What is the standard of our braveness? የጀግንነት መለኪያችን ምንድን ነው?

What is the standard of our braveness? የጀግንነት መለኪያችን ምንድን ነው?

አባቴ ጀግና ነበር። ጀግንነትን በመጀመሪያ ያየሁት በርሱ ነው። ከጀግንነቱ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ነበሩ። አንደኛ ቃሉን በጣም ያከብራል ተናገረ ማለት አደረገ ነው። በዚህ አገሩ ህዝቡ ሁሉ ያውቀዋል። በዚህ ምክንያት ቃሉ ፊርማው የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር። አባቴ ፈርም ሳይባል ነው ያለፈው። ቃል ቃል ነው ይላል። ሌላው አባቴ ድሆችን ይረዳል። ያለኝ የኔ ብቻ ነው የሚል እምነት የለውም። ለሰው የሚኖር ነው። ከብዙ ዓመታት በፊት በአገሩ ድርቅ ሆነና ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ተሰደዱ። ገበያ ውሎ ሲመጣ ብዙ የሚያውቃቸው ሰዎች አገር ጥለው እንደሄዱ ተነገረው። ከዚያም በማለዳ ተነሳና ሲከተላቸው ውሎ ደረሰባቸው። እኔ እያለሁ አገራችሁን ጥላችሁ አትሄዱም። ለዚህ ክረምት የሚበቃችሁን እኔ እሰፍርላችሁአለሁ። ከዚያ ደግሞ ፈጣሪ ያውቃል ብሎ ወደ ቀያቸው መለሳቸው። አንድ ዓመት ሙሉ ሲቀልባቸው ኖረና የችግሩ ጊዜ አለፈ። ይህ ውለታው በመንደሩ ሲነገርለት ይኖራል። አባቴ ለድኃ ተሟጋች ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ሰው መንገድ ላይ አዝኖ ሲሄድ ያገኘውና ምን ሆነሃል ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም ፍርድ ቤት በግፍ መሬቱን ለባለጋራው እንደፈረደበት ሲነግረው ና እንሄድ አለና ይግባኝ ጠይቆ ተማገተለት ረታለትም ያ ሰው ከሰላሳ ዓመት በኋላ አግኝቶኝ እንባ እየተናነቀው የአባቴን ጀግንነት ነገረኝ። አባቴ ጀግና ነው። አገሩ በጣልያን ስትወረር በመዝመት ከጠላት ተከላክሎአል። አባቴ ጀግና ነው ትጉ ሰራተኛ በመሆን ትጋትን ለልጆቹ አስተምሮአል። ከአባቴ ከቤቴ የተማርኩት ጀግንነት ይህ ነው። ለሰው መኖር ተግቶ መስራት ቃልን ማክበር ወዘተ። በታሪክ እንደተማርኩት ደግሞ የኢትዮጵያ ጀግኖች አገራቸውን ነጻ አገር አድርገው ለማቆየት ህይወታቸውን ገብረዋል። ዘመናዊ ትምህርት ሳይማሩና በጣታቸው እየፈረሙ በዘመናዊ መሳሪየ እስካፍጢሙ የታጠቀውን ወራሪ መክተዋል። ብሄርና ጎሳ ሳይለዩ ሁሉም አንድ ላይ ሆነው ለአገራቸው ቆመዋል።በዚህም ምክንያት ነጻ ሆነን ተወልደናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ስለነጮች የምናስበውና በነርሱ ግዛት የነበሩ ጥቁር ህዝቦች የሚያስቡት እጅግ የተለያየ ነው። እኛ አስተሳሰባችን በነጻነት የተቃኘና የተመሰረተ ነው። ከዚህ ሁሉ የተማርኩት እውነተኛው ጀግንነት አገርን መውደድ ህዝብን መውደድ። ለሌሎች መኖር ። በነጻነት ህሊና እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ። ጎረቤትነትን አክብሮ መኖር ቃልን መጠበቅ፡ እርስ በርስ መቀባበልና መከባበርን ነበር። አሁን አሁን ስመለከት ግን ጀግንነት በሌላ መንገድ የገባው ወይም በራሱ እይታ የራሱን ጀግንነት የፈጠረና የጀገነ ትውልድ እያየሁ ነው። እናንተስ ይታያችኋል? በዘርና በብሄር የመለያየት ጀግንነት። የሌላውን ቋንቋና ብሄር የማጥላላት ጀግንነት፡የጎጥ ጀግንነት የጦርነት ጀግንነነት የነጭ ባሪያ ሆኖ የነርሱ ተላላኪ የመሆን ጀግንነት በዝቶአል። የጀገነ ሁሉ ወደ ፌስ ቡክና ዩቱዩብ ጫካ እየሸፈተ የቪዲዮ ምንሽሩን እያነሳ ነው። ስድብን መተኮስ ጥላቻን መዝራት እንደ ጀግንነት የተቆጠረበት ጊዜ ሆኖአል።  አንድ ሰው ጎበዝ ተሳዳቢና ዘርን በዘር ላይ የሚያነሳሳ ከሆነ እንደ አንበሳ ገዳይ ይሸለልለታል። በአባቴ ዘመን የሚያስወግዘው ነገር አሁን የጀግንነት መለኪያ ሆኖአል። የድሮዎቹ ጀግኖች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አስወግደው ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሙ የአሁኖቹ ግን ኢትዮጵያዊ የተናገረው የማይዋጥላቸው የነጭ አሽከሮች ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ለነርሱ ሲል አንድ ቆዳው ነጣ ያለ ቃል አቀባይ ቢቀጥር ጥሩ መሰለኝ። ምክንያቱም ለኢትዮጵያ እንታገላለን የሚሉት ሁሉ ትግላቸውን የሚጀምሩት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውን በመናቅና ከነጭ ጋር በማበር ሆኖአል። ነጮቹ እንደሰው እንኳ እንደማይቆጥሩአቸው አላወቁም። ስለዚህ ነጋ ጠባ እነርሱ በር ላይ ሲጮሁ ይውላሉ። ቀኝ ገዢነት ማለት ምን እንደሆነ ረስተውታል። ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረው እኮ ጥቁር ራሱን በራሱ ማስተዳደር አይችልምና ላግዘው ብሎ ነው። አባቶቻችን ግን አስተማሩት። ዛሬ ያለው ትውልድ ግን ለነጮቹ ትክክል ናችሁ እኛ ራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር አንችልም። ያለእናንተ እርዳታ መቆም እንችልም። እርስ በርሳችን መነጋገርና መሰማማት እንችልምና ኑ ግዙን ድምጻችሁን አሰሙን እያለ ነው። ይህ ሁሉ ህዝብ ፍትህን ፍለጋ እንደሰው እንኳን ከማይቆጥሩት ነጮች በር ተኮልኩሎ ሲውል ያሳዝናል። እንዲያ በማድረጉም ጀግና ይባለል። አባቴ  አይስማ። አባቴ ጀግና ነበር። ጀግንነቱም ከራሱ ከኢትዮጵያ መንግስትም ጋር አጋጭቶታል። ነገር ግን እርዳታ ፍለጋ ወደ ፈረንጅ አልሄደም። እርሱ ራሱ በኢትዮጵያዊነቱ ተጋጠመው። ዛሬም በኢትዮጵያ መንግስት ችግር የለም አልልም። የተለያዩ ችግሮች ሁልጊዜም ይኖራሉ። ጀግና ማለት ግን ኢትዮጵያዊነቱን ሳያወልቅ ሳይተው ለፈረንጅ ሳይሰግድ እርስ በርስ ተመካክሮ ተደማምጦ ተከባብሮ የሚፈታ ብቻ ነው። ስለዚህ ጀግንነታችን መለኪያው በየፌስቡኩ ሲሳደቡና ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጣሉ መዋል ሳይሆን መልካም ጉርብትናን በመስበክ ሰዎችን በመውደድ በመከባበር በመሰማማት የሚገለጥ ይሁን። አብዝታችሁ በመሳደባችሁና ህዝብን በማበጣበጣችሁ ጀግንነት የተሰማችሁ ሁሉ ጀግኖች አይደላችሁም። ጦርነት በማወጅ ጀግንነት የተሰማችሁ ሁሉ ጀግኖች አይደላችሁም። ሰው ጀግና የሚባለው የውጭ ጠላትን ለመመከት ብቻ ሲከት ነው። በአገሩ ላይ በህዝቡ ላይ በፌስቡክም ሆነ በመሳሪያ ጦርነትን የሚያውጅ ግን ጀግና ሳይሆን ሰነፍ ፈሪ ነው። ከኮምፒውተር ጀርባ ሆኖ ቃላትን የሚተኩስ የፈሪ ፈሪ ነው። ጀግና ግን ሰላምን ፍቅርን አንድነትን እየሰበከ በህዝቡ መካከል ይኖራል።

አባቴ ጀግንነትን ስላስተማርከኝ አመሰግንሃለሁ።

%d bloggers like this: