Wefe-Gezit ወፈ-ገዝት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መምህር አሰግድን አወገዙ ሌሎችንም አስጠነቀቁ። - Melkam Zena

Wefe-Gezit ወፈ-ገዝት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መምህር አሰግድን አወገዙ ሌሎችንም አስጠነቀቁ።

Abune mathias

Wefe-Gezit ወፈ-ገዝት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መምህር አሰግድን አወገዙ ሌሎችንም አስጠነቀቁ።

ወፈ- ገዝት፡- የኢትዮጵያው ፓትሪያርክ «አቡነ»  ማቲያስ ጸረ ወንጌሎችን ትተው ወንጌልን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የሚሰብኩትን አወገዙ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ፓትርያርክም ሆነ እውነተኛ መንፈሳዊ  አባት እንደሌላት ገና ዛሬ ነው በደንብ የገባኝ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ መምህር አሰግድን ያወገዙበትንና ሌሎችንም ያስጠነቀቁበትን ቃለ ውግዘት ስሰማ እኚህ ሰውየ ወፈ ገዝት ናቸው እንዴ? ነው ያልኩት። ለነገሩ እኚህ ግለሰብ የተጻፈላቸውን እንደሚያነቡና የርሳቸው ውሳኔ  አለመሆኑ ከንግግራቸው ያስታውቃል። (ግለሰብ ያልኩአቸው መምህር አሰግድን ያዋረዱ መስሎአቸው ግለሰብ ሲሉት ስለሰማሁ እርሱ እውነተኛውን ወንጌል ስለሰበከ ግለሰብ ከተባለ እርሳቸው በሐሰት ሲያወግዙ ግለሰብ ቢባሉ አያንስባቸውም ብየ ነው። እርሳቸው እያልኩት ያለሁትም ስለሽበታቸውና ሽምግልናቸው ብየ ነው።) ወሳኙ ወይም አውጋዡ አካል ሲኖዶሱ መሆኑና እርሳቸውም ከሲኖዶሱ ጋር ተስማምተው መስራት እንዳለባቸው የሚጠበቅና አግባብ ቢሆንም እንደ ፓትሪያርክነታቸው ግን ከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነትና አባትነት ይጠበቅባቸው ነበር። ይህም ማለት አንዳንድ ጊዜ ሲኖዶስ በተወሰኑ ፓለቲከኞችና ለቃሉ ክብር በሌላቸው ሰዎች ተጠልፎ ትክክለኛ ያልሆነ ሐሳብ ሲያቀርብ እርሳቸው ከወንጌሉ ጋር ወግነው ሊቆሙና ትክክለኛ ያልሆነ ውግዘት እንዳይተላለፍ መከላከልና መሸምገል ነበረባቸው።  እርሳቸው ግን ወይም ለራሳቸውም እውነተኛው ወንጌል አልገባቸውም አለዚያም ስልጣናቸው በሲኖዶሱ እንዳይነካ በመፍራት ይመስላል እንደ ፖለቲካ ተጽፎ የቀረበላቸውን ሲያነቡ አይተናል።  እነ መምህር አሰግድንና እውነተኛውን ወንጌል በቅን ልብ የሚሰብኩትን ያወገዙት ከልባቸው አምነውበት ከሆነ ሰውየው ወንጌልን ሳይማሩ ነው ፓትሪያሪክ የሆኑት ማለት ነው። ምክንያቱም ወንጌልን የተማረና ለወንጌል ህይወቱን የሰጠ ያውም ይህን ለመሰለ ታላቅ ኃላፊነት የበቃ ሰው እውነተኛውን የመድኃኔ ዓለም ክርሰቶስን ወንጌል የሚሰብኩትን ሊያወግዝ አይችልምና። ውግዘቱን ያስተላለፉት ሲኖዶሱን ለማስደሰት ከሆነ ደግሞ ለክርስቶስ ኢየሱስ ሳይሆን ለስልጣንና ለስማቸው የሚኖሩ ስለሆኑ ለዚህ ስፍራ ብቁ ሊሆኑ አይችሉም። ከሁሉም የገረመኝ ውግዘቱን ሲያስተላልፉም እንኳ የሐዘንና የልብ መሰበር ስሜት አይታይባቸውም። አንድ አባት ልጁ ሲጠፋበትና ሲለየው እኮ ያዝናል። እኚህ ሰው መምህር አሰግድን ሲያወግዙ እርሱን እንደ እውነተኛ ወንጌል ሰባኪነቱ የሚቀበሉና በአገልግሎቱ የተጠቀሙ ብዙ ሺኅ ምእመናንም ነው እያወገዙ ያሉት። ታድያ ውግዘቱ እውነት ቢሆንም እንኳ ኖሮ ይህ ሁሉ ሰው ሲጠፋ አይታዘንም እንዴ? አንድ መንፈሳዊ አባት ይህንን ያህል ልጅ በአንድ ቀን ሲያጣ እኮ ሽልማት አይደለም። እንዴት አያዝኑም? ልባቸውስ እንዴት አይሰበርም? አንድ ወንድም ሲለይ እኮ አንድን ብልት የመቁረጥ ያህል ነው። ከአካሉ ከቤተ ክርስቲያን ብልቶች ሲቆረጡ የማይሰማቸው አባቶች ህያዋን ናቸው ትላላችሁ? ህያው የሆነ ሰውማ ይሰማዋል። ይህም ሰውየው እውነተኛ መንፈሳዊ አባት እንዳልሆኑና ውግዘቱም የእግዚአብሔር ስልጣን የሌለበት ተራ ውግዘት እንደሆነ ያሳያል።  በአባቶቻችን ሐዋርያት ከነሱም በኋላ በተነሱት ቅዱሳን የእምነት አባቶቻችን ውግዘት እንዲህ ቀላል አልነበረም። እነርሱ የሚሉትንና እነርሱ የሚያደርጉትን  ጥቃቅን ነገር የማያደርገውን ክርሰቲያን ሁሉ አያወግዙም ነበር።  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በርሱ ላይ መከራ እያመጡ ወንጌልን የሚሰብኩትን እንኳ አላወገዘም። ስለነዚህ ሰዎች ሲናገር

«አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።» ይላል። ፊሊ.1፡15-18።

ስለዚህ ቅዱሳን ሐዋርያትና ከነርሱም በኋላ ያስቀመጡልን የእምነት ፈለግ ከነርሱ ጋር በጥቃቅን ሐሳብ ያልተስማማውን ሁሉ ሳይሆን ዋና በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ላይ የተሳሳተና የተዛባን ትምህርት ያስተማረ እንደሆነ ብቻ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት ሌላው ቀርቶ «ቅዱሳን አያማልዱም ያለን ወይም ማርያም አታማልድም ያለን ሰው እንኳ አላወገዙም። ለነገሩ በዚያን ዘመን ገና እውነተኛው ወንጌል በሐሰት ስላልተቀበረ «ማርያም ታማላድለች» የሚል ትምህርትም አልነበረም። በሐዋርያት ሥራ ምእራፍ አንድ ላይ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶሰ በክብር ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከደቀመዛሙርቱ ጋር አብራ እንደነበረች ሉቃስ ይነግረናል።

«በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር። ሐዋ.1፡12-14 ይላል።

ይህ በዚህ እንዳለ በሐምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በነርሱ ላይ ወረደና ሞላቸው። በዚያ የነበሩት ህዝብ ጎሽ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል ብለው ሲናገሩ   ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ ስለኢየሱስ ክርሰቶሰ ሞትና ትንሳኤ እንዲሁም በአብ ቀኝ ስለመቀመጡ ተረከላቸው። የወንጌሉንም ቃል ከሰሙ በኋላ ህዝቡ ልባቸው ተነካና ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ብለው ጠየቁአቸው። ልብ በሉ ቅድስት ድንግል ማርያም ከነርሱ ጋር በመካከላቸው አለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በዛሬው ዘመን እንዳሉት ሰባኪዎች እናቱን ከልጅዋ ጋር እንድታማልዳችሁ ጥይቁአት አላለም። በአካል ከርሱ ጋር ቆማ ሳለች እንዲህ አለ

«ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። ሐዋ.2፡38-39።

እውነተኛው ወንጌል ይህ ነው። ሰው ወደ እግዚአብሔር መመለስና የዘላለምን ደህንነት ማግኘት የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በጥምቀት ሞቱንና ትንሳኤውን በመተባበር ብቻ ነው። ስለዚህ በአባቶቻችን በሐዋርያትም ሆነ ከነርሱ በኋላ በተነሱት የእምነት አባቶቻችን አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን የሚለየው የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት እንዲሁም አዳኝነቱን ካልተቀበለ ብቻ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ቢሆን የሚያስተምረን ይህንን ነው። እስኪ እንመልከተው።

«ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና። 2ኛ ዮሐ.9-11።

ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ነው የሚለው። ስለዚህ አንድን ሰው ሊያስወግዘውና ከቤተ ክርስቲያን ሊያስለየው የሚችለው ይህ ብቻ ነው። አርዮስም ሆነ ንስጥሮስ የተወገዙት ማርያም ወይም ሌሎች ቅዱሳን አያማልዱም ስላሉ ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት ስለካዱ ነው።ውግዘት ቀላል ነገር አይደለም። ውግዘት በትክክል ከተከናወነ ከዘላለም ሕይወት የሚለይ ነው «አማን እብለክሙ  ዘአሰርክሙ በምድር ይከውን እሱረ በሰማያት ወዘፈታሕክሙ በምድር ይከውን ፍቱሐ በሰማያት» ማቴ.18፡18 በማለት ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው ስልጣን ታላቅ ስልጣን ነው። ሐዋርያት ግን ከነርሱ ጋር የተጣላውን ሁሉ አላወገዙበትም። ስማቸውንና ክብራቸውን ለማስጠበቅ አላዋሉትም። ስልጣኑ የነርሱ አይደለምና ለትክክለኛው ሁኔታ ካልሆነ በቀር አይሰራም።ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተስማምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ስልጣን ነው። አለዚያ የአስቄዋ ልጆች ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጋንንትን ሲያወጣ ያዩት የአስቄዋ ልጆች በኩረጃ የሚሰራ መስሎአቸው ራሳቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑና ሳይከተሉት «ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን» በማለት ሲሞክሩ በአጋንንት ቆሳስለውና ተሸንፈው እንደሸሹት ይሆናል። ኢየሱስ ክርሰቶስ ከኛ ጋር ካልሆነ በስሙ ምንም ማድረግ አንችልም። እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስ ባላደረባቸው ጳጳሳት የሚተላለፍ ውግዘት ስልጣን የለውም። ግን መንፈስ ቅዱስ እንዳላደረባቸው በምን እናውቃለን? ለምትሉ ጠያቂዎች መልሱ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት አምነው ወንጌሉን የሚሰብኩ ሰዎችን አያወግዝም የሚል ነው።መንፈስ ቅደስ ሁልጊዜ ከእውነተኛው ወንጌል ጋር እንጂ ከሐሰት ጋር ከፖለቲካ ጋር ከሥጋውያን ጋር አይሰራም። ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችንም ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ከመውረዱ በፊት ስለሚመጣበት ዓላማ ሲናገር  «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።» ብሎ ተናግሮአል። (ዮሐ.16፡12-14) መንፈስ ቅዱስ  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማክበር ነው የመጣው። ኢየሱስ ክርሰቶስ ሲሰበክና ሲከብር ደስ ይለዋል ዓላማው ይህ ነውና። እንግዲህ ቅዱሳን ሐዋርያትና አባቶቻችን ያወገዙት መንፈስ ቅዱስ ያከበረውንና የሚያከብረውን ኢየሱስ ክርሰቶስን ያላከበሩትን እንደነ አርዮስ ያሉትን እንጂ ከዚህ ውጭ በሆኑ ጥቃቅን ምክንያቶች ውግዘትን አላስተላለፉም። ከዚህ ሌላ  አንድ ምእመንም ሆነ አገልጋይ ጥፋቶችን አጥፍቶ ቢገኝ  ለጊዜው የሚሰጠው ቀኖና ሲሆን ይህም አንድ ሰው ከተሳሳተው ሥጋዊ ስህተት ተመልሶ እንዲታደስ የሚሰጠው ተግሳጽም ሆነ ቅጣትን ያጠቃልላል። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን በአንደኛ ቆሮንቶስ ላይ ያለው የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ነው። ይህ ሰው በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ቅጣትን የተቀበለ ሲሆን በኋላ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልሰው ምህረት እንዲያደርጉለት ሲጽፍላቸው እናያለን። አሁን በቤተ ክርስቲያናችን እየተወገዙ ያሉት መምህር አሰግድም ሆነ ሌሎች ብዙዎች በነዚህ ነገሮች ተከሰው ማስረጃ አልቀረበባቸውም ተጠርተው በሲኖዶሱ ፊት አልተጠየቁም።እንዲሁ ዝም ብሎ ተወግዘዋል እየተባለ መግለጫ ይሰጣል።አንድ አስተዋይ ልቡና ያለው ኒቆዲሞስ በሲኖዶሱ መካከል የለም። ኢየሱስ ክርስቶስን በሐሰት ክስ ሲከሱት በነበሩት ፈሪሳውያን መካከል አንድ አስተዋይ ልቡና ያለው ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር። ይህ ሰው በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውና በኋላም ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስን የገነዘው ነው። በፊረሳውያኑ መካከል እንዲህ በማለት ነበር የተናገረው።

«ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ፦ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፦ አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። ዮሐ.7፡50-52 ይላል።

እነርሱ በጭፍንና እንዲሁ ከገሊላ መልካም ነገር አይወጣም እያሉ በትምክህት ቢፈርዱም እርሱ ግን እውነትን ነበር የተናገረው። በአሁኑ ሲኖዶስ ውስጥ አንድም ኒቆዲሞስ አለመገኘቱ ግን ገርሞኛል። እንዲያው በቀን በብርሃን በግላጭ ኢየሱስ ክርሰቶስን መከተልና ለወንጌሉ መቆም ቢያቅታቸው እንደ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ እውነቱ መምጣት አቃታቸው? ያሳዝናል። አሁንም ያለው ሲኖዶስ (የፈሪሳውያን ጉባኤ ብለው ይሻለኛል) አንድ ሰው ከኛ በበለጠ ሁኔታ እንዴት ወንጌል ይሰብካል? አንድ ሰው የጳጳስ ልብስና ቆብ ሳያጠልቅ እንዴት ወንጌልን ሰብኮ ተቀባይነት ያገኛል በሚል ቅንአት ብቻ ተነሳስተው ወንጌሉን የሚሰብኩትን ተግተው እያወገዙ ነው። እነዚህ እየተወገዙ ያሉ ሰዎች ግን ኢየሱስ የሚያስወግዘውን ሳይሆን የማያስወግዘውን ነው እያደረጉ ያሉት። ወንጌልን ነው እየሰበኩ ነው ያሉት። አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ከሰበከ ሲኖዶሱና ፓትሪያሪኩ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስለሰበክህ አውግዘንሃል ካሉ በእውነት በሰማያት የተወገዘው የቱ እንደሆነ እናውቃለን። እግዚአብሔር እነርሱ ያሰሩትን ሁሉ ሲያስር የሚውል መስሎአቸዋል። በእግዚአብሔር ፊት የተወገዘው ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራንዮ መስቀል የሞተውንና በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተነስቶ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማያት ያረገውን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይሰብክና የሚሰብኩትን የሚያሳድድ ብቻ ነው። ግለሰቡ (ፓትሪያሪኩ) ውግዘቱን ሲያነቡ አንድም እንኳ ሊያስወግዘው የቻለውን ስነ መለኮታዊ ተፋልሶ ወይም በኢየሱስ ከርስቶስ ላይ ምን አይነት የተሳሳተ ነገር እንዳስተማረ አልተናገሩም። ይህም የሚያሳየው ያወገዙት እንዲሁ ስለማይወዱትና ማውገዝ ስለሚወዱ ማንንም ሳያወግዙ ሲኖዶሱ እንዳይበተን ነው። ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ሰው እያወገዘች የምትለይበት ሰአት ነው? ለመሆኑ ምን ነው አርቀው ማየት አቃታቸው? አባቶቻችን በብዙ ተጋድሎ ያቆዩን የወንጌል እውነት እኮ ከቤተ ክርስቲያኒትዋ እየተሰረዘ በተለያዩ ዘመናት ለሆድና ለፖለቲካ ተብለው በተደረሱ ገድላትና በፖለቲካ እየተተካ ያለበት ጊዜ ነው።ካወገዙ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ሆነው እንዳይሸሙ የደነገጉትንና በስንክሳር ሳይቀር አስጽፈው የእግዚአብሔር ውሳኔ እንደሆነ እንድናምን አድርገው ሲያታልሉን የኖሩትን የቤተ ክርስቲያን ፖለቲከኞች አያወግዙም ነበር? ወጣቱ ትውልድ እኮ በግእዝ ተሸፍኖ ሲነበብለት እውነት መስሎት አሜን እያለ ሲያምነው የኖረውን ሐሰት አሁን በሚገባው ቋንቋ ተተርጉሞ ሲያነበውና ከቅዱሱ ወንጌል ጋር ሲያስተያየው ሐሰት ሆኖ ስላገኘው ነው ሆ ብሎ የተነሳው። ለፖለቲካዊ ጥቅምና ለእንጀራ መብያ ተብለው የተጻፉ ገድላት በወንጌሉ ይፈተሹ በማለቱ እንዴት ይወገዛል? ጳጳሳቶቹ በዚሁ ከቀጠሉ ሐሰትን አላምንም ያለውን ወጣት ሁሉ አውግዘው እንደሮም ካቶሊክ የሚያነቡላቸውን ሁሉ እየሰሙ አሜን የሚሉና ማንበብ የማይችሉ ጥቂት የእድሜ ባለጸጎችን ብቻ ይዘው እንደሚቀሩ የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንዋን ተረካቢ የሌላት የወላድ መካን ያደርጋታል። 64 ፐርሰንት ወጣት ባለባት አገር ወጣቱ የሚጠይቀውን የወንጌል ጥያቄ በአግባቡ የማትመልስ ቤተ ክርሰቲያን ምን ሊገጥማት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ከእስልምና ወጥተው በወንጌሉ ተማርከው ወደ ቤተ ክርስቲያንዋ የመጡትንም ወጣቶች ሲያወግዙ አይተናል። ይህም ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን አለመማራቸውን ያሳያል።እስኪ ረጋ ብለን እናስበው አሁን ወንጌሉን ሰምቶና አምኖ  ከእስልምና የመጣ ሰው ይወገዛል? በአጠቃላይ ወጣቱ ትውልድ እውነተኛውን ወንጌል በቤቱ የሚያቀርብለት እረኛ አጥቶ ወደ ተለያዩ ቤተ እምነቶች እየጎረፈ ያለበት ጊዜ ነው። ይህንን ጉዳይ በሚሄደው ትውልድ ላይ ብቻ ማሳበብ ሞኝነት ነው። ልጃችንም እንኳ ቢሆን እንደሚገባ ካልመገብነውና በቤቱ ምግብን ካላቀረብንለት ጎረቤት ሄዶ መቀላወጡ የማይቀር ነገር ነው ረሃብ አያስችልምና። እንደዚሁም በአሁኑ ሰአት በቤተ ክርስቲያናችን እውነተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዳይሰበክ እየተከለከለና «ኢየሱስ» ያለ ሁሉ መናፍቅ እየተባለ ስለሆነ ሰዎች  ስለ ኃጢአታቸው ስለሞተላቸው የፍቅር ጌታ ለመስማት ወደ ጎረቤት ቤተ እምነት እየሄዱ ነው። ፓትሪያሪኩ የጠራ የአባትነት ልብ ቢኖራቸው ሲኖዶሱም ስለቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ጉዳይ አርቆ ቢያስብ ኖሮ ዘመኑ ሰዎችን በፍቅር እያቀፍን ወደ ቤተ እግዚአብሔር የምናስገባበት ዘመን እንጂ ወጣቱን ትውልድ የምንበትንበት አልነበረም። ቤተ ክርስቲያናችን ስለኢየሱስ ክርሰቶስ ወንጌል እንዳልተጋደለችና እንዳልሰበከች የእምነት አባቶቻችን ወገባቸውን ታጥቀው ለእውተነኛው ወንጌል እንዳልተሟገቱ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ክርሰቲያናችን ስፍራ አጥቶ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ስለርሱ ለመማር እንሂድ?!!!! የኢየሱስ ክርሰቶስን ስም በነጻነት ለመጥራትና ለርሱ ፍቅር ለመዘመር እነሸማቀቅ? ይህ እንዴት ያሳፍራል? ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ሰአት በአፍሪካ ቀንድ በአፍሪካ ስላለው ነገር አሻግራ መመልከት ትችላለችን? የተከበብነው በምንድን ነው? ለመሆኑ የከበቡንን አገሮች በወንጌል ለመድረስ ምን እያደረግን ነው? ወደነዚህ አገሮች ተልከው ወንጌልን የሚሰብኩና የሚያስፋፉ በቂ ሰባኪያን አሉን? እየላክንስ ነው? ሐዋርያት እኮ ወንጌል ሰባኪ ይልኩ የነበሩት የተተከለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሄዶ በቅዳሴ እንዲያገለግል አልነበረም። የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ባልተጠራበት ስፍራ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ እንደ ፊሊጰስ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሰርት እኮ ነው ወንጌል ሰባኪ የሚላከው። ዛሬ በዙሪያችን ስንት ወንጌል ያልተሰበከበት አገር አለ። እነ መምህር አሰግድንም ሆነ ሌሎቹን ከማውገዝ ቤተ ክርስቲያንዋ ለምን ወደኒዘህ አገሮች አትልካቸውም? ይህ ሁሉ የወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ እየጠበቀን ለማውገዝ ብቻ መኖር ምንድን ነው? ለመሆኑ በአሁኑ የሲኖዶስ ስብሰባ ለስብከተ ወንጌል በዙሪያችን ወዳሉ አገሮች የተላከ ሰው አለ? ይህማ ቢሆን መልካም ነበር ግን የለም። በአጠቃላይ አይናችን ተከፍቶ ብናይ አዝመራው ብዙ ነው ሰራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው። ሲኖዶሱም ሆነ ሁላችን የአዝመራው ባለቤት እንደተናገረው ሠራተኞችን እንዲልክ መጸለይ ይገባናል እንጂ የላካቸውን ሠራተኞች ማውገዝና ማባረር አይደለም። እንዲያው ሲኖዶሱ ያውግዝ እንኳ ከተባለ ዘረኝነትና ብሔረኝነትን የሚያዘሩትን፣ ቤተ ክርስቲያንዋን የሰላም ቤት ሳይሆን የጠብና የክርክር ቤት ያደረጉትን ሥጋዊያን፣ በመንፈስ ቅዱስ ሳይሾሙ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚኖሩትን፣ቤተ ክርስቲያንን  አሳንሰው የጎጃም፣ የጎንደር፣ የሸዋ፣ የትግራይ እያሉ በዘር የሚከፋፍሉትን ያለ ጉቦ የማይሰሩትን ለምን አያወግዝም? በአስተምህሮ ህጸጽ ላውግዝ ካለ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ ከሰጠበት እውነተኛው የመዳን ወንጌልና ሐዋርያት አባቶቻችን ካስተላለፉልን ወንጌል ሌላ የሆነና «ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም» ፣ «ማረያም ባትኖር ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ የለም» ወዘተ እያሉ ተረት ተረት የሚያወሩትን ለምን አላወገዘም? ይገርማል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያሪክና ሲኖዶስ ያለ ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም የሚሉትን ትቶ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ እኛን ከኃጢአታችን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በመስቀል ሞቶ ተነስቶ አዳነን የሚሉትን አወገዘ። ይህንን ፍርደ ገምድልነት የሚለው ቃል እንኳ አይገልጸውም። እውነት ለመናገር ችግር አለባቸው የሚባሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ፓርላማና ፍርድ ቤቶች እንኳ ከዚህ ሲኖዶስ ይሻላሉ። ፍርድ ቤቶች እኮ አንድ ሰው ሲከሰስ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥና ራሱን እንዲከላከል ይፈቅዳሉ። በአገሪቱ ህግ መሠረት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም ይቀጣል ካልሆነም በነጻ ይሰናበታል። ለመሆኑ የሲኖዶሱ ህገ መንግስት ምንድን ነው? የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አይደለምን? ሰው ሲከሰስ ለምንድን ነው በወንጌሉ ቃል ሚዛን የማይመዘነው? ለምንስ ነው ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ የማይፈቀድለት?

እኔ የአሁኑ ውግዘት ውግዘትን እንዳልፈራም ነው ያደረገኝ። ድሮ የያዙት ስልጣንና ወንጌል እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት እየሰመለኝ «አወገዙ» ሲባል በጣም ነበር የምፈራው የምንቀጠቀጠው። አሁን ግን ሌባና ቀጣፊውን ታቅፈው ቀንና ሌሊት በትጋት ንጹሑን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩትን እውነተኛ ሰባኪዎች ሲያወግዙ ስለሰማሁ ውግዘታቸው ቀልድ መሆኑ ገባኝ። ምክንያቱም ባለችኝ ትንሽ እውቀትና በህሊናየም ቢሆን እግዚአብሔር ከእውነተኞች ጋር እንጂ ከሐሰተኞች ጋር እንደማይቆም አውቃለሁና። ንጹህ ህሊና ያለውም ሁሉ እንደዚያ እንደሚያስብ እያየን ነው። ድሮ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ተወገዘ ሲባል ሁሉም ነበር ፈርቶና ግዝቱን አክብሮ ዝም የሚለው አሁን ግን ብዙዎች የግዝቱን ቀላልነት አይተውና ሰምተው ይህማ ትክክል አይደለም እያሉ ቃላቸውን እያሰሙ ነው። እንዲያውም በእውነተኛው ወንጌል የሚያምኑትና በሲኖዶሱና በፓትሪያሪኩ እየተፈጸመ ያለውን አለማስተዋልና ፓለቲካዊ ሂደትን የተላበሰ እርምጃ ለመቃወም በሰልፍ ወጥቶ መንበረ ፓትሪያርክ ድረስ በመሄድ ተቃውሞውን ማሰማት ነበረበት። ሁሉም በየተራው እስኪወገዝ ካልጠበቀ ወይንም እውነተኛውን ወንጌል ካልገፋ በቀር ይህ ግድ ነው። ሲኖዶሱ ሐሰትንና ፖለቲካን እየሰበኩ ህዝቡን የሚያስቱትንና ቤተ ክርስቲያንዋን የፖለቲካ መድረክ እያደረጉ ያሉትን ትቶ እንደቃሉ እውነተኛውን ወንጌል የሚሰብኩትን የሚያወግዝ ከሆነ ወንጌሉ ይሻለኛል የሚሉት ምእምናንና ቀሳውስት ሁሉ በየተራ መወገዛቸው ይቀጥላል። ስለዚህ እውነተኛውን ወንጌል የምናምን ሁሉ ተራችንን እየጠበቅን ከምንወገዝ ለእውነቱ ወንጌል ጸንተን በመቆም ልንሞግታቸውና ውግዘታቸው ውሀ እንደማያነሳ ልናሳውቃቸው ይገባል።

አመሰግናለሁ።

ናታኒም ነኝ ከመቅደሱ።

 

%d bloggers like this: