ይመስለዋል። ደርግ ከወደቀ ከሃያ  ዓመታት በላይ አልፈዋል አሁን ያለው ደርግ ወይም ከደርግ የበለጠ ጠላት ነው። ለመሆኑ ይህ ጠላት ማነው እንዴትስ ከደርግ የበለጠ ሆነ? አንደኛ የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረና የኑሮ ውድነትም እየባሰ ስለሆነ አገሪቱን የሚመግብና አዲሱን ትውልድ የሚያስተናግድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት ቀላል ነገር አይደለም። እንደ ደርጉ ጊዜ የትጥቅ ትግልን ባይጠይቅም የውስጥን ትጥቅ የሚጠይቅ ከባድ ስራ ነው። በነዚህ ሃያ ዓመታት ብዙ ነገር እስከተየቀየረ ድረስ ትግሉም መልኩን እየቀየረና እየተለዋወጠ ነው እየሄደ ያለው። ያንጊዜ ደርግን በጣላችሁበት የስርዓት መረብ የትግል ስፋትና አቅም አሁን ያለውን ችግር ማሸነፍ አትችሉም። ለአሁኑ ችግር የሚመጥነው የአሁን መፍትሄ ያስፈልገዋል። ከኢኮኖሚው አስራር በስተቀር ሌሎች የኢህአዴግ ርእዮተ አለሞችና አካሄዶች ያን ጊዜ የነበረውን ስርአት ለመጣል የተዘሩጉት ናቸው። እስካሁን አልሰፉም አልተሻሻሉም። የፖለቲካው ምህዳር አሁን ያለውን አስተሳሰብ አሁን ያለውን የህዝብ ብዛት አሁን ያለውን ስልጣኔ አሁን ያለውን ርእዮተ አለም የማያስተናግድ ጠባብ ነው። ስለዚህ በአገሪቱ ልክ መስፋት አለበት። ሌላው ከደርግ ጋር በተደረገው ውጊያ የኃይል እንጂ ብዙም የፕሮፓጋንዳና የቴክኖሎጂ እገዛ አልነበረም። የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱም ቢሆን በአብዛኛው በአገር ውስጥ ባለው ህዝብ ህሊናና በጥቂት የውጭ ወዳጆች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። አሁን ግን ፌስ ቡክ ራሱ እንደ ብዙ ታንክ ሊቆጠርና ሊታይ ይገባል። ኢንተርኔት እንደ ሚሳየል ዩቲዩብ እንደ ላውንቸር ሊታይ ይገባል። ምክንያቱም በፕሮፓጋንዳና በህዝብ ግንኙነት ትግሉ እነዚህ ነገሮች የሚጫወቱን ሚና ጠንካራ ነን የሚሉትን የምእራባውያን መንግስታት እንኳ ያናጋ ነው። በአንድ ከተማና መንደር የተደረገው ነገር ሁሉ ከመ ቅጽበት ለአለም በሚዳረስበት ጊዜ ላይ ሆነን ሞያ  በልብ ነው ብሎ መቀመጥ ሽንፈትን ያመጣል። የሰራው ተቀምጦ የዋሸው ይሸለማል። ሌላው የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ካለው የአለም ህብረተሰብ ጋር ለመስራት በመቁረጡና በሩን በመክፈቱ በሌሎችም ይገመገማል። እነዚህ የውጭ አገራት ምንም ነገር ቢያደርጉ ለመጽደቅ እንደማያደርጉ ከታሪክ እንማራለን። የሚፈልጉት የራሳቸው ዓላማ አላቸው። በሁለት ቢላ የሚበሉ ክፉዎች ናቸው። ከኛ ጋር ስለበሉ የኛ ብቻ ወዳጆች ናቸው ማለት አይደለም። ምሳቸውን ከኛ ጋር በልተው ራታቸውን ደግሞ ከአገሪቱ ጠላቶች ጋር ነው የሚበሉት። ለዚህም ነው እነርሱንና ህዝባቸውን የጎዱትን ሰዎች አሸባሪዎች እያሉ እስከ ምድር ዳር ሲያድኑ በኢትዮጵያ ብዙ ንፁሐንን የገደሉና ለመግደል የሚንቀሳቀሱትን አክብረው በአገራቸው የሚያኖሩት። ስለዚህ ትግሉ ሰፊና እልህ አሽጨራሽ ነው። አሁን ደርግ ከመንግሥት አእምሮ መሰረዝ አለበት። አሁን ካሉት የአገሪቱ ጠላቶች ጋር ሲወዳደር ደርግ ትንሽ ጠላት ነበር። የደርግ ስርአት ያንን ያመነበትን አላማ  የማይቀበሉትን ቢዋጋና ውጊያው ማስተዋል የጎደለው ቢሆንም ለኢትዮጵያ ህልውና ነበር የሚዋጋው። አሁን ያሉት ጠላቶች ግን ብዙዎቹ ለኢትዮጵያ አይዋጉም። ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የካዱና ኢትዮጵያዊ ላለመሆን የሚዋጉ ናቸው። ይህንን ዓላማቸውን የሚወዱላቸውና በልብ ከነርሱ ጋር የሆኑ የውጭ አገራት ደግሞ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እያቀረቡላቸው ነው። ድሮ ኢህአዴግ ሲዋጋ ውሎ አመሻሹ ላይ የሚበላውን እንጀራ ለማግኘት  ገበሬውን እንጀራ እየለመነ ይዋጋ እንደነበረው አይደለም። በዚያን ጊዜ የነበሩት ታጋዮች አብዛኛዎቹ የፈለጉትን ምግብና ልብስ ማግኘት ይቅርና የሚበላ አጥተው በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ ነው የታገሉት። የአሁኖቹ ታጋዮች የሚበቃ ገንዘብ በባንክ አላቸው። ምክንያቱም ስንቅና ትጥቃቸውን የሚያገኙት ከድሀው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ አገሮች ነውና። የጦርነቱን ስልት የሚነድፉትና ጦርነቱን የሚመሩት በአውሮፓና በአሜሪካ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ተቀምጠው ነው። ስለዚህ መንግሥት ይህንን አዲስ አይነት በስልጣኔ የተቀናበረ በውጭ ሀገራት ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ኃይል ለመመከት በአዲስ ትጥቅ መታጠቅና መዘጋጀት አለበት። ይህ አዲስ ትጥቅ ምን ይሆን? ለነገሩ አዲስ አይደለም። ድሮም ለጥቂት ጊዜ ታጥቆት ነበር በኋላ ላይ አውልቆት ነው እንጂ። ለመሆኑ ይህ ትጥቅ  ምንድን ነው?  ይህ ልዩ የሆነና ማንም የማያሸንፈው ትጥቅ የህዝብ ልብ ነው። ኢህአዴግ ድሮ ለህዝብ ነበር የሚታገለው። የደርግ ወታደሮች የገበሬውን በር በዚያ ትንሽ ታንክ በሚያክለው ጫማቸው  ሰባብረው ሲገቡና ህዝቡን እያንቋሸሹ ሴቶችን ሲደፍሩ የኢህአዴግ ታጋዮች ግን በመሳሪያ ብቻ ሳይሆን በሞራልና በስነ ምግባር የታነጹ ነበሩ። የራሳቸውን ምኞት ለማርካት ህዝብን አይበድሉም ነበር። እንጀራና ውሀ በትህትና ይጠይቃሉ ከተከለከሉ ይሄዳሉ። ለህዝቡ ጥቅም የታገሉ መሆናቸውን ያሳዩት ቤተ መንግሥት ሲገቡ ሳይሆን እዚያው በመንደሩ በጫካው ሳሉ ነው። ይህንን ያየው ጭቁን ህዝብ ልቡን ሰጣቸው ልጆቼ ብሎ ሳማቸው። ልጆቹን ለዚህ ዓላማ መርቆ ሰደደ። ብዙ ወጣት አለቀ። ስልጣኑን ከተቆናጠጡ በኋላ  ግን ይህ ልብስ ቀስ በቀስም ቢሆን የወለቀ ይመስላል። መቼም ይህ ትጥቅ አልተለወጠም የሚል ቢኖር አይኔን ግንባር ያርገው ያለ ሰው ብቻ ነው እንጂ ለሁሉም በሚታይ መልክ ይህ ልብስ ተለውጦአል ወይም ገርጥቶአል። እኔ በትግሉ ወቅት የአስራ ሁለት አመት ልጅ ነበርኩ። በተወሰነም መጠን ቢሆን ያየሁት ነገር አለ።  የአሁኑና የያንጊዜው በጣም የተለያየ ነው። ባለፈው ዓመት አንድ የትግሉ ተሳታፊ የነበረና አሁን በስልጣን ላይ ያለ ሰው አገኘሁና እንዲያው ቢገባውና ለጓደኞቹም ቢያስተላልፍ ብየ እንዲህ አልኩት «በትግሉ ወቅት በበረሃ ህይወታቸውን የገበሩት ታጋዮች ተመልሰው የመምጣትና የማየት እድል ቢገጥማቸው ኖሮ ደርግ በየት በኩል ተመልሶ መጣ ብለው ይወጉአችሁ ነበር አልኩት። መጀመሪያ ትንሽ ደነገጠ ተናደደም። የጓዶቹ ደም ሳይወቅሰው አይቀርም። ከዚያም ትንሽ አሻሻልኩና ወይም እናንተን ራሱ ደርግ ሆናችኋል ብለው በግምገማ ያስወግዱአችሁ ነበር አልኩትና አሁን ያለውን ብዙ ንቅዘት የምችለውን ያህል አስረዳሁት። በትንሹም ቢሆን የተረዳኝ ይመስለኛል። ቢያውቁት እኮ እውነቱን ከህዝብ መስማት በጣም ነው የሚጠቅመው። እውነት ነው እነዚያ ለህዝብ ጥቅም ብለው ክቡር ህይወታቸውን የገበሩት ውድ ወጣቶች አሁን ያ አብሮአቸው የነበረው ሰው ጉቦ ተቀበለ ሲባል ቢሰሙ ምን ይላሉ? እንግዲህ መንግሥት ብዙ ወጣቶች ህይወታቸውን በመገበር ያስገኙትን መልካም አስተዳደር ሊጠብቀው ይገባል። እነርሱ ጦር ሜዳ ውለው ማታ ይገመገሙ ከነበረ ዛሬ በቢሮ ተቀምጦ ሰው የማይገመገምበትና የማይሰታካከልበት ምክንያት ምንድን ነው? እንዴት ይህን ማድረግ ያቅታል?

ስለዚህ እነዚህን ህዝብ ያማረሩትን ሰዎች ማጥራትና ህዝቡን ከራሱ ጋር ማሰለፍ ይገባዋል። አገሪቱን ወዳላስፈላጊ መፈራረስ ለመውሰድ የሚፈልጉት አፍራሽ ኃይሎች ይህንን በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ያለውን ክፍተት በጣም ነው የሚፈልጉት። መንግሥት ህዝቡን በማስቆጣትና ለመልስ በመዘግየት  ለጸረ ኃይሎች ማመቻቸት የለበትም። የሰፋ ክፍተትና የህዝቡ ምሬት በነርሱ ወጥመድ እንዲያዝና  ክፉ ዘራቸውን ለመዝራትና ለማብቀል የሚጠቀሙበት መልካም መሬታቸው እንዲሆን ያደርጋል። ጠላትን ከአገር የምናስወጣው ከህዝብ ልብ በማውጣት ብቻ ነው።  ስለዚህ ህዝቡን በአስተዳደራዊ በደል እያማረሩ ለጸረ ሰላም ኃይሎቹ የሚያዘጋጁት ብልሹ አመራሮች ከነርሱ ተለይተው ሊታዩ አይገባም። አገሪቱን ከውስጥ የሚያፈርሱ ነቀዞች ናቸው። መስተካከል መታረም ካልሆነም ከስራቸው መነሳት አለባቸው። ይህ በአዋጅና በመመሪያ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተገልጦ በህዝቡ እርካታ መታየት አለበት።

ሌላው መንግሥት የይስሙላ ዴሞክራሲን ማራመድ ማቆም አለበት። የተሻለና አገር የሚጠቅም አስተሳሰብ ያላቸውን የግልና የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎችን ለማስገባት የስርአቱን በር ወለል አድርጎ መክፈት አለበት። የሚገርመው ከብዙ ተቃዋሚዎች በጣም ጥሩ የሆነ ጠቃሚ ሐሳብ ሰምቻለሁ። ነገር ግን ኢህአዴግ የሚል ስም ስላልለጠፉ ብቻ ከስርአቱ ውጭ ሆነው ይታያሉ። ጠቃሚ ሐሳብ የያዘን ሰው ለአገሪቱ ጥቅም ብለን ለምነን ልናስገባው ይገባል። ለምሳሌ ልደቱ አያሌው የሚባሉት ኢትዮጵያዊ የጻፉአውንና በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው ችግር የሰጡትን አስተያየት ስመለከት እኚህ ሰው አንድን ወገን ያልወገኑና ለአገር ጥቅም የሚያስቡ መሆናቸውን ታዝቤአለሁ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ለምን በአመራሩ ላይ ስፍራ አይሰጣቸውም? ኢትዮጵያዊ መሆን እኮ ኢህአዴግ ከመሆን ይበልጣል። ኢህአዴግም የሌላ ፓርቲ አባልም የምንሆነው እኮ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ነው። ስለዚህ አንድን ሰው በፓርቲ መነጽር ከማየታችን በፊት በኢትዮጵያዊነት መነጽር ልናየው ይገባል። ከየትኛውም ወገን ይምጣ አገርን የሚጠቅምና ብዙኃኑ የሚቀበለው ሐሳብ ከሆነ የትጥቅ ትግል ተደርጎ እስኪመጣ መጠበቅ የለበትም። ሌላው ፓርቲ የነካው ሐሳብ ሁሉ ጠቃሚ አይደለም የሚል አስተሳሰብ ጠባብነት ነው። ጠቃሚ ከሆነ እንኳንስ ከአንድ ዜጋ ይቅርና ከውጭ መንግስታት ስንት ነገር እንቀዳ የለ? አንድ ነገር በኢትዮጵያዊ ሲነገረን የሚመረን በውጭ መንግስታት ሲነገረን ግን እንደ ማር እየጣፈጠን የምንቀበለው ለምንድን ነው? ይህ ነገር ከበሽታዎች እንደ አንድ መፈረጅ ያለበት ይመስለኛል። የዚህም ነገር ምንጭ ጥላቻና መናናቅ ነው።

ሌላው መንግሥት አንድን ርእዮተ አለምና አንድን ፖሊሲ ይህ አቋሜ ነው ብሎ ክችች ከማለት ይልቅ ህዝቡ ይቀበለዋል ወይ  ለህዝቡ ይስማማል ወይ ብሎ መጠየቅ አለበት።  ፖለቲካና ርእዮተ አለም የማንለውጠው ሃይማኖት አይደለም። ለህዝብ የማይጠቅም ከሆነ መለወጥ አለበት። ህዝብ የማይቀበለው ከሆነ አሁንም በመንግሥትና በህዝብ መካከል ቅሬታንና ክፍተትን አምጥቶ  የሌላው መመሸጊያ ከመሆኑ በፊት መሻሻል ይገባዋል።  ለምሳሌ ፌዴራሊዝም ያመጣውን ያልታሰበ የጎን ውጋት በግልጽ      እያየን ነው። ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሲወሰን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ከምትባል አገር ወጥተው እንደ ኤርትራን ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ ሳይሆን ሳይሆን በአንድነት ተሳስረውና መብታቸው ተከብሮ አንዲትን ኢትዮጵያ ለማጽናት ነበር። ይህ ዓይነቱ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ የሌላቸውና ፌዴራሊዝምን የፈለጉት ከማይወዱአት ኢትዮጵያ ተለይተው ለመገንጠል እንደ መጀመሪያ ምእራፍ እንዲያገለግልና በፌዴራሊዝም ስም በራቸውን ከማእከላዊው መንግሥት ዘግተው በደንብ ከተጠናከሩ በኋላ ለመለየት መሆኑ እየታየ ነው። ገና ሙሉ በሙሉ ሳይለዩም እንኳ ወደነዚህ ክልሎች ስትገቡ ከኢትዮጵያ ወጥታችሁ ወደ አጎራባች አገር የገባችሁ ያህል  እንዲሰማችሁ የሚያደርግ አሰራር ታያላችሁ። በአሜሪካ ግዛቶች ከአንዱ ስቴት ወጥታችሁ ወደሌላው ስቴት ስትገቡ ወደዚህ ስቴት እንኳን በደህና መጡ የሚል ታፔላ እስካላያችሁ ድረስ ድንበሩን ማቋረጣችሁን እስከማታውቁ ድረስ ስርዓቱ ተመሳሳይ ነው። በስቴቶች መካከል የጎላ ልዩነት የለም። አንድ ሰው ከፈለገ ዛሬ ከአንዱ ስቴት ወጥቶ ሌላኛው ስቴት ስራ መቀጠርና ኑሮ መመስረት ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘረጋው ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠፋና የአገሪቱን ዜጎች ልብ የሚያራርቅ መሆን የለበትም። ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያዊነትን  ፍቅር ከልብ የሚፍቅ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርጎ የሚያቆማት ደግሞ ህገ መንግስቱ ሳይሆን ራሱ ኢትዮጵያዊነት ነው።  ትክክለኛው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ ህገ መንግሥት በሰው ልብ ውስጥ የተጻፈ እንጂ በወረቀትአይደለም።በሰው ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ካልተጻፈ በወረቀት ህገ መንግሥት ሊመጣ አይችልም። በወረቀት ያለው ህገ መንግሥት የሚጠቅመው በሰው ልብ ካለው ተቀድቶና ተገልብጦ ሲጻፍ ብቻ ነው። መንግሥትኢትዮጵያዊነትን ከሰው ልብ እየፋቀ በወረቀት ለጻፈው ብቻ ቢቆም ህዝብ አንድ አይሆንም።

ህገ መንግሥቱ ከዚህ ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተቀዳ ሰነድ እንጂ ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያን ለማድረግ የተጻፈ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት በመወለድ የምናገኘው የተፈጥሮ የአገር ፍቅር ነው። ይህ ነገር በውስጣችን ተጽፎ ከሌለ በህገ መንግሥት ኢትዮጵያዊ አንሆንም። ስለዚህ መንግሥት በወረቀት የተጻፈውን ህገ መንግሥት ለማስከበር ደፋ ቀና ከማለቱ በፊት በህዝቡ ላይ የተጻፈውን ኢትዮጵያዊነት ማጠናከርና በተለያየ የሐሰትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ይህንን ከህዝቡ ልብ ለመፋቅ ከሚጥሩት ፎርጂድ ሰራተኞች መጠበቅ አለበት። ኢትዮጵያዊነትከሰውልብየሚፋቀውበውጭፕሮፓጋንዳ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያዊነትን ከሰው ልብ ለመፋቅ የሚሰሩት ኃይሎች አንደኛው ወገንበኃይማኖት አክራሪነት የተጠመቁ ከተፈጡሩባት አገር ከኢትዮጵያ ይልቅ ኃይማኖታቸው የተመሰረተበትን አገር የሚወዱና ራሳቸውን የዚያ አገር ዜጋ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው።ሁለተኛው ወገን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት የማያምኑ በጥንቲቱ ኢትዮጵያ ተበድለናል ብለው በቂም በቀል ፕሮፓጋንዳ የተታለሉና ኢትዮጵያን የሚጠሉ ናቸው።

ሌላውና የነዚህንም ያህል ባይሆን የአገርን ፍቅር የሚያቀዘቅዝና አንድን ዜጋ ጥግ ይዞ ተመልካች ብቻ ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ  በመንግሥት የሚደርስ የአስተዳደር በደል ነው። ሰዎች የአስተዳደር በደል ሲበዛባቸው የዜግነት መብት ትርጉም እያጣባቸው ይሄዳል።ለዚህም መንግሥት ለዜጎቹ የቆመ መሆኑን በተግባር በማሳየት በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሜዳ ማመቻቸት ይገባዋል።  ለወጣቱ ትውልድ ታሪኩን በደንብ ማስተማርና የአገርን ፍቅር በልቡ ማሳደግ ያስፈልጋል።  ስለዚህ መንግሥት ይህንን ጉድለት በፍጥነት ማስተካከል ይኖርበታል። ይህም አንዳንዶች እንደሚሉት የፌዴራሊዝም ስርአቱን በማፍረስ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች የአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት በሙላት የሚጠበቅበትንና የዘር የቋንቋና የብሄር አድልዎ የሌለበትን የፌደራል ስርአት በማጠናከር ነው። ይህም የፌዴራሊዝሙን ስርአት እንደ መሸሸጊያ ተጠቅመው ህዝቡን ለማለያየትና ለማራራቅ የሚፈልጉትንና የጥቂቶችን ምኞት የህዝቡ ፍላጎት አስመስለው በማቅረብ ኢትዮጵያን የሚጎዱትን ግለሰቦች ስፍራ ያሳጣቸዋል። አዎ የፌዴራሊዝሙ መንፈስና መሰረት የህዝቡን በቋንቋ በባህል በብሄር መለያየትና ህብረ ብሄር መሆን እንደ ኢትዮጵያ ውበት ቢያስቀምጥም እንደ ውበት ሳይሆን እንደ መፎካከሪያና እንደ መራራቂያ  እንደ መናናቂያ የሚጠቀሙ እንዳሉ እያየን ነው። ይህ እንዳይሆን አንደኛ በጠንካራ የፌደራል አቃቤ ህግ አሰራር በሁሉም ክልሎች የዜጎች መብት መጠበቅ አለባቸው። የክልል መንግሥት አለም አቀፍንና የኢትዮጵያን ህግ በጣሰ መልክ የዜጎቹን መብት እየጣሰ ራሱን እንደቻለ አገር እንዲንቀሳቀስ መፈቀድ የለበትም። የፌዴራል መንግስቱ በክልል መንግሥት ለሚበደሉ ዜጎች ፈጣንና ጠንካራ ፍትህን በመስጠት ሊያስተምር ይገባል። በተለይ በዘር በብሄር በቋንቋ ጥላቻ የሚፈጠሩ አድልዎዎችና ወንጀሎች በከፍተኛ የወንጀል ደረጃ መታየት ይገባቸዋል። ዜጎችም በዚህ ጉዳይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና በዚህ ሴንሴቲብ በሆነ ጉዳይ  ላይ ስልጠናና ንቃተ ህሊና እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። እንዲህ ዓይነት ነገሮች በብዙ ብሄረሰቦች ለተዋቀረች አገር በጣም ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ለእሳት የሚያስፈልገውን ያህል ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። እሳት ለብዙ ነገር ጠቃሚ መሆኑን እናውቃለን። የእለት ምግባችንን ከማብሰል ጀምሮ በጣም ብዙ ነገሮችን እንዳርግበታለን። ከባድ ብርድ ሲያጋጥመን ቀርበን በመሞቅ እንደሰትበታለን። በጥንቃቄ ካልተያዘ ግን የሚያደርሰው ጉዳት የዚያኑ ያህል ከባድ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች ተከባብረውና ተቀራርበው ሲኖሩ የአገሪቱ ውበት የመሆናቸውን ያህል በክፉ ሰዎች በሚለኮስ እሳት ያለ አግባብ ሲቀጣጠሉ ግን አደጋን ያመጣሉ። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ የሚታዘብ የሚከታተልና የሚዳኝ ልዩ አቃቤ ህግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ካለ ጥሩ ከሌለ ግን ሊታሰብበት ይገባል።

ሌላው የመሬት ፓሊሲ ጉዳይ ዋናው በብዙ ተቃዋሚዎች የሚነሳ ነገር ነው። ምንም እንኳ መንግሥት ባለፉት ሃያ  ዓመታት ውስጥ የሰራው ጥሩ ነገር ቢኖርም ህዝቡ ካልረካና የተሻለ ነገር ካለ መንግሥት በቀጥታ ህዝቡን ማድመጥ አለበት። የህዝቡ ጩኸት በተቃዋሚዎች ጆሮ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በመንግሥት ጆሮ መግባት አለበት። መንግሥት በልማት ስም መሬትን ለውጭ ባለ ሀብቶች ሲሰጥ ለዜጎች ትክክለኛና ተመጣጣኝ ካሳ መስጠት አለበት። የአገርን ዜጋ የማታለል ያህል በጥቂት ሺህ ብሮች ሸኝቶ መሬቱን በሚልዮን መቸቭቸብ በምንም ተአምር ፍትሀዊ ሊሆን አይችልም። የሚነሱትን ዜጎች ተለዋጭ ቦታ መስጠት ይህንን አያካክስም። እንዲያውም መንግሥት አርቆ በማሰብ ተመጣጣኝ ገንዘብ መስጠት ብቻ ሳይሆን በሚመሰረቱት ተቋማት ውስጥ ህዝቡ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው በመደራደር መብቱን ቢያስጠብቅለት ህዝቡ እነዚያን የልማት ተቋማት እንደ የውጭ ባለሀብት ንብረት እያየ ይህ መሬት እኮ የኔ ነበረ እያለ ከንፈሩን ከመንከስ ድኖ ሳይሆን በማየት ይንከባከባቸዋል። በዚህን ጊዜ መንግሥት የህዝቡን ልብ አሸነፈ ገዛ የውጭ ሀይሎችም በመሳሪያ ሳይሆን በህዝብ ልብ ተሸነፉ ማለት ነው። ህዝቡ ካላስገባቸው በየትኛውም ወደብ ወደ ኢትዮጵያ መግባትና ሰላምን ማደፍረስ አይችሉም። መንግሥት ለካድሬዎቹ ሳይሆን ለህዝቡ ጆሮው መከፈት አለበት። ማስከፋትም ካለበት ህዝብ የሚያማርሩ ካድሬዎቹን እንጂ ህዝቡን አይደለም። ካድሬ ይተካል ህዝብ ግን አይተካም።

በመጨረሻ የማነሳው የአገሪቱን የፍትህ ስርዓት ነው። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ብዙ መንገዶች ተሰርተዋል ብዙ ህንጻዎች ተገንበተዋል። አገሪቱ ጠላትም በሚመሰክረው መልክ ብዙ የልማት እመርታዎችን አሳይታለች። የፍትህ ስርዓቱ ግን ነጻና ፍትሀዊ ነው ለማለት ያስቸግራል።  የፍትህ ተቋማቱና ዳኞቹ መንግሥት እኔን አገልግሉኝ ባይላቸውም እንኳ ከመንግሥት ነጻ በሆነ መንፈስ ህዝቡን ማገልገልን ገና አልለመዱም። ስለዚህ ከፖለቲካ ባርቲ ወይም በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ነጻ ሆነው መንግሥትና ህዝብን በእኩል የሚዳኙ የፍትህ ስርዓቶችና ዳኞች ያስፈልጋሉ። አስቀድሜ ከጠቀስኩት መሰረተ ልማት ቀድሞ መልማት ያለበት ይህ ስርአት ነው። ይህ ስርአት ሳይጠናከርና ሳይጸና መሰረተ ልማቶችን ብቻ ብናለማ መንገድና ፎቅ ብንሰራ ስርአት አልበኝነት ሲነግስ ያፈርሳቸዋል። የፍትህ ስርአቱ እንደ መሰረት ከተቀመጠ በኋላ ልማቱ ቢሰራ ግን በትክክለኛ መሰረት ላይ ተሰርቶአልና ዘላቂ ይሆናል። ስለዚህ ለአንዲት አገር ትክክለኛ የልማት መሰረት የመንግስቱ ስርአት በሰላማዊ መንገድ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበትንና ዜጎችና መንግሥት የሚፋረዱበትን ተከራክረው የሚሸናነፉበትን የፍትህ ሜዳ መዘርጋት ነው። ይህ ከሆነ የሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ አፍራሽ ወደ ሆነ መንገድ ከመሄዳቸው በፊት በዚህ ስርአት ብቻ እልባት ያገኛሉ። የፍትህ ስርአቱ እንደዚህ ከተመሰረተ አንድ ዜጋ መንግሥት መብቱን ሲነካበት ሄዶ መብቱን የሚያስከብርበት ከሆነ ይህንን ትቶ አድካሚውንና አፍራሹን መንገድ የሚመርጥ አለ ብየ አላስብም።

%d bloggers like this: