THE REASON BEHIND THE REASON OF THE CURRENT ETHIOPIAN PROBLEM

THE REASON BEHIND THE REASON OF THE CURRENT ETHIOPIAN PROBLEM

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እየታዩ ካሉት ችግሮች ጀርባ ያለ እውነተኛ ምክንያት።

ከብዙ ምክንያቶች ጀርባ ያለ አንድ ምክንያት

የአንድን  ችግር ምንጭ ማወቅ የችግሩ ግማሽ መፍትሄ ነው ይባላል። የችግርን ምንጭ ማወቅ እንዴት መፍትሄ ይሆናል ለሚል ሰው መፍትሄው የችግሩን ምንጭ ማወቃችን ራሱ ሳይሆን የችግሩን ምንጭ ማወቃችን ትክክለኛውን መፍትሄ እንድናገኝ ስለሚረዳን ነው። የማንኛውንም ችግር ምንጭ ካላወቅን ያልተቀደደ ስንሰፋ የማያድን የግምት መድኃኒት ስንወስድ እንገኛለን።  ያ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ  ደግፍ እንደሚባለው ችግሩን መፍታት ሳይሆን ያባብሰዋል። ስለዚህ ከችግሮች ጀርባ ያለውን እውነተኛውን የችግሩን ምንጭ አለማወቅ ሰዎችን ህዝብን አገርን በእጅጉ ይጎዳል። ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ሆስፒታል የተከሰተው ችግር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ሁለት ሴቶች በተለያየ ህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ይመጣሉ። የአንደኛዋ ችግር በአንገትዋ ላይ የወጣን እበጥ በቀዶ ጥገና ለማስወገድ ሲሆን የሌላኛዋ ደግሞ የቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የሆድ ውስጥ ህመም ነበር። ዶክተሩ በስማቸው ተመሳሳይነት በመሳሳትና መዝገባቸውን በሚገባ ባለማየት አንገትዋ ላይ ያለውን እበጥ ለማስወገድ የመጣችው ህመምተኛ ላይ የሆድ ላይ ቀዶ ጥገና እንዳደረገና ሌላኛዋን ማለትም የሆድ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋትን ደግሞ የአንገት ላይ ቀዶ ጥገና ሊያከናውን ሲል ነገሩ እንደታወቀና ዶክተሩም ከስራው እንደታገደ በመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል።  ይህ ታሪክ የአንድን ችግር ምንጭ በሚገባ ሳንረዳ የምንሰጠው መፍትሄ መፍትሄ ሳይሆን ከችግሩ የባሰ ችግር መሆኑን ያሳየናል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውም ችግር በዚህ ታሪክ ሊመሰል የሚችል ነው። በመንግስት የመልካም አስተዳደር ጉድለት ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለ ግልጽ በደል ይታያል። ህዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት ተማሮአል። የተወሰኑ ሁሉንም በገንዘባቸውና በስማቸው ማከናወን የሚችሉ ሰዎች መልካም አስተዳደር ባይኖርም አልተጎዱም። ህይወታቸውንና ስራቸውን የሚመሩበት የራሳቸው «የዝንጀሮ መንገድ» ስላላቸው እንዲያውም ሁሉንም በእኩል የሚያስተናግድ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አይፈልጉም። ያ ከመጣ ሁሉም በሚመራበት ህግ ሊመሩ ነውና ይህ ደግሞ በአንድ ቀን የሀብት ጨረቃ ላይ ማረፍ ከቻሉበት የሙስና ሮኬት ያወርዳቸዋልና ነው። ብዙኃኑ ግን መልካም አስተዳደር እንደውሀ እንደጠማው እሙን ነው። ይህንንም ጥማቱን በተለያየ መንገድ እየገለጸ ነው። እንግዲህ ችግሩ መልካም አስተዳደር ከሆነ መልሱ መልካም አስተዳደር እንዲመጣ በተለያየ ህጋዊ መንገድ መጣርና መንግስትን በህጉ መሰረት መሞገት ነው። ለአንድ ህብረተሰብ የህሊናንና የመንግስትን ህግ ተከትሎ መብቱን ከመጠየቅ ሌላ መንገድና መፍትሄ የለም። ይህን ለማድረግ ግን ሰው ራሱን በመግዛትና ክፉ ማንነቱን በመገደብ  ሊጀምር ይገባል። አገላለጡ ይለያይ እንጂ በሰው ሁሉ ውስጥ ክፉ የሆነና ራሱንም ሆነ ሌላውን ሰው በእጅጉ የሚጎዳ ማንነት አለ። ህግና መንግስት የሚያስፈልገን ያንን ክፉ ተፈጥሮአችንን ገድቦ በመያዝ እንደ ህብረተሰብና እንደ አገር መኖር እንችል ዘንድ ነው። ክፉው ማንነታችን ለህብረሰብና ለአገር ግንባታ ይቅርና ለራሳችንም አደገኛ የሆነ መርዝ ነው። የማንነታችን ጉድጓድ ተከፍቶ ክፉው ማንነታችን አግጥጦ ከወጣ አገርን የሚጨርስ ሰደድ እሳት ይፈጥራል። እንደ አገርና እንደ ህዝብ ተሳስበን አብረን በሰላም መኖር የምንችለው ክፉ የሆነውን ማንነታችንን በህግና በህሊና አስረን በተሻለው ማንነታችን ለመኖር ስንወስን ነው። ክፉ ማንነታችንን ሳንጠቀም አድካሚና ሰላማዊ በሆነው አገርንና ህብረተሰብን በማይጎዳ መንገድ መንግስትን ለመሞገትና መልካም አስተዳደርን ለማምጣት የማይፈልጉ ሰዎች ሁልጊዜ አቋራጩን መንገድ ይጠቀማሉ። አቋራጩ መንገድ ይህንን በህሊናና በሀይማኖት እንዲሁም በህግ የታሰረውን የሰውን ክፉ የውስጥ ክፍል ፈትቶ መልቀቅ ነው። የሰዎች ክፉ የሆነውን የማንነታቸው ክፍል ሲነሳ ሰብአዊ ፍጡር የማይፈጽመውን ዘግናኝ ነገር ይፈጽማሉ። በርዋንዳ ሶስት ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚልዮን በላይ ህዝብ እንዲያርዱ ያደረጋቸው ይህ ነው። በአሁኑ ሰአት በአለም ዙሪያ ሰዎች ሰውን እንደ እንስሳ እያረዱ ያሉበት ምክንያትም ይህ ነው። ሰው ይህ የተቀበረው የውስጥ ማንነቱ ያለገደብ ሲገለጥ ምንም አይነት ገመድ የማይዘው ህሊናውን የበጠሰ ፍጥረት ይሆናል። ከአካላዊ ቁመናው በቀር ሰው እንደነበረ የሚያሳየን ቅሪት የለም። እንግዲህ ለሚያስተውል ሰው በአለም ላይ ለምናያቸው ከአእምሮ በላይ ለሆኑ እልቂቶችና በህዝቡ ሁሉ ለሚታየው የገነፈለና መልክ የሌለው ዓመጽ ምክንያቱ ይህ ከጀርባ ያለው በሌላ ኃይል የሚመራው ማንነታችን ነው። ሰው ሁሉ የራሱን ማንነት አደገኛነት ካላወቀ አደገኛው ነገር ያ ነው። ማንነታችንን እንደ እሳት ልንመስለው እንችላለን። እሳት በአግባቡ ተጠንቅቀን ስንጠቀምበት ምግባችንን ያበስልልናል ጣፋጭም ያደርግልናል። ከሚገባው ገደብ እንዲያልፍ ካደረግነውና ካቀጣጠልነው ግን አገርን ያጠፋል እኛንም ያጠፋል። የሰውም ማንነት እንዲሁ ነው። የወደቀው ሰውነታችን ለሰው የሚያዝን፣ የሚራራ፣ ሰውን ለማዳን ዋጋ የሚከፍል፣ የሚሰጥ ክፍል እንዳለው ሁሉ ሰውን የሚጠላ፣ ሰውን የሚገድል፣ በሰው መከራ ደስ የሚለው፣ ክፉ የጨለማ ማንነትም አለው።  መልካም የሆነው ባህርያችን ሲገለጥ እንደህብረተሰብ እንደ አገር አብረን መኖር አይከብደንም። ለሰው ማሰብ፣ አብሮ መኖር፣ በአንጻራዊ ፍቅር መዋደድ፣ ለሰው ማዘን የሰውነታችን ቅመሞች እንደሆኑ በመገንዘብ በነዚህ ባህርያት እንኖራለን። አንዱ አንዱን ሲበድልም ከሰውነት ውጭ ባልሆነ መንገድ ህግና ስርአቱን ጠብቀን እንከራከራለን እንነጋገረለን ችግሮቻችንንም እንፈታለን። ከህሊናችን ከስብእናችን ስንወጣ ግን ጨለማው ማንነታችን ስለሚገለጥ  ዓመጽና መፍረስ ጥላቻ ግድያ ይሰፍናል። በዚህም አገርና ህብረተሰብ ሰላምን ያጣል አልፎም ይጠፋል። ከብዙዎቻችን የተሰወረው ነገር ግን ከዚህ ጨለማ ከሆነው ከወደቀው ማንነታችን ጀርባ የሚሰራና ይህ ክፉ ማንነታችን ብቻ እንዲገለጥ የሚፈልግ ኃይል መኖሩን አለማወቃችንና ባለማወቅ የኛ እየመሰለን የርሱን አላማ መፈጸማችን ነው። ይህ ኃይል በቀጥታ ጨለማውን ማንነታችንን በማነሳሳት ወይም አገልጋዮቹ በሆኑ ፖለቲከኞችና የህብረተሰብ መሪዎች በሚለቀው ቅስቀሳ የጨለማችንን እሳት በማቀጣጠል አላማውን ይፈጽማል። እርሱ ማን እንደሆነ ስለማይታወቅና እንዲታወቅም ስለማይፈልግ እነዚህ ፖለቲከኞች ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱትና እንዲጫረስ የሚያቀጣጡሉት የራሳቸው ሐሳብና አላማ እየመሰላቸው ነው። ይህ የጨለማው ገዢና አለቃ ሐሳቡን በሰዎች ውስጥ የሚያስገባውና የሚያስፈጽመው የራሳቸውን ሐሳብና ፈቃድ እየፈጸሙ ያሉ በማስመሰል ነው። ለዚህም ነው ህዝብን ለዓመጽ የሚያነሳሱትም ሆነ የሚነሳሱት ሁሉ የዓመጻቸውን ምክንያት ሲያስቀምጡ የሰዎች ፍቅር፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የሰዎች ነጻነት ተጋድሎ፣ የአገር ፍቅር እንደሆነ የሚገልጹት። በነጻነትና በአገር ፍቅር ካባ የተሸፈነ ዓመጽ በጭቃ እንደተሸፈነ እሾህ ነው። ሳይታይ ይወጋል ያቆስላል። ለአገር ፍቅርና ለሰዎች ነጻነት ብሎ ሰውን የሚገድል ሰው ዓመጸኛ ነው። ትክክለኛ የፍትህና የነጻነት ታጋይ የአንድም ሰው ህይወት ሳያጠፋና ሰውን ሳይጠላ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ሰው ብቻ ነው። ይህንን ያደረጉ ጥቂት ሰዎች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አሉ ብዙዎች ግን አይደሉም። እንደዚህ አይነት  ሰው ሌላውን ሰው ሁሉ ይወዳል ይቀበላል ለሰው ያዝናል ይራራል። በምንም ምክንያት መሰሉን አይገድልም ለመግደልም አያነሳሳም። እውነቱ ይህ ከሆነ ዛሬ ብዙ ፖለቲከኞች ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱት በአገርና በነጻነት ፍቅር ተሸፍነው ዓመጽ ሲሰብኩ የሚታዩት በብዙ የዋሆችም ተቀባይነት የሚያገኙት ለምን ይሆን? መግደልን ጥላቻን ጦርነትን ዓመጽን የሚሰብክ ሰው እንዴት ይሰማል? ጥቂትስ ቢሆን ሰሚና ተከታይ እንዴት ያገኛል? የዚህ ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? በማስተዋል ካየነው የዚህ ምክንያቶቹ ሁለት በአንድ የሆኑ ምክንያቶች ናቸው። አንደኛው ሰው አደገኛና ጽለመታዊ የሆነ የማንነት ክፍል ያለው ፍጥረት መሆኑን አለማወቁና ይህ የጨለማ ማንነቱ ተፈትቶ እንዲለቀቅ መፍቀዱ ነው። ለምሳሌ በተለያዩ የአለማችን ዋና ከተሞች የዱር አንበሳና የመሳሰሉት የዱር አራዊት የሚጎበኙት ሙዜም አለ። ይህ ሙዜም ግን ልቅና ክፍት የሆነ ለምለም ሜዳ ሳይሆን በጠንካራ አጥር የታጠረ ቦታ ነው። እንደ በግና ላም የመሳሰሉ እንስሳት ክፍት በሆኑ ለምለም ሜዳዎች ሲሰማሩ እነዚህ የዱር እንስሳት ግን በአጥር ግቢ ሆነው ሰው ከውጭ ሆኖ ይጎበኛቸዋል። ለምን  ወደ ከተማ መጡ ሰው እንዲጎበኛቸው እንዲያያቸው። ውበታቸው እንዲታይ የተፈጥሮ ውበታቸውን እያየ ሰው እንዲደሰት። ለምን በታጠረ ቦታ ተቀመጡ? ከውበታቸው በተጨማሪ አደገኛና ሰዎችን የሚጎዳ ብሎም የሚያጠፋ ማንነት ያላቸው የዱር አራዊት ስለሆኑ። ሰውም ምንም እንኳ ከነዚህ እንስሳት የተሻለና የከበረ ቢሆንም በውድቀቱ ምክንያት እነዚህን እንስሳት እንደመሰለ ይታወቃል። ስለዚህ ሰውም ከትክክለኛው ሰውነቱ ጀርባ ያለውን አውሬነቱን የሚገድብ የህግ አጥር የሚያስፈልገው ፍጥረት ነው። ህግ የተሰራው «ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥» ነው ይላል ታላቁ መጽሐፍ (1.ጢሞ.1፡9-11) እንግዲህ አንድ ህብረተሰብ ሁሉንም ማድረግ ያለበት ከዚህ የህግ አጥር ሳይወጣ መሆን አለበት። በአቋራጭ መንገድ ወደ ስልጣን መምጣት የሚፈልጉ ብዙ የፖለቲካ አቀንቃኞች ግን ይህ አጥር ፈርሶም ቢሆን ወደ ስልጣን መውጣት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ይህንን አደገኛ የሆነውንና ህብረተሰብን የሚጎዳ ማንነቱን በመፍታትና በመልቀቅ ይተባበሩታል። የዚህ አጥር መፍረስ በኋላ እነርሱንም እንደሚጎዳ ይዘነጋሉ። አጼ ኃይለ ስላሴን በግፍ የገደለውና በመስኮት ወደ ስልጥን የገባው ያለፈው ትውልድ ያ ዓጼውን ለማስወገድ የከፈተው አጥር እርሱንም እንሚጎዳው አልተገነዘበም ነበር። አሁን ያለውም ህብረተሰብ ካለፉት ጥፋቶች የተማረ አይመስልም። መንግስትም አገዛዙ በትክክለኛ መንገድ የሚቀየርበትን መንገድ በሚገባ የቀረጸ አይመስልም ህዝቡም እንደለመደው በሰላማዊ ሰልፍና በዓመጽ ስርአት መቀየር ይፈልጋል። አንድ ጤነኛ ተቃዋሚ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት የዓመጽን መንገድ ማውገዝ ነው። ከዚያም በኋላ ህዝቡ በትክክለኛው መንገድ የሚበጀውን መንግስት እንዲመርጥ ማነሳሳትና መታገል ነው። የፖለቲካ መሪዎች ዓመጽን ማውገዝ ያለባቸው እነርሱን ከስልጣን ሊያወርድ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን እነርሱን ወደ ስልጣን ለማሳረግ ሲመጣም ነው። አሁን የሚታየው ግን እነርሱን ወደ ስልጣን ለማድረስ ይችላል ያሉት የህዝብ ዓመጽ ሲነሳና በህግ አጥር ውስጥ ተከልሎ ሊኖር የሚገባው ክፉው የሰዎች ማንነት አጥሩን ጥሶ ሊወጣ ሲሞክር አጥር በማፍረስ መተባበር እነርሱን ለማውረድ ከሆነ ግን አጥሩን የመፈለግ አዝማሚያ ነው። ይህ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም አይደለም። የምድረ በዳ አራዊቶች የሚኖሩበት ሙዜም ሁልጊዜ የታጠረ እንደሆነ ሁሉ የሰዎች አደገኛው ማንነትም ሁልጊዜ በህግ አጥር ስር መሆን አለበት። አሁን ይህንን አጥር እያፈረሱ የብዙዎችን አውሬነት በሚለቁ ኃላፊነት በማይሰማቸው የፖለቲካ መሪዎች ምክንያት ብዙዎች እየተነከሱ ነው። ሁለተኛ ይህ የሰው ማንነት  በሰይጣን የቀጥታ አለቅነትና የበላይነት የሚገዛና የሚታዘዝ መሆኑን እንዳይታወቅ መታወሩና ይህንን ክፉ የጭካኔ የመግደል ተግባሩን ለአገር ፍቅር ብሎ እንደሚያደርገው ማሰቡ ነው። የአንድ ነገር ምክንያት ትክክለኛ እንደሆነ ከተሰማን የምናደርገው ነገር ትክክል እንደሆነ እንዲሰማን ያደርጋል። ምክንያቱ የተሳሳተ እንደሆነ ካወቅን ብቻ ነው ድርጊታችንን ልንገታ የምንችለው። ይህንን ካልን አሁን ከነዚህ ችግሮች ሁሉ ጀርባ ያለውን እውነተኛ ምክንያት እንመልከት። በኢዮጵያና በሌሎችም አገሮች  ያለው ዓመጽና ግድያ ህዝብ በህዝብ ላይ መንግስት በመንግስት ላይ ያለው መነሳሳት በህብረተሰቦችና በግለሰቦች ውስጥ ያለ ስር የሰደደ ጥላቻ ምክንያቱ ሌላ ምንም ሳይሆን ከጀርባ ያለው የጨለማው ገዢና አለቃ ነው። በታላቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳየንን ታሪክ እናገኛለን። ይህ ታሪክ የቃየንና የአቤል ታሪክ

«ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።….ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።» ዘፍ.4፡4-5፡8

ለምን እግዚአብሔር የአቤልን መስዋእት ተቀበለ የቃየንንስ ለምን አልተቀበለም? የዚህ ምክንያቱ  አቤል መስዋእቱን በእምነት ማቅረቡ እንደሆነ በሌላ ስፍራ ይነግረናል።

«አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል።» እብ.11፡4።

ታሪኩን ላይ ላዩን ስናነበው ቃየን ወንድሙን አቤልን የገደለው በቅናት ተነሳስቶ ይመስላል። እግዚአብሔር የርሱን ትቶ የወንድሙን መስዋእት ስለተቀበለ ቀንቶና ተናዶ ገደለው።ላይ ላዩን ሲታይ ጉዳዩ ይህን ይመስላል። ቃየን ወንድሙን በድንጋይ ለመግደል ይህ ምክንያት በቂ ሆኖለታል። እውነተኛው ምክንያት ግን ከጀርባው ያለ ሌላ ግብዳ ምክንያት ነው። ይህንን ከጀርባ ያለውን ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ እንዲህ ይገልጸዋል። «ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።» 1.ዮሐ.3፡11

አያችሁ እውነተኛው ምክንያት ይህ ነው። ቃየን ከክፉው ነው። ክፉው የሚባለው ደግሞ ሰይጣን ራሱ ነው። በቅናት ቁልፍ ልቡን  ከፍታ በርሱ ለመንገስ በልቡ ደጅ ታደባ የነበረችው ኃጢአት የዲያብሎስ ተፈጥሮ ናት። ልቡ ስለከፈተላት ከሰይጣን ጋር አንድ አደረገችው።  የራሱ አስመስላና ቅናቱን አቀጣጥላ ወንድሙን በድንጋይ አስገደለችው። የወንድሙ መስዋእት ተቀባይነት ማግኘቱና የርሱ ግን አለማግኘቱ ወንድሙን ለመግደል በቂ ምክንያት እንዲመስለው ታወረ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰውን ያውም የናትና የአባቱን ልጅ ገደለ። በርሱ ግድያ ሰውን መግደል «ሀ» ብሎ ጀመረ።

ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ነፍሰ ገዳዩ ቃየን ግን ጉዳዩን እንደዚህ  አይመለከተውም፡ በደጅ ያደባችውን የሰይጣን ኃጢአት ልቡን ከፍቶ አስገብቷታልና ልቡን አሳወረችው። ወንድሜን የገደልኩት ከሰይጣን ስለሆንኩ ኃጢአት ስለነገሰችብኝ ቀድሞ በመምጣት የገሰጸኝንና እንድነግስባት የመከረኝን አምላኬን ባለመስማቴ ነው ብሎ አልተጸጸተም። በዚህ ስፍራ በግልጽ እንደምናየው ቃየን ወንድሙን የገደለበት ዋናው ምክንያት ከክፉው ስለሆነ፣ የሰይጣን መገለጫ ስለሆነ፣ ጨለማ የሆነውን ማንነቱን ስለፈታና ስለለቀቀው ነው። ወገኖች ሆይ ዛሬም እንዲሁ ነው የቱንም ያህል በአገር ፍቅርና በነጻነት ስም ይሸፈን ሰውን መጥላት ሰዎችን በዘርና በብሄር እየከፋፈሉ ማጋጨትና በሰላም እንዳይኖሩ ማድረግ፣ እርስ በርስ በጦር እንዲፈላለጉ ማነሳሳት፣ ጎረቤትን በጎረቤቱ ላይ ማነሳሳት፣ እንዳይተማመኑና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲያየው ጥላቻን መዝራት፣ አልፎም ሰዎችን መግደል በሰይጣን ጋሻ ጃግሬነት ከሚመራው ከጨለማው ማንነታችን እንጂ ከአገር ወይም ከህዝብ ፍቅር የሚመነጭ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ ላይ ያለው መንግስትና ባለስልጣኖች ሰውን ቢጨቁኑ መልካም አስተዳደርን ቢነፍጉ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት ህዝቡን በታማኝነት ባያገለግሉ ይህን ማድረጋቸው  ክፉ ቢሆንም  ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ጦርነትን በማወጅ ሰዎች ለማጫረስ የሚሰብኩት ግን ከነርሱ የከፉ የጠላት መገለጫዎች ናቸው። ብልህ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል እንደሚባለው የሚሻለውን መልካም አስተዳደርና ሰላምን ማምጣት ያለብን በብዙ ድካምና በረጅም አመታት ጉዞ ያገኘነውን ትንሽም ቢሆን ሰላምና መረጋጋት በመጠበቅ ነው እንጂ እርሱኑ ንደን ከዜሮ በመጀመር አይደለም። ስለዚህ ይህንን ለማንበብ እድል ያገኘህ ወገኔ ሆይ ሞኝ አትሁን። ራስህን ለሰይጣን መጠቀሚያነት አሳልፈህ አትስጥ። በቅን ልብ ለህብረተሰብ ጥቅም የሚጥሩ ሰዎች ጦርነትን በማወጅ ሰውን በሰው ላይ በማነሳሳት አይታገሉም። ፍቅርን ሰውን ሁሉ መቀበልን  መተሳሰብን ታጥቀው ነው የሰዎችን ልብ የሚያሸንፉት። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በየሚዲያው ለጦርነት እንድትነሳ የሚሰብኩህን ሰዎች አትስማቸው። ከዚህ ክፉ ጨለማ የሆነ ማንነት ነጻ እንዲወጡ ጸልይላቸው። እንደብዙዎቹ ተታለህ በወጥመዳቸው ውስጥ አትግባ። መግደል፣ ጥላቻ፣ ጎረቤትን በጎረቤት ላይ ማነሳሳት በማንኛውም ወገን ይፈጸም የሰይጣን የዲያብሎስ አላማ ነው።

የህብረተሰቡ መልካም አስተዳደር እጦት አሳዝኖአቸው ያ እንዲሻሻል እየጣሩ ያሉ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው። አሁን በየመስኮቱ ጦርነትን ሲያውጁ የምንሰማቸው ምሁራን ነን ባዮች ግን ሳያውቁት የጨካኙ የዲያብሎስ መልእክተኛ የሆኑ፣ ሰው ዳነ ብለው ሳይሆን ሰው ሞተ ብለው መዘገብ የሚወዱ፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ደም ምንም የማይመስላቸው ናቸው። ብቻ የነርሱ አላማ ተፈጽሞ ስልጣን ላይ ይውጡ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሹ ቢሞት ምንም የማይመስላቸው ናቸው። እነርሱን መስማት ለችግራችን መፍትሄ አያስገኝልንም። እነርሱ የችግሩ አካል እንጂ የመፍትሄው አካል አይደሉም። ህዝቡ ከነርሱ ተነጥሎና ሰላማዊ መንገድን በመከተል መንግስትን መጠየቅ ይችላል። ይህ ቀላል ነው ማለት ሳይሆን ትክክለኛ ነው።  አንድ ሰው ሞቶ በአንድ ቀን ለውጥ ከምናገኝ ምንም ሰው ሳይሞት ከአንድ አመት በኋላ ለውጥ ብናገኝ ይሻላል። የሰው ልጅ ክቡር ነው መሞት የለበትም። ሰዎችን ማጫረስ የሚፈልገው ሰይጣን ብቻ ነው።  መቸም በርሱ ሐሳብ የታወሩ ብዙዎች ይህንን ይረዱልኛል ብየ አልጠብቅም በጣም ርቀው ወደ ጨለማው ጉድጓድ ያልገቡ ግን ቆም ብለው እንዲያስቡ ይረዳቸዋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ አሁን የሚታየው ዓመጽ የተነሳበትን ትክክለኛ ምክንያት ስናስተውለው ከሚባለው ያለፈ ነው። ሰውን በብሄሩ በቋንቋው እንድትጠላው የሚያደርግህ ሰይጣን ነው። በሰዎች ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ እንዲኖርህ የሚያደርግህ ሰይጣን ነው። ፍትህን ነጻነትን ሰላምን አንድነትን ለማምጣት በሚል ምክንያት ጦርነትን የሚያሳውጅ ሰይጣን ነው። ትክክለኛው ሰውነታችንና ህሊናችን ግን ሁሉንም ሰው እንድንወድ በሰላም እንድንኖር ይጠራናል። ሰው ሆይ ወደ ህሊናህ ወደ ተሻለው ማንነትህ ተመለስ። በሌላ ላይ ሳይሆን በዓመጸኛውና በክፉው ማንነትህ ላይ ዝመት። ሰውን በቋንቋው፣ በዘሩ፣ በብሄሩ፣ እያሳበበ እንድትጠላውና እንድትገድለው የሚያነሳሳህን  ድምጽ እሺ አትበለው። ክፉዉን በመልካም አሸንፍ። አሳስተው ነግረውህ ነው እንጂ  ሰው ሁሉ ከአንድ አዳም የተገኘ ወንድምህና እህትህ ነው። ሁሉም ሰው አንድ ነው። በሰዎች መካከል ልዩነት የለም ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጉራጌው ነጩ ጥቁሩ ዘርህ ማንነትህ ነው ። ሁሉም ሰው በሚለው «ክበብ» ውስጥ ያለ ፍጥረት ነው። ለክፉ ፖለቲከኞችና ለክፉ ሀይማኖተኞች አእምሮህን አታስማርክ። ህሊና የምትባል ትንሽ የጭላንጭል ቀዳዳ አለች በዚያች አልፋ በምትገባው ብርሃን ብቻ ተራመድ። ከላይ ያነሳነውን ምሳሌ ደግሜ ልጨርስ። ህመም ቢኖርም ትክክለኛ መድኃኒት እንፈልግ እንጂ ህመሙን የሚያባብስ መድኃኒት አንምረጥ። ጉሮሮዋ ላይ ያለውን በሽታ ልትታከም ሄዳ ሆድዋን ቀዶ ጥገና እንደተደረገችው አንታለል። አሁን ላለው የመልካም አስተዳደር መፍትሄው ዓመጽ ማስነሳት፣ ህዝብን በህዝብ ላይ ማስነሳት፣  ጦርነትን ማወጅ፣ ወንድምን በወንድሙ ላይ ማነሳሳት ሳይሆን በሰላምና በፍቅር አንድ ላይ ቆሞ መንግስትን በሰላማዊ መንገድ መሞገት ነው። አለዚያ በሽታው ያለበትን ቦታ ትተን በሽታ የሌለውን ቦታ የምንታከም ሞኝ ሰዎች ነው የምንሆነው። ይህ ደግሞ ሌላ በሽታ ይወልድብናል።

ሰው ሆይ ወደ ህሊናህ ተመለስ።

%d bloggers like this: